በቆቦ ይገኙ የነበሩ 60ሺ የትግራይ ተፈናቃዮች ከትህነግ ጋር በመተባበር የቆቦን ሕዝብ እያስጠቁ ነው እየተባለ የሚለቀቀው መረጃ ውሸት ነው - ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ
Posted: 29 Aug 2022, 19:53
ራያ-ቆቦና አካባቢውን በተመለከተ ሁለት ነገሮችን ግልጽ ስለማድረግ!
1. እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት የቆቦ ከተማና አካባቢው እስከ አሁኗ ስአት ድረስ በጠላት ቁጥጥር ስር ነው የሚገኘው። አንዳንድ ሀላፊነት የጎደላቸው ወገኖችና የማህበራዊ ሚዲያ ሰዎች የወገን ጦር ቆቦ ከተማ ገብቷል በማለት የሚሰጡት መረጃ ትክክል አይደለም። ይህም ሆኖ የወገን ጥምር ጦር በቆቦና አካባቢው እየወሰደው ባለው የተቀናጀ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ቆቦ ከተማና አካባቢው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነጻ ሊወጣ እንደሚችል ይታመናል።
2. "በቆቦ ከተማ ይገኙ የነበሩ 60,000 የትግራይ ተፈናቃዮች ከትህነግ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር የቆቦ ከተማን ሕዝብ እያስጠቁ ነው" እየተባለ የሚለቀቀው መረጃም ውሸት ነው። ሁኔታቸው ተጣርቶ ወደ ሐይቅ (ጃሪ) መጠለያ ጣቢያ እስኪላኩ ድረስ ቆቦ ከተማ ውስጥ የሚቆዩት የትግራይ ተፈናቃዮች ቁጥር በአጠቃላይ ከአንድ ሽህ በታች እንደነበረ ይታወቃል።
ከእነዚህ ውስጥ በቡድንና በግለሰብ ደረጃ ሆነው ጥቆማ እየሰጡ በግለሰቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ እያደረጉ የሚገኙ እንዳሉ መረጃ ደርሶኛል። ስለሆነም በእነዚህና በሌሎችም አስጠቂ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ጥብቅ ክትትል አድርጎ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የአካባቢው ሕዝብ ሀላፊነት ነው።
ከዚህ ውጭ የትግራይ ተፈናቃዮች የሚገኙት ሐይቅ ከተማ አጠገብ በሚገኘው ጃሪ መጠለያ ጣቢያ ሲሆን ቁጥራቸውም ከላይ የተባለውን ያህል አይሆንም። ወደዚህ መጠለያ ጣቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ራዮችም (የራያ-አላማጣ እና የራያ-አዘቦ ተወላጆች) በስህተት ከትግራይ ተወላጆች ጋር አብረው እንዲገቡ በመደረጉ ወገኖቻቸው ወደሚገኙበት ድሌ ሮቃ (ጃራ) መጠለያ ጣቢያ መግባት ይሻሉና ይህም እውነታ ሊታወቅና ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል።
ይኸ መጠለያ ጣቢያ ደግሞ ሐይቅ አጠገብ የሚገኝ በመሆኑ ከቆቦ ከተማ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ያለው። እናም መረጃዎች ትንሽ እውነትን በመያዝ በተጋነነ መልኩ ቢቀርቡ እኮ ምንም አልነበረም፣ እንዲሁ ከሜዳ ተነስቶ መቀደድ ግን የጤና አይደለም። ራስን ትዝብት ውስጥ ከቶ ተዓማኒነትንም ያሳጣልና ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል።
Please wait, video is loading...