ሰበር ዜና
ዶ/ር ደብረፅዮን በምክትል ጠ/ሚነት ሊሾሙ ነው!
የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የኢትዮዽያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ሹመት ሊሰጣቸው መሆኑን የተራራ ኔትዎርክ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በህወሓትና የፌደራል መንግስት መካከል በቅርቡ የተደረገውን ስምምነት መሰረት ባደረገ መልኩ አዲስ የካቢኔ ድልድል እንደሚኖር የጠቆሙት ምንጮቻችን በርካታ የህወሃት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ባለስልጣናትን ወደፌደራል ስልጣኖችና በከፍተኛ ማዕረግ ወደ መከላከያ መልሶ ለማካተት ቅድመ ዝግጅት እየተገባደደ መሆኑን ለተራራ ኔትዎርክ ገልፀዋል፡፡
ከነዚህ ባለስልጣናትም መካከል ግንባር ቀደምትነቱን የሚወስደው ዜና የዶ/ር ደብረፅዮን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት መታጨት ሲሆን በመቀጠል ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመሾም እንደታቀደ ለማወቅ ተችሏል:: አቶ ጌታቸው ረዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካልሆኑ ደግሞ የጠ/ሚኒስትር አቢይ የውጭ ጉዳይና ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ሊሾሙ እንደሚችሉና በአሁን ወቅት የውጭ ጉዳይና ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሊሾሙ እንደሚችሉ ምንጮቻችን ምልከታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የምክትል ጠ/ሚነቱንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ደርበው የያዙት አቶ ደመቀ መኮንን በአዲሱ የስልጣን ሽግግር ኒውዮርክ በሚገኘው የተባባሩት መንግስታት ፅሀፈት ቤት በሙሉ አምባሳደርነት ለመሾም እንደታቀደና ይህንንም ለማመቻችት አቶ ደመቀ የአምባሳደርነት ስልጠና እየወሰዱ እንደሰነበቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡