Page 1 of 1

የአፍሪካ ኅብረት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊጭበረበር እንደነበር አስታወቀ:-ተጠርጥረው ተያዙቀሲስ በላይ መኮንን

Posted: 01 May 2024, 13:45
by Za-Ilmaknun
የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚገኘው የባንክ ተቀማጩ ላይ ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማጭበርበር ወጪ ሊደረግ ሲል ማዳኑን ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል።

ሰኞ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ/ም ገንዘቡን ሊያወጣ የነበረውና በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብ የኅብረቱ ተቀጣሪ እንዳልሆነም አስታውቋል።

ግለሰቡ ለግንባታ እና ለውሃ ጒድጓድ ቁፋሮ ተከፋይ በሚል ባቀረባቸው የተጭበረበሩ ሰነዶች አማካይነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ሊያወጣ ሞክሮ እንደነበረ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የፀጥታ ባለሥልጣናት ወዲያውኑ ስለ ሁኔታው እንዲያውቁ መደረጉን እና ግለሰቡ በምርመራ አሰራር ደንብ መሠረት ተለይተው መያዛቸውን ኅብረቱ ማስታወቁን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

ተጠርጥረው ተያዙ የተባሉት ግለሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን :roll: መሆናቸውንና ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ አገልግሎት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዚያ 16፣ 2016 ጠበቃቸውን አነጋግሮ መዘገቡ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የስምንት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

https://amharic.voanews.com/a/au-bank-f ... 93590.html

Re: የአፍሪካ ኅብረት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊጭበረበር እንደነበር አስታወቀ:-ተጠርጥረው ተያዙቀሲስ በላይ መኮንን

Posted: 01 May 2024, 14:01
by Za-Ilmaknun
የቀሲስ በላይ የባንክ ማጭበርበር የደህንነት አቋሜን እንድፈትሽ አድርጓል ሲል አፍሪካ ሕብረት አሳወቀ

አፍሪካ ኅብረት፣ ከኹለት ሳምንት በፊት በግቢው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ለግንባታና ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በሚል በተጭበረበሩ ሰነዶች ሊወጣ የነበረው ገንዘብ 6 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጧል።

ኅብረቱ የተደረገበትን የማጭበርበር ሙከራ የፋይናንስ ሠራተኞቹ ማክሸፋቸውን ገልጦ፣ ሙከራው ግን በከፍተኛ አንክሮ የምመለከተው ክስተት ነው ብሏል። ኅብረቱ፣ የማጭበርበር ሙከራው በደኅንነት ሥርዓቱ ላይ ፍተሻ ለማድረግ በር እንደከፈተለትም ጠቅሷል።

በባንክ ሒሳቡ ላይ ወደፊት የማጭበርበር ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በትብብር እየሠራ መኾኑንም ኅብረቱ አስታውቋል።

Re: የአፍሪካ ኅብረት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊጭበረበር እንደነበር አስታወቀ:-ተጠርጥረው ተያዙቀሲስ በላይ መኮንን

Posted: 03 May 2024, 13:13
by Za-Ilmaknun
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን ላይ የክስ መመሥረቻ 15 ቀናት ፈቀደ:

በሐሰተኛ ሰነድ ከአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ገንዘብ ለማውጣት በመሞከር የተጠረጠሩት ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ መመሥረቻ 15 ቀናት በፍርድ ቤት መፈቀዱን ጠበቃ አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ዛሬ ሐሙስ 24/ 2016 ዓ. ም. ረፋድ ላይ በነበረው የፍርድ ቤት ውሎው ነው።

ቀሲስ በላይ እንዲሁም አብረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት አጃቢያቸው እና ሹፌራቸው ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት፤ ባለፈው ሳምንት በነበረው ችሎት ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ፖሊስ ስምንት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀዱ ነው።
https://www.bbc.com/amharic/articles/cgrjgnn5z6go