Page 1 of 1

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር:- በጉራጌ ላይ የተቀናበረ ሴራን ለማክሸፍ የጉራጌ ክልል መሆን አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው!

Posted: 05 Mar 2023, 16:01
by Wedi
ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር - International Gurage Association - IGA

በጉራጌ ላይ የተቀናበረ ሴራን ለማክሸፍ የጉራጌ ክልል መሆን አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው!

መግቢያ

የጉራጌ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያን መንግሥት ያቆሙ ዋና ዋና የጦር መሪዎችን ያፈራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አውራጃ ነበር። ጉራጌ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር ቅርብ ቁርኝት የነበረው ሕዝብ እንደነበር ተጽፎ እናገኛለን። የጉራጌ አውራጃ የውስጥ አስተዳደር ይመራ የነበረው በጉራጌ ተወላጅ መሪዎች ነበር።ይህ ማኅበረሰብ የሥራ ወዳድነት ገድሉ በበርካቶች የሚመሰከርለትና ለማንም ቢሆን አርዓያ ሊሆን የሚችል መገለጫው ነው። የጉራጌ ማኅበረሰብ የሥራ መንፈስ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዲጋባ የሥራ መንገድን የቀደደ ማኅበረሰብ ነው::

ጉራጌ በደርግ ዘመነ መንግስት በሶስት አውራጃዎች ውስጥ በስፋት ባህሉን ቋንቋውንና ማንነቱም በሚገባ ጠብቆ የኖረ ሕዝብ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ የጉራጌ ብሔረሰብ በሀገራችን ካሉት ከ3ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ሲሆን በበርካታ ትላልቅ ሀገራዊ ተቋማት የኃላፊነት ቦታዎችን በመያዝ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ ያለ ሀቅ ነው::

በ1983 ዓ.ም የሕወሀት መራሹ ኢሕአዲግ ደርግን አስወግዶ ስልጣን በያዘበት ጊዜ ኢትዮጵያን አሁን ያለችበትን ብሔርን እና ቋንቋን መሰረት ባደረገ መልኩ የማዋቀር ሥራውን ሲጀምር እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን በጠላትነት ፈርጆ ብዙ ሴራዎችን ሲሰራ እንደነበር ሀገረ ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው:: በጠላትነት የተፈረጁት በአብዛኛው ከዘረኝነት የፀዱና ለኢትዮጵያዊነታቸው ከፍ ያለ ቦታ ሲሰጡ የነበሩ ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው:: እነዚህ ሕዝቦች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ የፈረጀበት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩት:-

⏩የመጀመሪያው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው በመሆናቸው ለዘረኝነት ፖለቲካ በትልቁ ሊገዳደሩ ይችላሉ፤ብሎ መደምደም ሲሆን
⏩ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተቆጣጠሩ በመሆናቸው ፖለቲካውን በቀላሉ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ የሚሉ ነበሩ::

ከመግቢያው ላይ እንደተገለጸው የጉራጌ ማኅበረሰብ ደግሞ በሕዝብ ቁጥርም ሶስተኛ ወይንም አራተኛ ደረጃ የያዘ በመሆኑና በአብዛኛው ደግሞ ከተማ ስለሚኖር የነቃም ማኅበረሰብ ስለሆነ ፖለቲካው ላይ ከቁጥሩ በላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚችል ሕወሀት መራሹ ኢሕአዲግ በግልፅ ትንታኔ አስቀምጦ ነበር:: በሌላ በኩል በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ደግሞ የጉራጌ ማኅበረሰብ የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ስለነበረ ሕወሀት መራሹ ኢሕአዴግ በጉራጌ ማኅበረሰብ ላይ የነበረው ስጋት እጅግ የገዘፈ እንዲሆን አድርጎታል::

ስለዚህ ይህን ማኅበረሰብ በሴራ መበተን ወይንም መለያየት እንደሚያስፈልግ አምኖበት ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ሕወሀት ኢሕአዴግ የያዘውን ርዕዮተ ዓለም አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞችን በተለይ ደግሞ በማእከላዊዉ ኢትዮጵያ የማፅናት ችግር እንደሚገጥመው በግልፅ አውቆት ነበር:: በመሆኑም ከጫካ ይዞት የመጣውን መላው ዓለም የተፀየፈውን የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያ ላይ ለመትከል ጉራጌን ከኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲወገድና ሰፊውና ግዙፉን የጉራጌ ማኅበረሰብ በሴራ መበታተን ሥራ ከመጀመሪያው የስልጣን ዘመኑ ጀምሮ በሰፊው ሲሰራበት ኖሯል::

ጉራጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው በጉራጌ ላይ የተሰሩ ሴራዎች በወፍ በረር ለማስቀመጥ እንሞክራለን፡፡

⏩ ሴራ 1፡ ጉራጌ ያለፍላጎቱ በክልል 7 እንዲደራጅ የተሰራ ሴራ

በ1984 በተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የጉራጌ ማኅበረሰብ ቁጥር በአራተኛ ደረጃ ያለ ነበር፡፡ ለዘመናት የገጠሙትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ራሱን በራስ አገዝ ልማት ያደራጀ እንዲሁም ደግሞ ለዘመናት ያካበታቸው ጠንካራ የባህል እና የአብሮነት እሴቶች የነበሩት በመሆኑ በ1983 ዓ/ም በሽግግሩ ወቅት በቀጥታ እንደ ክልል እንዲደራጅ ከተወሰኑ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ጉራጌ አንዱ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሽግግር መንግስት ዋነኛው መሪ ህወሃት በመሆኑና ህወሃት ደግሞ ቀደም ብሎ ያስቀመጥናቸው ስጋቶች ስለነበሩት ለጉራጌ ክልል የተሰጠበትን ሀሳብ ቀይሮ ያለ ማህበረሰቡ ፍላጎት ክልል 7 በሚል ዋና ከተማውን ሆሳእና እንዲሆን ያደረገ አደረጃጀት ውስጥ እንዲገባ አደረገ፡፡ ይህ ሸፍጥ በወቅቱ የነበሩ የጉራጌ ምሁራን አባቶች የንግዱ ማኅበረሰብ አመራሩ እንዲሁም ወጣቱ አምርሮ ተቃውሞታል ታግሎታልም:: በወቅቱም ይህ ውሳኔ በመቃወም 34 የህዝብ ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው ወጡ:: ኢህአዴግም ያለ ጉራጌ ተወካይ ጉራጌ ላይ ወስኖ በዚሁ የክልል 7 አደረጃጀት እንዲቀጥል ተደረገ::

⏩ ሴራ 2፡ ጉራጌ ያለፍላጎቱ በደቡብ ክልል እንዲደራጅ የተሰራ ሴራ

ከጉራጌ ህዝብ ህዝብ ፍላጎት ውጪ የተቋቋመውን ክልል 7ን እንዲፈርስ በማድረግ በ1994 ከጉራጌ ህዝብ ጋር በቋንቋ በባህል በአኗኗርም ሆነ በስነልቦና ፈፅሞ ከማይመሳሰሉ ሌሎች 56 ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድ ቅርጫት ከተተው:: አላማውም የጉራጌ ስነልቦና እንዲጠፋና አንድነቱ እንዲላላ በማድረግ በውስጥ ችግሩ እንዲዳክር ማድረግ ነበር:: በዚህ ወቅትም የመንግስትን ኢፍትሀዊነት የተቃወሙ የጉራጌ ልጆች እጅግ ዘግናኝ በደል ደርሶባቸዋል:: በጉራጌ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች እንዲከስሙ ተደርጓል፡፡ በስርዓቱ ውስጥ አቅም ተነጻጻሪ አቅም የነበራቸውና የሕዝቡን ጥቅም የሚጠይቁ አብዛኞቹ የጉራጌ ፖለቲከኞች ከስርዓቱ ተገፍተው ወጥተዋል፡፡ ከክልል 7 ወደ ደቡብ ብ/ብ/ሕ የተደረገው የአደረጃጀት ለውጥ ጉራጌን የመስበር ሴራ አንድ አካል ነው፡፡

⏩ ሴራ 3፡ ስልጤን ከጉራጌ ለመነጠል የተሰራ ሴራ

ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የቆመውን ጉራጌን ለመስበር ህወሃት ኢሃዴግ ከአደረጃጀት መዋቅር በላይ የሆኑ ስራዎች መስራት ነበረበት፡፡ በባህልና በስነ ልቦና እጅግ የተዋሀደውን የጉራጌና የስልጤ ማኅበረሰብ የመሰንጠቅ ሥራም የዚሁ ሴራ አካል ነው፡፡ ይህ ስልጤን ከጉራጌ የመለየት ሥራ ከ1983 ጀምሮ በአቶ ቢተው በላይ መሪነት ሲሰራ የነበረ ሲሆን ጉራጌን ወደ ደቡብ ክልል እንዲገባና ከአስተዳደር፣ ከስልጣንና ከልማትም እንዲርቅ በማድረግ የስልጤ ማኅበረሰብ በጉራጌ ተበድለሀል የሚል ትርክትን ሲሰራ ቆይቶ በመጨረሻም የስልጤ ተወላጅ የሆኑ የአገዛዙ ተላላኪዎችን መልምሎና አሰልጥኖ የሴራ ሥራውን ተግባራዊ አደረገ::
ይሁን እንጂ ጉራጌን ከስልጤ የመለየት ሥራው ጉራጌን በቁጥርም ሆነ በኢኮኖሚ የበላይነት የማዳከም ሴራ የረባ ውጤት ያላስገኘለት ቢሆንም ጉራጌ እና ስልጤ አንድ ሆነው ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዳይፈጥሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

⏩ ሴራ 4፡ ጉራጌን እርስ በርሱ እና በጉራጌ ዞን ካሉ ብሔረሰቦች (ቀቤናና ማረቆ) ጋር የማናቆር ሴራ

➡️ 4.1) በዶ/ር ካሱ ኢላላ አማካኝነት የተካሄደው ጉራጌን ምሥራቅና ምእራብ ብሎ የመክፈል ሴራ በቅብብሎሽ ዛሬም ድረስ በዞኑ የሰላምና አንድነት ጠንቅ ሆኖ ቆይቷል:: ህወሓት ኢህአዴግ ስልጤን ከጉራጌ ለመነጠል የተጠቀመበት ሀይል አሁንም በቡታጀራና በዙርያው ያለውን ፖለቲካ እያመሱት ይገኛል:: በምሥራቅ ጉራጌ አከባቢ የሚያተራምሰው የሴራ ፖለቲካ ስልጤን ከጉራጌ የነጠለበት ያረጀ ስልት እንደሆነ ግልፅ ነው:: ለራሱ ከስልጣንም ከልማትም ተገፍቶ ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀው ጉራጌ ምእራብ ጉራጌ ምሥራቁን በድሏል የሚል የህዝብ ብሶት እንዲሰፋና ጉራጌ እርስ በራሱ እንዳይግባባና እንዲጠራጠር እያደረገው ይገኛል:: ክሶቹ ውሀ የምይቋጥሩ እንደሆነ ማሳያዎቹ እጅግ ብዙ ስለሆኑ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ:: አሁን ማሳየት የተፈለገው በጉራጌ ላይ የተዘረጋውን ሴራ ማጋለጥ ላይ ብቻ ነው ማተኩረው::

➡️ 4.2) ጉራጌን ለዘመናት በአንድነት ተዋደውና ተጋብተው የሚኖሩትን በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የማረቆንና የቀቤናን ብሔረሰቦች በመጠቀም የዞኑን ሰላም ማወክና አካባቢው ውስጥ የለየለት ህገ ውጥነት እንዲነግስ ማድረግ ነው:: ይህንን ሴራ የሚጠነስሱትና የሚተገብሩት ደግሞ ምሥራቅ ጉራጌን ከሚያምሱት የተለዩ ሀይሎች ናቸው::

የመጀመሪያው ለዘመናት በጋብቻና ጉርብትና የተጠናከረ መስተጋብር የነበራቸው የመስቃን ጉራጌና የማረቆ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የሚቆምረው ኃይል ነው :: ከሌላ ዞን በሚሰጣቸው አጀንዳ በእነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች ላለፉት አራት አመታት ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቷል፤ ከፍተኛ ንብረትም ወድሟል:: የመስቃንና ማረቆን ደም ያፋሰሱ ተላላኪዎች እና በስልጣን ያኮረፉ ቡድኖች ዛሬ ደግሞ ምዕራብ ምስራቅ ለተባለ ጉራጌን የመከፋፈል አጀንዳ ግንባር እንዲፈጥሩ ተደርገዋል፡፡ ከወያኔ ዘመን ሴራ የተረፈውን የሶዶ ክስታኔ ሕዝብ እየሸጡ ያሉ ውስን ባለስልጣናትና ባለሀብቶችም የዚህ ሴራ አካል ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ሴራ መሃል በጉራጌነቱ የማይደራደረው ሰፊው ሕዝብ ባይተዋር የተደረገበት ሁኔታ ይታያል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በወልቂጤ ዙርያ ያለው የቀቤና ወንድም ህዝብን ከጉራጌ ጋር የማቃቃር ሴራ ነው:: ይህ ሴራ በእድሜ ትንሽ ቀደም ያለ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አጀንዳ እየቀረፀ የሚሰጠው ማረቆንና መስቃን ጉራጌ ላይ የሚሰራው ሴረኛ ሀይል ነው::

የቀቤና ማኅበረሰብ በጉራጌ ዞን ላይ የቆየ የልዩ ወረዳ ጥያቄ እንዳለው ይታወቃል:: ይህንንም ለማስተናገድ የጉራጌ ዞን ብዙ ርቀት የተጓዘ መሆኑ ብዙ ማሳያዎች አሉ:: ለምሳሌ የቀቤና ማኅበረሰብ የልዩ ወረዳ ጥያቄውን ለማስተናገድ ያሉት የቀበሌ ብዛት በቂ አልነበሩም:: እንደሚታወቀው የቀቤና ማኅበረሰብ በብዛት የሚኖርባቸው አምስት ቀበሌዎች ብቻ ናቸው:: አምስት ቀበሌዎች ብቻቸውን በልዩ ወረዳ ማዋቀር ለአስተዳደርም ሆነ ለልማት ተደራሽነት አመቺ ባለመሆኑ አጎራባች ከሆኑ ሶስት የጉራጌ ወረዳዎች የተውጣጡ ወደ 20 የሚጠጉ ቀበሌዎች ተጨምረው የጉራጌ-ቀቤና ወረዳ እንዲመሰረት ተስማምተው ተመሰረተ:: አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ 70% የሚሆነው ህዝብ ጉራጌ ሆኖ ሳለ የወዳው ስም ቀቤና ወረዳ ነው፤ በወረዳው ካለው ከ80 በላይ የኃላፊነት ቦታዎች አንድም የጉራጌ ኃላፊ የለም:: በወረዳው ውስጥ የሚገኘው 70% ጉራጌ ልጆቹን በቀቤንኛ እንዲማር ተገዷል:: ቋንቋ የማንነት መለያ ከሆነ ጉራጌ የቀቤና ወንድሙን ጥያቄ ለመመለስ ማንነቱንም ጭምር ሰውቷል:: ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ዛሬም በሌሎች የሚሰጡትን አሉታዊ አጀንዳ ተቀብሎ የቀቤና ማኅበረሰብ ከጉራጌ ጋር እንዳይኖር ማህበረሰቡን በማይወክሉ ተከፋይ አክቲቪስቶች በወልቂጤ ዙርያ የፀጥታ ስርት ደቅኗል:: ጉራጌም በብልሀትና በጥበብ ሴራዎቹን አንድ በአንድ እያከሸፈ ይገኛል:፡

⏩ ሴራ 5፡ የጉራጌን ልማትና በአኮኖሚ እንዲሁም እሴት የማዳከም ሴራ

የጉራጌ ማኅበረሰብ በአፍሪካ ደረጃ የሚጠራ ጠንካራ የራስ አገዝ ልማት የነበረው ቢሆንም በአገዛዙ እንዲከስም ተደረገ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ አመራሩ ከፍ ብሎ በተገለጹት አራት ሴራዎች ላይ ተጠምዶ የሕዝቡን መሰረታዊ አገልግሎቶች ማቅረብ ተስኖት ለከፋ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተጋለጠ፡፡
በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚገኘው የንግዱ ማኅበረሰብ በአድሎአዊ አሰራር ከንግድ ዓለም ውስጥ እንዲወጣ ከፍተኛ ጫና ተደረገበት፡፡ለአብነት ጉራጌን ከመርካቶ ጠራርጎ ማስወጣትና ጉራጌን ግልገል ነፍጠኛ ብሎ መፈረጁ ይታወቃል:: በጥቅሉም በፖሊሲና በአሰራር አሻጥር የኢኮኖሚ የበላይነቱ የመንጠቅ ሥራ በመንግስት መዋቅር በገሃድ ተሰራ፡፡

⏩ መደምደሚያ

ጉራጌ ከላይ የተዘረዘሩትን የሴራ ፖለቲካን አክሽፎ ወደነበረበት አንድነት እና ጥንካሬው መመለስ ካልቻለ ወደፊት ማንነቱና ህልውናው እንደሚጠፋ ግልፅ ነው:: አንድነቱንና ጥንካሬውን እንዲሆም በኢትዮጵያ ላይ የሚገባውን ስልጣንና የባለቤትነት ድርሻ የማግኘት ደረጃ የሚደርሰው በመንግስት ተቀነባብሮ የመጣውን ክላስተር እምቢ ብሎ የራሱን ክልል ሲመሰርት ብቻ ነው:: ጉራጌ ክልል የሚጠይቅበት በርካታ የተደራጁ ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ ላለፉ 30 አመታት ሲሰራበት የነበረውን ፀረ ጉራጌ አሻጥር የሚያስቆምበት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑም ጭምር ነው:: ከመንግስት ጋር የገባንበትን እልህ አስጨራሽ ህዝባዊ ትግልን ወደ ጎን በመተው ለመንግስት እያጎበደዱ ያሉ አመራሮችም ህዝባቸውን የማይመጥን ጉራጌን በሀገር ደረጃ የሚያሳንስ አካሄድ ስለሆነ ከድርጊታቸው በአስቸኳይ ሊታቀቡ ይገባል::

በጉራጌ ላይ የተቀናበረ ሴራን ለማክሸፍ የጉራጌ ክልል መሆን አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው!!!

Please wait, video is loading...

Re: ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር:- በጉራጌ ላይ የተቀናበረ ሴራን ለማክሸፍ የጉራጌ ክልል መሆን አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው!

Posted: 05 Mar 2023, 20:21
by Horus
ጉራጌ በአዲስ አበባ ብቻ 1.5 ሚሎዮን ሕዝብ ሲኖረ በጉራጌ አገር ቤት፣ በመላ ኢትዮጵያ፣ ቅርብ ምሳራቅ፣ ሰሜን አሚሪካ ፣ አውሮፓና አፍሪካ ተርቶ ያለ ሕዝቡ ክ6 ሚሊዮን እስከ 8 ሚሊዮን እንደ ሚደረስ ይገመታል ። ታሪካዊ ድምበሮቹ በምዕራብ የግቤ ወንዝ፣ በሰሜን የአዋሽ ወንዝ፣ በምስራቅ ዝዋይ ሃይቅና በደቡብ ሃዲያና ከምባታ፣ የም ናቸው !