================
የብሄር ግጭት ባጋጠመ ቁጥር "የብሄር" ፌደራሊዝሙን ማውገዝ ተገቢ አይደለም፤ የችግሩ መንስኤ ፌደራሊዝሙ አይደለምና።
(1) ፌደራሊዝም አንድ የአስተዳደር መሳርያ (instrument) እንጂ በራሱ የችግር መንስኤ ወይም መፍትሔ ሊሆን አይችልም።
(2) የኢትዮጵያ ችግር የብሄር ፖለቲካ ነው ከተባለ የብሄር ፌደራሊዝም ስሕተት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ብሄሮች እርስበርሳቸው ካልተግባቡ ለየብቻቸው የየራሳቸው አስተዳደር እንዲኖራቸው (ራስ ገዝ እንዲሆኑ) ታደርጋለህ እንጂ አትቀላቅላቸውም። ለየብቻ እየተዳደሩ ያልተስማሙ ተቀላቅለው እንዴት ይስማማሉ? በየትኛው ቋንቋስ ይግባባሉ? በትንሽዬ መሬት እየተጣሉ እንዴት እንደ አዲስ እንዲካለሉ ይፈቅዳሉ?
(3) ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ፖለቲካ ከብሄር ፌደራሊዝም በፊት ጀምሮም ነበር። ህወሓቶች የብሄር ጥያቄ አንግበው ጫካ የገቡት ከብሄር ፌደራሊዝሙ በፊት ነበር። ኦነግ የኦሮሞ ብሄር ነፃ ለማውጣት ትግል የጀመረው ከብሄር ፌደራሊዝሙ በፊት ነው። ከብሄር ፌደራሊዝም በፊት ብዙ የብሄር ችግሮች ነበሩ። ስለዚህ ፌደራሊዝሙ የብሄር ፖለቲካ መነሻ ተደርጎ መወሰዱ ልክ አይደለም።
(4) የብሄር ችግር ባለበት ሀገር የብሄር ፖለቲካ ይኖራል፤ ምክንያቱም የፖለቲካ መነሻ ችግር ነው። ስለዚህ የብሄር ፖለቲካን ለማጥፋት ከመጣር ይልቅ የብሄርን ችግር መፍታት ይቀድማል። የብሄርን ችግር ሳትፈታ የብሄር ፖለቲካን ለማጥቃት በጣርክ ቁጥር የበለጠ ስር እየሰደደና እየተስፋፋ ይሄዳል። እየሆነ ያለው ይህንን ነው፤ ችግሩን ሳትፈታ ፖለቲካውን ማውገዝ ጉዳዩን ያባብሰዋል። የብሄር ፖለቲካ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀውስ Cause ሳይሆን Effect ነው።
(5) የብሄር ፖለቲካ በራሱ ችግር አይደለም፤ የብሄር ጥያቄ (ካለ) ማንሳት ተገቢ ነውና። ችግር የሚሆነው ብሄር ለፖለቲካ ዓላማ ሲውል (Ethnic Politicization) ነው። ይሄም ችግር አይደለም። ችግሩ የብሄር ጥያቄ መኖሩ ነው። የብሄር ጥያቄ መኖሩ ችግር አይደለም። ችግሩ የብሄር ጥያቄ መፈጠሩ ነው።
የብሄር ጥያቄ (የብሄር ችግር) መፈጠሩም በራሱ ችግር አይደለም። ችግሩ ለብሄር ችግር (ጥያቄ) መፈጠር መንስኤዎች መኖራቸው ነው። የብሄር ችግር መንስኤ አድልዎ ነው።
አድልዎ ሲኖር እኩልነት አይኖርም፣ ነፃነት እና ፍትሕ አይኖርም። ሁሉም ብሄር ያለ ምንም አድልዎ በእኩልነት የሚገለገልበት የፖለቲካ ስርዓት ሲገነባ የብሄር ጥያቄ አይኖርም። የብሄር ጥያቄ ከሌለ የብሄር ፖለቲካ አይኖርም። የብሄር ፖለቲካ ከሌለ የብሄር ግጭት አይኖርም። የብሄር ግጭት ከሌለ ያለአግባብ ሞት፣ መፈናቀል፣ ንብረት መውደም ወዘተ አይኖርም።
ሰው በማንነቱ ምክንያት አድልዎ ካልተፈፀመበት ስለ ብሄሩ አይጨነቅም። አንድ ዜጋ በብሄሩ ምክንያት አለአግባብ ካልተጠቀመ ወይም ካልተጠቃ ስለ ብሄሩ ለምን ሊጨነቅ ይችላል? እንደ ዜጋ ያለምንም አድልዎ በእኩልነት ከተገለገለ ብሄሩ በተለየ ሁኔታ የሚያስታውስበት ዕድል አይኖርም፤ በብሄሩም አያፍርም አይሸማቀቅም!
መፍትሔ
የብሄር ፖለቲካን ጠልተን የብሄር ፌደራሊዝሙን ከማውገዝ ይልቅ ዜጎች በብሄራቸው ምክንያት አድልዎ ሳይደርስባቸው በነፃነትና በእኩልነት የሚኖሩበት ስርዓት መገንባቱ ላይ ልንሰራ ይገባል። ለዚህም ነፃና ገለልተኛ (በብሄር ምክንያት የማያዳሉ) እንዲሁም ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት ሊገነቡ ይገባል።
መደምደምያ
አሁን የብሄር ግጭቶች እየተስተዋሉ ያሉ በብሄር ፌደራሊዝም ስለተካለልን ሳይሆን ያለ አድልዎ በእኩል ዓይን እያየ የሚያገለግለን መንግስታዊ ስርዓትና መዋቅር ስለሌለን ነው።
ፈየችግሩ መንስኤ ትተን ውጤቱ ላይ ብንንጠለጠል መፍትሔ አናመጣም!
It is so!!!
Please wait, video is loading...