እኔ ለብዙ አመታት ብዙ ግዜ እንዳነሳሁት በጎሳ የተለያዩት ኢትዮጵያዊያን አንድ የኢትዮጵያ ካልቸር መሰረት ናቸው የሚባሉትን እሴቶች (ቫልዩስ) ለይተን በውል ማወቅና ማዳበር አለብን ። ከዚህ ቀደም ያልኩትን ልድገመው።
አንድ፣
የካልቸር አንዱ መሰረት እምነት ነው ። ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ሃይማኖቶች አሏቸው፤ ነገር ግን ሁሉም በአንድ ፈጣሪ ያምናሉ። ስለዚህ እምነት በሚመለከት ሁሉም ጎሳዎችን አንድ የሚያደርጋቸው በአንድ ፈጣሪ ማመናቸው ነው። ይህ የመጀምሪያው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ እሴትና የኢትዮጵያ ካልቸር መሰረት ነው።
ሁለት፣
ሌላው የጋራ ካልቸር መሰረት ወንድማማችነት ነው። በአንድ ፈጣሪ የሚያምኑ ሁሉ ሰውን የፈጠረ አንድ ፈጣሪ ነው ብለው ያምናሉ። ስለሆነም ከአንድ ፈጣሪ፣ ከአንድ አባት የተፈጠሩ ሁሉ ወንድማማቾች ናቸው ። ስለሆነም ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በዘጠና ጎሳ ቢከፋፈሉም የአንድ ፈጣሪ አባት ልጆች ወንድማማቾች ናቸው። ስለሆነም ወንድማማችነት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ እሴትና የኢትዮጵያ ካልቸር መሰረት ነው።
ሶስት፣
ሌላው የጋራ ካልቸር መሰረት እኩልነት ነው። ጎሳዎች ወይም ስብስቦች በቁጥር፣ በስፋት፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በሃብት፣ በስልጣኔ ይለያያሉ። ነገር ግን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጎሳው ምንም ይሁን ምን በአንድ ፈጣሪ የተፈጠረ ስለሆነ ግለሰቦች ሁሉ እኩል ናቸው፤ ግለሰቦች ሁሉ እኩል ነጻነት እና እኩል መብት አላቸው ። ይህን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ እኩልነትን የሚበልጥ ወይም የሚልቅ ሌላ ሃይል የለም፤ ጎሳዊም ሆነ ህጋዊ። ስለሆነም የግለሰቦች እኩልነት ሶስተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ እሴትና የኢትዮጵያ ካልቸር መሰረት ነው።
አራት፣
ሌላው የጋራ ካልቸር መሰረት የስራ ክቡርነት ነው። የሰው ልጅ ከተፈጥሮው ባሻገር እራሱን በስራው የሚለውጥ ፍጡር ነው። ሰው ሰራሽ የሚባለው አለምን ሁሉ የሰራ ፣ የፈጠረ ፣ ያሻሻለ፣ ያበላሸ ሰው እራሱ በስራው ነው ። ስራ የካልቸርና የስልጣኔ ምክያት ነው ። ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ጎሳው ምንም ይሁን ምን የመጨረሻ ምንነትና ማንነቱ የሚወሰነው፣ የሚገለጸው በስራው ነው ። በስራ ክቡርነት የማያምን ክቡር ሰው ሊኖር አይችልም። ስለሆነም የስራ ክቡርነት አራተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ እሴትና የኢትዮጵያ ካልቸር ነው ።
እነዚህን አራት ግዙፍ የካልቸር መሰረቶችን ሰብስቦ የያዘው ለዘመናት የሰው ልጅ የሚፈላሰፍበት አንድ ጽንሰ ነገር በፍጥረት ሁሉ መልካምነት፣ በአለም ሁሉ ደህንነት፣ በተፈጥሮ ሁሉ ጤነንትና ሙሉነት ማመንና መተግበር ነው ። እሱም የፍጥረት ሁሉ ኬይርነት ወይም The Ethics of Well-Being of All ይባላል። ባሁን ወቅት የሰው ልጅ ንቃተ ህሳቤና ስነምግባር ደርሶበታል ከሚባለው የፍትሃ ንደፈ ሃሳብ የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ነው።
በዚህ የሰነምግባር እምነትና ፍልስፍና መሰረት እንሰሶች ልክ እንደ ሰው ደስታና ስቃይ ይሰማቸዋል፣ እጸዋቶች ልክ እንደ እንሰሳ እንክብካቤ ይፈልጋሉ፤ አየር፣ አፈር፣ ዉሃ ፣ ፍጥረት ሁሉ ደህንነት ይፈልጋል የሚለው ልሂቅ ህሳቤና ካልቸር ነው ። ይህን ስነምግባር ነው ኬይርነት የምንለው!! ኬይርነት ለኢትዮጵያ !!!