7h
በኡጋንዳ የሚገኘው ሴሬሬ ከተማ ፖሊስ ከአንድ መቶ በላይ የቤተክርስቲያን አባላት ወደኢትዮጵያ ገብተው በመጥፋታቸው ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ኦስካር አጌካ ትናት በሰጡት መግለጫ እንዳስረዱት እነዚህ ሰዎች ወንጌልን ለመስበክ በሚል ምክንያት ወደኢትዮጵያ የሄዱት ‹‹ክሪስት ዲሲፕሊንስ ቸርች›› በተሰኘው የሀይማኖት ተቋም አማካኝነት ነው፡፡ በሁለት ፓስተሮች የተመሰረተውና የሚመራው ይህ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮቹን ‹‹እግዚአብሄር ወደኢትዮጵያ ሄዳችሁ ወንጌልን እንድታስፋፉ አዟል›› የሚል ስብከት መስጠቱን የገለፁት ቃል አቀባዩ ይህንን ስብከት ተከትሎ ካለፈው የፈረንጆች ወር ማለትም ፌብሩዋሪ አንስቶ ከመቶ በላይ ኡጋንዳዊያን የቤተክርስቲያኑ አማኞች ወደኢትዮጵያ መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ሲናገሩ ‹‹በዚህ ጉዞ ላይ የተሳተፉት ሰዎች እያንዳንዳቸው ለጉዞ ሰነድ በሚል ሁለት ሚሊዮን ሽልንግ እንዲከፍሉ ተደርገዋል፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብ ከፍለው አንድ ከረጢት ዱቄት ብቻ ይዘው ወደኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡›› ካሉ በኋላ ይህንን ገንዘብ ለማሟላት አንዳንዶቹ ከብቶቻቸውን ወይንም ቤታቸውንና የቤት እቃዎቻቸውን መሸጣቸውን ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደኢትዮጵያ ከሄዱ በኋላ ድምፃቸው እንደጠፋና የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ የቤተክርስቲያኑ ፓስተሮችም መሰወራቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በፍለጋው ለመተባበር ፈቃደኛ ስላልሆነ ምናልባት በኦነግ ሸኔ ታግተው ሊሆን ይችላል ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል ::አሁን በፓስተሮቹ ላይ በይፋ ክስ እንደተመሰረተና በፖሊስ እየታደኑ እንደሚገኙና ወደኢትዮጵያ የሄዱትንም ሰዎች ለመፈለግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ መናገራቸውን ኢንዲፔንደንት ኡጋንዳ ዛሬ ዘግቧል፡፡
