«ቢያልፍልን» ብለዉ በአረብ ሃገራት...
To listen: https://www.dw.com/am/%E1%89%A2%E1%8B%A ... -11646-xml
ወጣቷ ሊሊ ከአምስት ዓመታት በፊት የትውልድ ቀዬዋ አቢ አዲን ለቃ ስትወጣ ብዙ ተስፋ ነበራት ። ለራሷም ተርፋ ቤተሰቦቿን ማሳረፍ ደግሞ ህልሟ ነበር ። አሁን ነገር ዓለሙ ተመሰቃቅሎባታል። ያለፉትን ሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ ያሳለፉት ቤተሰቦቿ በትክክል የእርሷን ድጋፍ የሚሹበት ጊዜ መጥቷል ።
ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን «ቢያልፍልን» ብለዉ ባህር አቋርጠው ተሰደዉ በደረሱበት ሐገር በአሰሪዎቻቸው ብዝብዛ እየተፈጸመባቸው የሚገኙ ወጣት እንስት ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ይዘን ቀርበናል። ታምራት ዲንሳ ነኝ አብራችሁን ቆዩ ።
የዛሬ ባለታሪኮቻችን ሊሊ እና መቅደስ ይባላሉ ። ለደላላ ከፍለው ባህር አቋርጠው ሊባኖስ በ2010 ዓ/ም ነበር። በሊባኖስ ቆይታቸው አንዱ አሰሪ ቤት ከሚደርስባቸው በደል ሽሽት ወደ ሌላ እያሉ ለዓመታት ብዙ ታግለዋል። ሊባኖስ በኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመመታትዋ መጀመሪያኑ በቅጡ መሠረት ያልያጠዉን ኑሯቸዉን አስከፊ አደረገባቸው ። ወጣቶቹ የነበራቸው ምርጫ ሊባኖስን ለቀው ወደ ዱባይ ዳግም መሰደድ ነበር፤ አደረጉት ።
ነገር ግን በንግድ እና የስራ አማራጮች ብዙ የሚወራላት ዱባይ ነገሮችን አልጋ በአልጋ አላደረገችላቸውም። የዛሬ ባለታሪኮቻችን የሆኑት ሁለቱ ወጣቶች የደረሰባቸውን ስላካፈሉን እንጂ በዚህ የበደል ታሪክ ውስጥ ሌሎች አራት ኢትዮጵያውያን ወጣት እንስቶችም ተካፋይ ናቸው።
ሊሊ በትግራይ ክልል አቢ አዲ ነው ተወልዳ ያደገችው ። በድህነት ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦቿን ለመደጎም ብላም ለራሷ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነበር ከሀገር የወጣችው ።አምስት ዓመት የገፋችዉን ህይወት ከውሃ ወቀጣ ለይታ አታየውም ። ያሰበችውን አላሳካላትም ። ቀን ቀንን እየተካ ፣ ወራትም ለዓመታት እያሻገሩ አሁን የመከራ ሕይወትን በምትገፋበት እና ዱባይ ውስጥ በሚገኝ የጽዳት ኩባንያ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት ተቀጠረች። ....