“ከፈተና ወደ ፍተላ”
-------
ይህን እጅግ ልብ አንጠልጣያ የሆነ፤ አሁናዊ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ፣ የብዙ ድብቅ ምስጢሮች ፍቺ የሆነውን የሃገራችን ፖለቲካ በደንብ የሚያመላክት ነው፡፡
ፖለቲከኛ ፣ጋዜጠኛ፣አክቲቪሰት ፣ተንታኝ ፣………. ወዘተ.. እንደ አንድ ማስረጃ እና መረጃ ሊጠቅም የሚችል ነው ፡፡ ለብዙዎች ይዳረስ ዘንድ እዚህም “በፊስብኩ” የቀረበ ነው !! እንዳትሰለች/ቺ እስከ መጨረሻው ይነበብ ፦
*
*
-------
“ከፈተና ወደ ፍተላ”
በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
የአንዳንድ አገራት ቤተ-መንግሥት በኪነት ሰዎች ከተያዘ በኋላ፣ የሕዝብ አስተዳደር እና የቴያትር ልዩነት እየተምታታ ነው፡፡ ዩክሬንን ከሰናኦር ግንብ ያላተመው ቮሎድሚር ዘለንስኬ የተሳካለት ኮሜዲያን ነበር፡፡ ድቡን እየነካካ ለማዝናናት መሞከሩ ግን፣ ከማሳቅ ይለቅ መከራ አምጥቶበታል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አህመድም፣ “ሦስት ማእዘን” የተሰኘ ፊልም ጽፈዋል፡፡ የድርሰቱ ዘውግ ትራጄዲ በመሆኑ፣ የአገዛዝ ዘመናቸውም፡- ሰላም የራቀው፣ ዜጎች የሚፈናቀሉበት፣ የሚጨፈጨፉበት፣ አሰቀቂ አገዳደል እንደ ትርኢት የሚታይበት፣ የክልል ፕሬዚዳንት በጥይት የደበደቡ ወንጀለኞች “በሌሉበት…” ተብሎ የሚፈረድበት፣ ዓለም በመአት ዓይኑ የሚከታተለው ፕሮጀክት ኃላፊ እንደ ሲሲሊ በዐደባባይ የሚገደልበት፣ ቢሊዮኖች የፈሰሰባቸው ኢንቨስትመንቶች በአንድ ምሽት የሚነዱበት… ሆኗል፡፡
‘ዐዲስ አቋቋም ነው’ የሚሉት ፓርቲም ገንዘብ አወጣጡ፣ የአሜሪካኑን “ሪፐብሊካን ፓርቲ” ያስንቃል፡፡ የድግስ ጋጋታው አያጣል ነው፡፡ ለአክቲቪስቱ የሚረጨው ደግሞ፣ በሴፍቲኔት የሚተዳደር ሕዝብ “የሚመራ” አይመስልም፡፡ ከነጋዴዎች ነጠቃ-መሰል መዋጮ መሰብሰቡንም ይዘነጋል፡፡ ከቁማር የተረፈውን የፖለቲካ ሥራንም፣ ችግኝ ወደ መንከባከብና ወደ ቢሮ እድሳት አውርዶታል፡፡
በዚህ ዐውድ፣ ሰሞነኛውን ጉባኤ እና የኦዴፓን ጠቅላይነት እንመለከታለን፡፡
ከጉባኤው ጀርባ
ብልፅግና ከጉባኤው በፊት እንደ “አምታታው በከተማ” የቴያትር ቡድን፣ ናዝሪት ከትሞ ሪሄርስ ቢያደርግም፤ ገዝፈው በወጡ ስህተቶቹ አማተሪሽነቱን አስረግጦ አልፏል፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ ጉባኤው በድጋሚ እንዲካሄድ ይወስናል ወይስ ያፀድቀዋል? የሚለውን ጥያቄ እያሰላሰልን፣ ዋንኛዎቹን ግድፈቶች እንጥቀስ፡፡
፩
የፓርቲው ሕገ-ደንብ “የኦዲት ኮሚሽን አባላት በጉባኤተኛው በቀጥታ ይመረጣሉ፤” ይላል። ይህ መርህ ሁሉም የፖለቲካ ማኀበሮች የሚገዙበት ነው። ብልፅግና እዚህ ጋ የሠራው ጥፋት ለክፍለ-ዘመኑ ቅሌት አጋልጦታል፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈልጉ የአመራር አባል ለ“ፍትሕ መጽሔት” የነገሩትን ምስክር እናድርገው፡-
“ባለቀ ሰዓት ዶ/ር ዐቢይ ከፓርቲውና ከምርጫ ቦርድ ሕግ በመቃረን፣ የክልል ኘሬዚዳንቶችን ጠርቶ ‘ለኦዲት ኮሚሽን የሚሆን ታማኝ፣ ገመና የማያጋልጥ አንድ አንድ ሰው ስጡኝ’ አላቸው። እነሱም ‘ፍፁም ታዛዥ ነው’ ያሉትን ለይተው ሲያቀርቡ፤ ‘በሉ ከአዳራሹ ውጪ ተነጋግራችሁ ሊቀ-መንበርና ም/ሊቀ-መንበር መረጣችሁ አሳውቁኝ’ ስላላቸው፣ በተባሉት መሰረት ተመራርጠው መጡ። ከዚያም፣ ስማቸው ለጉባኤተኛው ተነገረ።”
መቼም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወርቁ አይተነው ቢሆን ኖሮ፣ ድርጊቱን ወቸው ጉድ ብለን ባለፍነው ነበር!
፪
ሌላው፣ እጅ-ከፉ የተያዘው አጭቤ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ነው፡፡ ኦዴፓ ‘በኮሚቴው የሚወከሉ አመራሮች በሕዝብ ብዛት ልክ ይከፋፈላል’ የሚል ዐዲስ ደንብ አጸድቆ፣ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል፡፡ የበፊቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ 316 አባላት ሲኖሩት፤ ደቡብ፣ አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ሶማሌ እኩል በ45 ሰዎች ተወክለው ነበር፡፡ በወቅቱ፣ ጠቅላዩ የሶማሌ ድርሻ ከአጋራ ፓርቲዎች የተለየ እንዳይሆን ቢፈልጉም፤ እነ ሙስጠፌ ‘ብልፅግናችሁ በአፍንጫችን ይወጣ እንጂ፤ አንቀላቀልም!’ ብለው በማደማቸው፣ ተስማምተው ነበር፡፡ አሁን ጊዜው ተቀይሯል፤ ከቅያሪውም ጋ ዐማራም ሶማሌም… የተሰጠውን ይቀበል ዘንድ ገብሯል፡፡
“ውህድ ነኝ” የምትለዋ ጭዌም፣ የክት እርድና መሆኗ ተገልጧል፡፡
በዐዲሱ መተዳደሪያ ደንብ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ከ316 ወደ 225 ዝቅ እንዲል ቢደረግም፤ የኦዴፓ ኮታ ወደ 60 ከማደግ አልተገታም፡፡ አዴፓ በነበረው 45 ሲረግጥ፤ የሶማሌ ግማሹ ተቀንሶ በ23 ተገድቧል፡፡ በርግጥ፣ አጀንዳችን ይህ አይደለም፡፡ ጉባኤተኛው ከሚጠቁመው ሰው ብዛት በቀር፤ ለየክልሎቹ ምን ያህል ኮታ እንደተመደበ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ካለመነገሩ ነውና፡፡ ለዚህም ነው፣ ቀመሩን ለብቻቸው የሠሩት ዶ/ር ዐቢይ ‘ኮታውን እኔ ስለማውቀው፣ እናንተ ዝምብላችሁ ምረጡ’ ሲሉ በቀጥታ በተሰራጨው ፕሮግራም ያዳመጥከው፡፡ በውጤቱም ዐማራ 50 አቅርቦ 12ቱ ሲወድቁ፣ 38ቱ አለፉ፡፡ አፋር 16 ጠቁሞ፣ 16ቱም ተመረጡ፡፡ ኦሮሚያ 60 አቅርቦ፣ 60ውም ማለፋቸው ያልተጠበቀ አይደለም፡፡ ብቻ የሁሉም በዚህ መልክ ተካሄዶ ማዕከላዊ ኮሚቴውን የተቀላቀሉ አባላት ስም ተገልጾ፤ ሥራ-አስፈጻሚውን ለመምረጥ ወደሌላ አዳራሽ ሲያቀኑ፤ በቀቢፀ-ተስፋ የቀረውም፣ ትካዜ በተጫነው ሀዘነተኛ እርምጃ አዘገመ። ይኼኔም፣ አንድ ስህተት እንደተፈጠረ ታወቀ። አፋር ኮታው 12 ቢሆንም፤ ያቀረባቸው 16ቱም ተመርጠዋል። ደቡብ 2፣ ሶማሌም አንድ እላፊ ወስደዋል፡፡ በግልባጩ ዐማራ ከተመደበለት 45፣ 7ቱ ወድቀዋል፡፡
እድሜ ለዶ/ር ዐቢይ¡ ጉባኤው የመረጣቸውን አራት አፋሮች፣ ሁለት ደቡብ እና አንድ ሶማሌን በካልቾ አሰናብተው ‘ከዐማራ ጎደለ’ ያሉትን አሟልተዋልና።
ይህም ሆኖ፣ አብዛኛው ተሰብሳቢ ከአዳራሹ ስለወጣ፣ በትዕዛዝ ያለፉትን 7 ሰዎች ፍለጋው በየኮሪደሩ ተጧጣፈ። ስልክ እንዳይደወልላቸው፣ ይዞ መግባት በመከልከሉ እጃቸው ላይ የለም፡፡ እነ አቶ ደመቀ ጭምር ተሯሯጡ፡፡ 7ቱ ሰዎች የሥራ-አስፈጻሚው ምርጫ ላይ መሳተፍ አለባቸው። ግን፣ ከየት ይገኙ?! እዚህ ጋ፣ አንድ ወዳጄ እየሳቀ የነገረኝን ላስፍረው፡- “በጠቅላዩ ትዕዛዝ የተመረጡት የዐማራ ብልጽግና አመራሮች፣ በየቦታው ተፈልገው ጠፍተው ትንሽ አንገላቱን፡፡ በመጨረሻ፣ የዐይነቱ ብዛት ለማየት ከሚያታክተው የምግብ ቡፌ አገኘናቸው፡፡ ለነገሩ፣ ጉባኤው የመጣለትም፣ ጉባኤው የመጣበት በንጉሡ ግብር ተጠምዶ ነበር።”
አሁን ጥያቄው፣ በግላጭ የተጣሰውን ሕግ፣ ምርጫ ቦርድ እንዴት ያየዋል? የጉባኤተኛውን ድምፅ ያስከብራል? ወይስ የጠቅላዩን ውሳኔ አድንቆ ሳይመረጡ የተቀላቀሉትን 7ት የዐማራ አመራሮች ያፀድቃል?
መቼም፣ የሕወሓትን ምርጫ “የጨበራ…” ብለህ ሙድ ስትይዘህ ከርመህ፤ እንዲህ ዐይነቱ አዋራጅ በዘርህ አይድረስህ!
በተረፈ፣ ዛዲግ አብርሃ ዐማራን ወክሎ ለማዕከላዊ ኮሚቴ መመረጡ፣ አካባቢው ላይ ከሚነሳው የባለቤትነት ጥያቄ፤ እሱም ሕወሓትን ከመቀላቀሉ በፊት ‘ራያ ትግሬ አይደለም’ የሚል ከመሆኑ አኳያ አያወዛግብም፡፡ ነገሩን ግራ-ገብ የሚያደርገው ከወራት በፊት ፓርላማ የገባውም ሆነ በሰሞኑ ጉባኤ የተሳተፈው በትግራይ ብልፅግና መሆኑ ነው፡፡ በርግጥ፣ እነ ዶ/ር አብርሃም ለማዕከላዊ ኮሚቴ 10 ሰው አቅርበው፣ 3 ሲያስመርጡ፤ የራያውን ልጅ ከነመኖሩም አልቆጠሩት፡፡ ይህም ሆኖ፣ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሃቅ፣ ከዛዲግ የፖለቲካ እድል አሳዳጅነት አንጻር፣ ለዐማራ የፈረመው አምኖበት ይሁን፣ ለፊርማቶሪ ተመድቦ የሚያውቀው አላሃ ብቻ መሆኑ ነው፡፡
አባቴ፣ ፖለቲካ የገባው ኦዴፓ ይግደለኝ! በክልሉ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዐማርኛ ተናጋሪ ቢኖርም፤ ከ60ው፣ 60ውን ሲደፍን አልሸከከውም፡፡
ከዚህ ውጪ፣ ‘በአፋቸው አሃዳዊነትን እያወገዙ፣ በፌደራሊዝሙ ላይ የፈጸሙት ውንብድና ነው’ ካልተባለ በቀር፤ አብዛሃው የዐማራ አመራር መባረሩ ለሕዝቡ ኬሬዳሽ ነው፡፡ በብሔር የተደራጁት እነ ገዱም ቁማሩን በልተው ቢሆን ኖሮ፤ ጠቅላዩ በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣን እንደለቀቁ ከነገሩን በኋላ፣ የበሻሻ መናፈሻ አስተዳዳሪ አድርገው ከመሾም አይመለሱም፡፡
የጉባኤውን አጀንዳ ከማሳረጋችን በፊት፣ ሦስት የዐማራ ክልል ተወካዮች ያቀረቡትን ጥያቄዎች፣ የኦዲት ሪፖርቱን እና የሕገ-መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ የተሰነዘሩትን ነጣጥለን እናስታውሳቸው፡፡
ሀ
የሦስቱ ሰዎች ጥያቄ እንዲህ ይነበባል፡- ‘ብልፅግና የተሟላ የአመራር ቁመና የለውም፤ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ አይሰጥም፤ ለምን? በእኛው ችግር በጦርነት የተፈናቀለው የወሎና የጎንደር ሕዝብ በአግባቡ አልተቋቋመም፤ በዚህ ምክንያት ሺዎች በረሃብ እያለቁ ነው፤ መሰረተ-ልማታቸው ወድሞ በችግር እየማቀቁ ነው፤ አሁንስ ምን ታስቧል? የወልቃይትና የራያ የወሰንና የማንነት ጥያቄ፣ የዐማራ ሕዝብ ቀዳሚ አጀንዳዎች ናቸው፤ ሕዝባዊ ጥያቄ ነው፤ እስካሁን ግን ምላሽ አላገኙም፤ ብልፅግና እነዚህን ጥያቄዎች እንዴት ያያቸዋል? ጥያቄዎቹ የእኛ የፖለቲከኞች ብቻ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል፤ መላው ዐማራ በዐደባባይ በጥይት የተመታበት ጥያቄ ነው፤ ሳይውል ሳያድር ሊመለስ ይገባል፤ ዐማራ በየሄደበት እየሞተ፣ እየተፈናቀለ፣ እኛ ግን ስለ ብልፅግና ነው የምናወራው፤ መጀመሪያ በህይወት የመኖር መብታችን ይረጋገጥ? ብልፅግናዎች ሞትን ተለማምደናል፤ ዐማራ በአራቱም አቅጣጫ በጠላት እንዲከበብ ተደርጓል፤ የሕዝባችን ሞትና ስቃይ ጨመረ እንጂ፣ አልቀነሰም፤ ብልፅግና የዐማራን ሞትና መፈናቀል ለምን አቅልሎ እንደሚያይ አልገባኝም፤ መፍትሔ እንፈልጋለን?’
እነዚህ የጉባኤውን ድባብ የቀየሩ ጥያቄዎች፣ የምስጋናውን መድረክ እንዳረከሱ ተቆጥሮ፣ በጭብጨባ ለማቋረጥ ተደጋግሞ መሞከሩ ግን አስደንጋጭ ነው፡፡ ርግጥ፣ የጠቅላዩ ሃራምባና ቆቦ ምላሽ ይበልጥ ያስደነግጣል፡-
"…የዐማራ ልዩ ኃይል፣ የዐማራ ፖለቲከኞች፣ የዐማራ አክቲቪስቶች፣ በሃይማኖት ስም የመሸጋችሁ በሙሉ ጩኸታም ናችሁ። ለምሳሌ በዐማራ ክልል ‘የዐማራ ልዩ ኃይል’ የሚባል አለ። ‘ልዩ ኃይል’ ማለት በእንግሊዝኛው ‘Special Force’ ማለት ነው። ዐማራ እንኳን Special Force ሊኖረው፣ Special ሚሊሻም የለውም። ራሱን መከላከል የማይችል ነው። እነዚህ አካላት ከእንቁራሪት ጋር ይመሳሰላሉ። ‘ለዐማራ እቆማለሁ’ የሚለው ሁሉ ማታ ማታ በቤቱ ተቀምጦ እንደ እንቁራሪት ሲጮህ ነው የሚያድር። ፋይዳ የሌላችሁ ናቸሁ፡፡ […] ከዚህ በኋላ ፅንፈኛ የዐማራ አመራር፣ ሰርጎ-ገብ የዐማራ አመራር፣ ለEthio 360 መረጃ የሚሰጥ የዐማራ አመራር፣ ‘ሞትን፣ ተሰደድን’ የሚል የዐማራ አመራር፣ ከለቅሶ በስተቀር ብልፅግና የማይታየው የዐማራ አመራር በሙሉ ተነቅሎ ይጣላል።"
አጃይብ! የሚያሰኝሽ ግን፣ ለአልተገናኝቶው መልስና ለውርጅብኙ ያጨበጭብ የነበረው የዐማራ ፖለቲከኛ ብዛት ነው፡፡ በተረፈ፣ እነ ጄነራል ተፈራ 60 ሺሕ ልዩ ኃይል በሚገባ ማሰልጠናቸውን ነግረውናል፡፡ በወታደራዊ ትርኢት አጅበው ሲያስመርቁም በሚዲያ አሳይተውናል፡፡ ይህን ኹነት እንዳስታውስ ያስገደደኝ ምናልባት ከማናናቁና ማጥላላቱ ጀርባ ‘የብተና ሴራ ይኖር ይሆን?’ የሚል ጥርጣሬ ነው፡፡ መቼም፣ ‘ዐማራ እየሞተ ነው፣ እየተፈናቀል ነው’ ሲባል፤ ከመንግሥት “ራሱን መከላከል የማይችል ነው፤” የሚል መልስ መስማት፣ የመጪው ጊዜ ‘ሜትሮሎጂ’ የከፋ እንደሚሆን ይጠቁማል፡፡
ለ
የኦዲት ኮሚሽን ሪፖርቱን በተመለከተ አቶ ፀጋ አራጌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቅርቧል፡-
“በዐማራ ብልፅግና አመራሮች በብድር ስም በተከፋፈሉት 60 ሚሊዮን ብርና ያለ አግባብ ወጪ በተደረገው 100 ሚሊዮን ብር ዙሪያ ሪፖርቱ በግልፅ አላስቀመጠውም፤ በደፈናው 44.9 ሚሊዮን ብር መባከኑን ብቻ ገልጻችኋል፤ የተብራራ ነገር የለውም፤ የኦዲት ክትትል ኮሚሽኑ ሪፖርትና መረጃ ለጉባኤው ለምን ማቅረብ አልተፈለገም? ምክንያቱስ ምንድነው? በአዳማው መድረክ ኮሚሽኑ ያቀረበውን የዐማራ ብልፅግና የዘረፋ ሪፖርት፣ ገንዘቡን የተከፋፈሉትና የወቅቱ የፓርቲው አመራር ሰዎች ‘የኦዲት ኮሚሽኑን ሪፖርት አንቀበልም’ ብለው ውድቅ አድርገውት ወጥተዋል፤ ለዚህ የኮሚሽኑ አመራሮች ምን መልስ አላቸው?”
የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ኢንጂነር አወቀ ኃይለማርያም ምላሽ ሰጥቷል፡- "ኮሚሽናችን ኮሚቴ አዋቅሮ ዘረፋውን አጣርቷል። በዚህም 44.9 ሚሊዮን መዘረፉን አረጋግጠናል። ከነገረ-ቀደም የፓርቲ ገንዘብ ለብድር አገልግሎት የሚውልበት ሕግም፣ ደንብም የለም። ድርጊቱ ሕገ-ወጥ ነው። ስለዚህ፣ ኮሚሽናችን የፓርቲው ገንዘብ ያለ-አግባብ መውጣቱን ያምናል። ዘረፋ ነው የተፈፀመው። ‘ገንዘብ አልወሰድንም’ ያሉ አመራሮች ዘረፋውን ሕጋዊ የብድር መልክ ለማስያዝ የሄዱበት መንገድም ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን የተሰጠ መልስ ካልሆነ በስተቀር፤ ዝርፊያ ስለመሆኑ ኮሚሽናችን አይጠራጠርም።"
በርግጥ፣ ኮሚሽነሩ ይህንን በቃል ያብራራውን የምርመራ ግኝት፣ በሪፖርቱ እንዳላካተተው ስሰማ አልገባኝም ነበር፡፡ ነገሩ የተገለጠልኝ ዶ/ር ዐቢይ "ተራ መጠቃቃት ነው" ብለው ሲያቃልሉትና ከ5 ደቂቃ በላይ ሲጨበጨብላቸው ነው። ሪፖርቱ የፀጋ አራጌ ተቃውሞ፣ የቀለመወርቅ ምህረቴ እና ምስራቅ ተፈራ ድምፀ-ተዓቅቦ ሲጎድልበትም፣ በ“ሙሉ” ድምጽ ፀድቋል።
ሐ
የፓርቲው ኘሮግራም ሲነበብ፣ መንጋው እንደ ማርሽ ባንድ እየተቀባበለ ሲያቆለጳጵሰው ቢውልም፤ በመጨረሻ አንድ የተለየ እጅ ተቀሰረ፤ አሁንም ፀጋ አራጌ ነው። እድሉ ሲሰጠው እንዲህ አለ፡-
“በኘሮግራሙ በገፅ 18 ላይ ‘ሕገ-መንግሥት የምናሻሽለው ራሱ ሕገ-መንግሥቱ በሚያዝዘው አካሄድ ነው’ ለምን ተባለ? ሕገ-መንግሥቱ ራሱን እንዳያሻሽል ተደርጎ በወያኔ የተጻፈ መሆኑ እየታወቀ፣ ብልፅግና ለምን የሕገ-መንግሥት ጠበቃ ይሆናል? ለሕገ-መንግሥቱ ‘ጥብቅና እንቁም’ ካላችሁም መብታችሁ ነው፤ ነገር ግን፣ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 5 እና አንቀፅ 49 ለኦሮሞ ጥያቄ ሲባል ተጥሶ፣ በኘሮግራም መልክ የቋንቋና የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዲመለስ ተደርጓል፤ ለምን የዐማራ የዘመናት ጥያቄስ፣ በኘሮግራም እንዲመለስ አልተደረገም?”
ዶ/ር ዐቢይም ጥያቄውን፡- "ሕገ-መንግሥት አንነካም። የሕግ ጉዳዮችን፣ ለሕግ ባለሞያዎች እንተዋቸው። እኛ ፖለቲከኞች ነን፣ ስለ-ሕግ አይመለከተንም፤" ብለው በአጭር ቀጩት፡፡
አያስቅም! እሳቸው ልክ ናቸው፡፡ ሸገር፣ ሸኔ የሆነችው በአፍጋኒስታን ሕገ-መንግሥት እንጂ፤ በኢትዮጵያ አይደለም፡፡
አባ ጠቅል
አፈጣጠኑ የዶፒንግ አትሌቶችን ያስከነዳው ኦዴፓ፣ ኦሮ-ማራን ዱቄት ለማድረጉ አያሌ ማሳያዎች ቢኖሩም፤ ለዛሬ በኦቦ አባዱላ ገመዳ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩትን ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩንቨርስቲ እና አየር መንገድን፤ እንዲሁም ዶ/ር አለሙ ስሜ የቦርድ ሊቀ-መንበር የሆነበትን ኢቢሲ ለእስረጂነት እንጥቀሳቸዋለን፡፡
ብአዴንና ኦሕዴድ፣ ሕወሓትን ተጠቃቅሰው ካጨሱት በኋላ፤ ሌባ ሲሰርቅ እንጂ፣ ሲካፈል መጣለቱ ወግ ነውና፤ በቅርጫው ሲጋጩ፣ እነ ደብረፂዮን ገና መቀሌ አልደረሱም፡፡ ጦርነቱ ደግሞ፣ የልዩነት አጀንዳቸው እየበዛ እንዲሄድ ገፊ-ምክንያት ሆነ፡፡ በተለይ፡- ወልቃይት-ራያ፣ ፋኖ እና ከሕወሓት ጋር የተጀመረው ድብቅ ድርድር ዋንኞቹ ናቸው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን፣ ‘በጉባኤ ተበላው’ የሚለውም ሆነ አገልጋይነቱ የተራዘመለት ሁሉ፣ ‘በሦስቱም ጉዳዮች በምልዓት ወጥሮ ነበር’ ማለት አይደለም፡፡ ለፌደራሉ እና ለአዲስ አበባ ምንግዴው አመራር፣ መብራት ለሌበት ጎጡ ሲራኮት ነው ጊዜው ያለፈው፡፡ አልያማ፣ እነ-ወልቃይት በጎሉበት የኬኒያው ምስጢራዊ ድርድር፣ ከአንዴም ሁለቴ ፊት-አውራሪው አባዱላ ባልሆነ ነበር፡፡
(በነገራችን ላይ፣ ጄነራል ባጫ ደበሌ ከመከላከያ በድንገት የመሰናበቱ መግፍኤ ‘ማን በሞተበት ነው፣ እሱ አራት ኪሎ ተቀምጦ የሚደራደረው?!’ የሚል ተቃውሞ ማንጸባረቁ የፈጠረው ድንጋጤ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ጀኔራል ባጫን ካነሳሁ አይቀር ግን፣ በአቢዬ ግዛት የሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ሜ/ጄ ሙዜን ሳልጠቅስ ማለፉ አይቻለኝም፡፡ ይህ ትግራዋይ ጄነራል ገና ከመነሻው በሕወሓት እና በእነ ዐቢይ መሃል የተካረረው ፍጥጫ ምቾት አይሰጠውም ነበር፡፡ ሁለቱም ‘ለኢትዮጵያ አይበጁም’ ብሎ ያምናል፡፡ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ስለነበረም፣ በኤጄቶ ዐመጽ አዋሳን ከታቀደላት ጥፋት ታድጓል፡፡ ከጦርነቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ኃላፊነቱን ለጄነራል ሰለሞን ኢተፋ በውክልና አስረክቦ፣ ሰላም ለማስከበር ወደ ሱዳን ሊሄድ አካባቢ ስለ-አገራችን ዕጣ-ፈንታ እኩለ-ሌሊት ድረስ አውግተን ነበር፡፡ ብዙ ነገር አነሳን፡፡ የሕወሓትን ወሮ-በላነት ያህል፣ የማዕከላዊው መንግሥትም ብስለት በጣም ያሳስበው ነበር፡፡ አንድ ከፍተኛ የኦነግ መሪን በቁጥጥር ስር አውሎ ካስረከበ በኋላ፣ ለምንና እንዴት እንደተፈታ ግራ እንደሚገባው አውርቶኛል፡፡ የኬኒያውን የኦነግ ማሰልጠኛ በተመለከተም ዝርዝር መረጃ ያጠናከረው እሱ የሚመራው እዝ ሲሆን፤ ወታደራዊ እርምጃ ወይም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ አለመሰጠቱ ‘ኦነግ እየፈረጠመ እንዲሄድ ያደርገዋል’ ብሎ ይሰጋ ነበር፡፡ ዛሬ ስጋቱ እውን ሆኗል፡፡ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የተገደለ እለት ደግሞ፣ ከአዋሳ ወደ አዲስ አበባ የመሄድ እቅድ እንዳለው የሚያውቅ አንድ ኦሮሞ ጄነራል ስልክ ደውሎ በፍጥነት እንዲወጣ የነገረውን፣ ጭፍጨፋው ከተፈጸመ በኋላ ቀጣጥሎ ለማሰላሰል እንደሞከረ አጫውቶኛል፡፡ በቅርቡ ይህ አገር ወዳድ መኮንን መኮብለሉን ስሰማ አዝኛለሁ፡፡ በርግጥ፣ የኦዴፓ-ኢትዮጵያ ያልገበረውን በሙሉ ‘የቀን ጅብ፣ ጁንታ…’ በሚል የመግፋት አባዜ ስለተጠናወታት፣ የጄነራሉ ውሳኔ አልገረመኝም፡፡)
በአናቱም፣ በድርድሩ ትሩፋት ይሆን በሌላ ምክንያት ባይረጋገጥም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕወሓት በወታደራዊ ቁመናው ተጠናክሮ የሚወጣበት በር ተበርግዶለታል፡፡ የፍትሕ ምንጮች እንደሚሉት ከአንድ ወር በፊት ዐሥር አንቶኖቭ አውሮፕላኖች (ሰባቱ ሽሬ፣ ሦስቱ መቀሌ) በተለያየ ጊዜ አርፈዋል፡፡ የተወሰኑት መነሻቸው ዩክሬን እንደሆነም ተሰምቷል፡፡ ይህ ሁኔታ፣ ‘ከአራት ኪሎ እውቅና ውጪ ነው’ ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በተቀረ፣ “መለማመጃችን” የተባለው “ሽፍታ” ከለታት አንድ ቀን ‘የድሮን ጥቃት ሰነዘረ’ የሚል ዜና ብሰማ አልደነቅም፡፡
እነ አሜሪካ ‘የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠር ኢሳያስ አፈወርቂ ከተወገደ፣ ደብረፂዮን እና ዐቢይ አያስቸግሩንም፤’ የሚል አቋም ከያዙ ሰንብቷል፡፡ የስቴት ዲፓርትመንት ሰዎችም አንዳንድ የኦዴፓ አመራሮችንና የብሔሩ ልሂቃንን በተናጠል እያገኙ ‘ኦሮ-ማራ ለቀንዱ ፖለቲከ አደገኛ ነው፤’ ማለት ከጀመሩ ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን ጄነራል Stephen Townsend የተባለ አሜሪካዊ ከፍተኛ መኮንን በቅርቡ ጦርነቱ የመፈንዳቱን አይቀሬነት መጠቆሙም ቅዠት አይመስለኝም፡፡ አቦይ ስብሃት ነጋም ‘ከአገር ወጥተው ተደራዳሪነቱን እያሳለጡ ነው’ መባሉ እውነት ከሆነ፣ ተለዋዋጭ ክስተቶች መኖራቸው ተገማች ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይም ከ45ቱ 32 ነባር የአዴፓ አመራሮችን አባርረው ሲያበቁ፤ ለዐዲሶቹ “…‘ሞትን፣ ተሰደድን’ የሚል የዐማራ አመራር፣ ከለቅሶ በስተቀር ብልፅግና የማይታየው የዐማራ አመራር በሙሉ ተነቅሎ ይጣላል፤" ሲሉ የሰጡት ማስጠንቀቂያ፣ ‘በቀጣይ የሚሆነውን ስለሚያውቁ ነው፤’ ወደሚል መደምደሚያ ይገፋል፡፡
እዚህ ጋ፣ ከጥቂት ሳምንት በፊት ተሰናባቹ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ አንድ አባል “የወልቃይትና የራያ ሕዝብ የወሰንና የማንነት ጥያቄ ‘ወዴት ተገፍቶ ነው ከወያኔ ጋር መደራደር?’ የሚል አጀንዳ የተከፈተው? እንዴት ይህንን ጉዳይ አታስቡትም?” የሚል ጥያቄ አዘል ተግሳጽ ሰንዝሮ እንደነበረ አስታውሰን እንቀጥል፡፡
ኦዴፓ ‘እንደ ዓይኔ ብሌን እጠብቀዋለሁ’ እያለ በመግለጫ አዛ ሲያደርገን የነበረውን ሕገ-መንግሥት ደፍጥጦ፣ አዲስ አበባን ጨለንቆ ማስመሰል ከጀመረ አራት ዐመት ሊሆነው ነው፡፡ ለግማሽ ክፍል-ዘመን በኦሮሙ ስም ሲቀነቀኑ የነበሩ የሃሰት ትርክቶች ያዋለዷቸው “ጥያቄዎች”ን እንደ ተረጋገጠ ሃቅ ወስዶ፣ በኃይል እየመለሳቸው ነው፡፡ ባለፈው እሁድ በተቋጨው ጉባኤ በፓርቲው ፕሮግራምና ሕገ-ደንብ ዐዲስ ከተካተቱ አንቀጾች፡- የክልሎች የሥራ ቋንቋ የፌደራሉም እንደሚሆኑ እና የብልፅግና ዋና መቀመጫ ‘አዲስ አበባ/ፊንፊኔ’ እንደሚባል ያሰፈረው ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሕገ-ወጥነት በጠርዘኛ-ልሂቅኑ አገላለጽ፡- ‘ከ150 ዐመት በፊት የተወሰደውን ማስመለስ’ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ወሎና ራያም እንደማይቀርላቸው ይናገራሉ፡፡ ነገሩ እየተናበቡ መፈጸሙን የሚያረዳህ ደግሞ፣ ጠቅላዩ ‘የሌሎች ሕዝቦች ጥያቄዎችን በፓርቲ ፕሮግራም ለመመለስ ሕገ-መንግሥቱ ያግደናል’ ሲሉህ ነው፡፡ በመጨረሻው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጃንጠራር አባይ፡- “የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ክልል ድንበር ጥያቄ መቼ ነው የሚፈታው? የፌደራል መንግሥት ጣልቃ-ገብቶ ለምን አይፈታውም? ድንበር መከለል ከሕገ-መንግሥት ጋር አይያያዝም፤ ሌላ የሚጠበቅ ነገር ከሌለ በስተቀር” ብሎ የጠየቀው ጥያቄ ግዘፍ-የሚነሱ እውነታዎች የታጨቁበት ቢሆንም፤ “አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ” ብሂልን የዘነጋ ነው፡፡
በርግጥ፣ ጃንጠራር ምሬቱን እንዲህ ሲል ዘርግፏል፡- ‘የአዲስ አበባ አስተዳደር ልክ አይደለንም፡፡ ሶፍትዌራችን አንድ አይደለም፡፡’
ይሁንና፣ ከንቲባ አዳነች አበቤ ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዣንጠራርን በመጠቆም ማስመረጧን ስሰማ፣ በኦዴፓ የትወና ችሎታ መደመሜን አልሸሽግም፡፡
አሁን ወደ ተቋማቱ እንለፍ፡፡
፩
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩንቨርስቲ ቦርድ ሊቀ-መንበር፡- አባዱላ ገመዳ፣ ምክትሉ የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ፣ ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና ሲሆኑ፤ ሁሉም ኦሮምኛ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ዶክተሩ በ2010ሩ “ለውጥ” የተቋሙ አለቃ ሆኑ ከተመደበ በኋላ፣ ንቅለ-ተከላውን አስፈጽሟል፡፡ አራቱን የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታዎችም በዘመነ-ኢሕአዴግ ኦሮሞ፣ ደቡብ፣ ዐማራና ትግሬ እኩል ይከፋፈሉበት የነበረው አሠራር ተቀይሯል፡፡
ኦሮሞው ዶ/ር ጠና በቀለ ሁለት የምክትል ፕሬዚዳንትነት (የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት እና የምርምርና ማኀበረሰብ ም/ፕሬዚዳንት) ደርቦ ከያዘ ዐመት ሆኖታል፡፡ ዘጠኙን ዲኖችም ቁጠራቸው-
1. የትምህርትና ሥነ-ባህሪ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቀደ ቱሉ ኦሮሞ
2. የከተማ ልማት ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ይፍሩ ዋቅቶላ ኦሮሞ
3. የሚንሊክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኩማ ጌታሁን ኦሮሞ
4. የቋንቋዎችና ሥነ-ሰብ ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ፍሰሀ ሞቱማ ኦሮሞ
5. የሳይንስ-ሾርድ ካምፓስ ዲን አቶ አቤል ጫላ ኦሮሞ
6. የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ዲን ዶ/ር የማነ ጎሳየ ደቡብ
7. የተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ዲን ዶ/ር ማስረሻ አማረ ትውልዱ ደብረዘይት
8. የማኀበራዊ ሳይንስ ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ግርማ በላቸው ዐማራ
9. የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ ዲን ዶ/ር ሀይለሚካኤል ሙሌ ዐማራ
በነገራችን ላይ፣ በተቋሙ ከኦሮሞ ውጪ ለመመደብ ባልተጻፈ ሕግ የብልፅግና ወዳጅ መሆን ያስገድዳል፡፡ ፓርቲውን ‘ለእኛ እንደሚመች አድርገን ነው የሠራነው’ የተባለውን እዚህ ጋ ታገኘዋለህ፡፡ የዳይሬክተር ኃላፊነት ቦታዎችም የብሔር “ማመጣጠኑን” የጠበቀ ነው፡-
1. የፕሬዘዳንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙህዲን መሀመድ ሁሴን ኦሮሞ
2. የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ደጀን ጫካ ኦሮሞ
3. የአካዳሚክ ስታፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አፈታ ኦሮሞ
4. የድህረ-ምረቃ ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሴፍ ቤኮ ኦሮሞ
5. የዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ቱሉ ኦሮሞ
6. የሳይንስ-ቴክኖሎጂ ኢንጅነሪንግ ማቲማቲክስ (STEM) ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ ኦሮሞ
7. የማኀበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር በሌና ተርፌሳ ኦሮሞ
8. የተከታታይና የርቀት ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ቶሎሳ ኦሮሞ
9. የሥርዐተ-ፆታ ዳይሬክተር ወ/ሮ ምኞት ጌታቸው ኦሮሞ
10. የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ገርቤ ኦሮሞ
11. የንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አብዱ ሁሴን ኦሮሞ
12. የግዢ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ኦሮሞ
13. የደህንነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባዬ ኦሮሞ
14. የትምህርት ጥራት ዳይሬክተር ዶ/ር አልማዝ ዋሴ ደቡብ
15. የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ረዳት ዶ/ር አልማዝ ደብሩ ደቡብ
16. የምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ቅድስት ዮሐንስ ዐማራ
17. የቅድመ-ምረቃ ዳይሬክተር ዶ/ር መስፍን አበበ ዐማራ
18. የፀረ-ሙስና እና ሥነ-ምግባር ዳይሬክተር ዶ/ር የሺጥላ መንግሥቴ ዐማራ
19. የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ም/ፕሬዚዳንት ረዳት አቶ መስፍን ወንደሰን ዐማራ
በግልባጩ፣ ዶ/ር ሩቂያ ሀሰን የምርምርና ህትመት ዳይሬክተር፣ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የምርምርና ልህቀት ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ጌታው ባዩ የቋንቋዎችና የማኀበረሰብ አገልግሎት ዲንን ጨምሮ፤ በርካታዎች ከኃላፊነታቸው ከተነሱበት ምክንያት፣ ዋንኛው ‘ኦሮሞ አለመሆን ነው’ ሲባል መስማቱ በራሱ ብዙ ይነግርሃል፡፡ በርግጥ፣ የዩንቨርስቲው ጉድ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ‘ጭላሎ አውራጃ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት’፣ ስብሰባዎችን በኦሮምኛ የሚያደርግበት ጊዜም መኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ከአንድ ወር በፊት ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጋር በጋራ የሚያዘጋጀውን ኮንፍረንስ በተመለከተ የራሱን ስብሰባ አድርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ኃላፊ በመምህራን ክበብ ውስጥ “በቋንቋችን ስብሰባ ማድረግ ችለናል” ብሎ በኩራት ሲያወራ፤ ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆኑም መሳተፋቸውን የሚያውቅ መምህር፣ እንዴት ሊግባቡ እንደቻሉ ሲጠይቀው፤ ዘና ብሎ ዶ/ር ብርሃነመስቀል እያስተረጎመ መወያየታቸውን “አብስሮታል”፡፡
ዝውውርን በተመለከተም አድሏዊው አሠራር ጠርዝ-የረገጠ ነው፡፡ በስም ለመዘርዘር ገጽ አይበቃም፡፡
ፕሬዚዳንቱ በዘረኝነት ላይ አምባገነንነትንም መደረቡ ግን፣ ተቋሙን ለከፋ አደጋ ማጋለጡ አይቀርም፡፡በዩንቨርስቲው የሚሠሩ ጥናቶች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያስገኙም፣ ከመመሪያው ውጪ በሁሉም ላይ በጉልበቱ ካልተሳተፍኩ ባይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ 125 መምህራኖች በቦሌ ቡልቡላ የተሰጣቸው የኮንዶሚኒየም ቤት በስማቸው እንዲዘዋወር ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሲወስዱት ደግሞ፣ ‘ተደፈርኩ’ በሚል ብስጭት መምህራኑ ከቤት ወደ ሥራ የሚገለገሉበትን ሰርቪስ አግዷል፡፡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት የሚያመላልሰው ግን በተቋሙ መኪና ነው፡፡ በቅርቡ፣ የዩንቨርስቲው ዘመናዊ ጂም እቃዎች ተፈታተው ቢወሰዱም፤ የተጠየቀም የተከሰሰም ስለመኖሩ አልሰማሁም፡፡
ተቋሙ ምን ያህል የካድሬ መፈንጫ እንደሆነ የምትረዳው፣ በከንቲባ አዳነች አዛዥነት “የ6ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ አፈጻፀም ስኬቶችና ተግዳሮቶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር” በሚል ርዕስ ‘ምርምር አካሄድኩ’ ሲልህ ነው፡፡ ነገሩን በቅንነት እንውሰደው ቢባል እንኳ፣ በጥናቱ የተሳተፉት ከዶ/ር አልማው ክፍሌ በቀር፣ የብልፅግና ወዳጆች ናቸው፡፡
ዶ/ር ብርሀነ መስቀል ጠና፣ ኦሮሞ
አቶ ሙህዲን መሀመድሁሴን ኦሮሞ
ዶ/ር አየነው ብርሀኑ ኦሮሞ
ዶ/ር መልካሙ አፈታ፣ ኦሮሞ
ዶ/ር ፍሰሀ ሞቱማ፣ ኦሮሞ
አቶ ሮቤል ሳህሉ፣ ዐማራ
ዶ/ር አልማው ክፍሌ፣ ዐማራ
በነገራችን ላይ፣ በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ምርጫ ቦርድም በራሱ በኩል እያስጠና ሲሆን፤ የሳንሱር ሰለባ ካልሆነ፣ ብዙ ጉድ መዘርገፉ አይቀርም፡፡
ኢቢሲ
ይህ ተቋም ከተመሰረተ ጀምሮ የሕዝብ ሆኖ አያውቅም፡፡ የጃንሆይን ምስል እንደ ዜና በየቀኑ “ሲያስኮመኩም” ባጅቶ፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲመጣ፣ በአንድ ጀንበር አብዮተኛ ሆኗል፡፡ በድኀረ-ደርግ ኢሕአዴግ ፈንጭቶበታል፡፡ ካለፉት አራት ዐመት ወዲህ ደግሞ፣ ኦዴፓ እያንጃበበበት ነው፡፡ ታላቁ ጥላሁን ገሰሰ “አልማዝን አይቻት፣ አልማዝን ባያት…” እንዲል፤ ከዶ/ር አለሙ በፊት፣ የቦርድ ሰብሳቢው ኦቦ ፍቃዱ ተሰማ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ፣ በ“ሪፎርም” ስም ተቋሙን ለመጠቅለል የተሞከሩ እርምጃዎች በሙሉ፣ ዐደባባይ እየወጡ ሲቸገሩ ቆይቷል፡፡ አሁን ፈር እየያዘ ይመስላል፡፡ የዘንድሮ የዐደዋ በዓልን ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ በአርበኞች ፎቶ አስደግፎ በዘከረበት ፕሮግራሞቹ፣ ዐፄ ምንሊክን ማሳየት አለመፍቀዱም በማን ስር እንደዋለ ይነግርሃል፡፡ በባህር ዳር እዚህ ግባ የማይባል አንድ ቢሮ አስመርቆ በቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሰጠ ተቋም፤ የዐድዋ ዕለት የዜና ሰዓቱን ጠብቆ ከመዘገብ አለማለፉ፣ የሰፈነበትን መንፈስ ያመላክታል፡፡
የባሌ ልጅና የጠቅላዩ ቀኝ እጅ ዋና ሥራ-አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱም ‘ኢቢሲ ዐማራ በዝቶበታል፤ ይሄንን ለማስተካከል እየሠራን ነው፤’ የሚለው ፊት-ለፊት ነው፡፡ ድምዳሜው ከተረኝነት እንጂ፤ ከማመጣጠን አለመዛመዱን የሚያስረግጠው ግን፣ ‘በዛ’ የሚለው አንዱን የዐማርኛ ቋንቋ ክፍል ብቻ መርጦ መሆኑ ነው፡፡ ተቋሙ፡- በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሌኛ… በሌሎቹም ቋንቋዎች በየብሔሩ ተወላጆች ያደራጃቸው ክፍሎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ አድርባይነት ምን ያህል እንደ ነገሠ የሚያረዳህ ደግሞ፣ ኃላፊው ወደ ሥልጣን የመጣው ከምርጫው በኋላ ቢሆንም፤ የቴሌቪዥን ስቱዲዮ መግቢያ 1ኛ ፎ ላይ የብልፅግናን የምርጫ ምልክት መስቀሉ ነው። መቼም፣ እንዲህ ዐይነቱ ያፈጠጠ ድፍረት በአዛውንቱ ኢሕአዴግም አልታየም፡፡ ቢያንስ የተቋሙ ፖሊሲ በመርህ ደረጃ ከሁሉም ፓርቲዎች ነፃ መሆኑን የሚገልጸው አልጣሰም፡፡
ፍሰሃ በዋና ሥራ-አስፈጻሚነት በተሾመ በወሩ (ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም) ሠራተኞቹን ኢትዮጵያ ሆቴል ሰብስቦ በፈረደበት የ“ሪፎርም” አጀንዳ አወያይቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ዶ/ር ዐቢይ በ“ድንገት” ተከስተው ሰርፕራይዝ አድርገዋቸዋል፡፡ “እዛ ኢቲቪ ሄጄ የላችሁም፤ እዚህ እንደሆናችሁ ሲነግሩኝ ስበር መጣሁ፤” አሉ፣ እንደ ሮጠ ሰው ቁና-ቁና እየተነፈሱ፡፡ በሞቀው ጭብጨባ መሃል፣ አየር ስበው ቀጠሉ፡- “ከዚህ ከውቃቢያም ቤት ውጡ፡፡ እኔ ሸጎሌ የመከላከያን ቤት እንድትወስዱ መከላከያን አሳምኛለሁ፡፡ ጅማ በር ደግሞ የመኖሪያ ቤት ይሠራላችኋል፡፡” አሁንም ደማቅ ጭብጨባ፡፡
በመጨረሻም፣ በዘወርዋራ ‘የሪፎርሙ ደራሲ እኔ ነኝ’ በሚል መልእክት አሳረጉ፡፡ “ዋና ሥራ-አስፈጻሚው ልጅ ነው አግዙት፡፡ የፈለገውን እንዲወስን ነግሬዋለሁ፡፡ እኔ ኢቢሲን እወደዋለሁ፡፡”
ሃሃሃ “…አልበላሽምን ምን አመጣው!?” አለ፡፡ ኦቢኤን በቦሌ እምብርት ምን የመሰለ ህንፃ ሲገነባ፤ በቅጡ የሠራተኞች ሰርቪስ የሌለውን ኢቢሲ፣ ሸጎሌ ጫካ መወርወር?!
የሆነው ሆኖ፣ “ልጁ”፣ ከኦቢኤን ከመጣው አብድሩሃማን ሩቤ እና ከጉራጌዋ ሀቢብ ፋሪስ ጋር ተጋግዞ “ዐዲስ ትውልድ” በሚል ሽፋን አንጋፋዎችን አባርሮ፣ በተረኛ የሚሞላውን “ሪፎርም” ሊተገበር ሽር-ጉዱን ጨርሷል፡፡ የምደባው መስፈርት ለተርታው ሠራተኛ፡- ‘የትምህርት ማስረጃ፣ የሥራ ልምድ፣ የማህደር ጥራት፣ የሥራ-አፈጻጸም…’ እና (ለአመራርነት ‘አንድ ዐመት በኃላፊነት የሠራ’) የሚል ቢጨምርም፤ አካሄዱ የተለመደው ማደናገሪያ ነው፡፡ እነዚህ መስፈርቶች በድምሩ ከ60 ይታረማሉ፡፡ ቀሪው 40 ደግሞ አመራሩ የዓይን ቀለም እያየ የሚሰጠው በመሆኑ፤ ለማባረር ያሰበውን እንደ ፊሊቲ በቀላሉ ይረፈርፈዋል፡፡ ባሳለፍነው ወር ከቦታቸው የተነሱት፡- ካሳሁን ቃሲም የመዝናኛና ስፖርት ዲቪዥን ም/ስ/አስፈጻሚ፣ ፀሐይ አክሊሉ የቋንቋዎች ዲቪዥን ም/ስ/አስፈፃሚ፣ አባይነህ ጥላሁን የዜና ማዕከል ኃላፊ፣ ነፃነት ፈለቀ የብሔራዊ ሬድዮ ዲቪዥን ዋና አዘጋጅ፣ ስለሺ ዳቢ የFM 104.7 ኃላፊ፣ ኤርሚያስ ጌታቸው የFM 97.1 ኃላፊ ይጠቀሳሉ፡፡ ከስለሺ በቀር፣ ሁሉም ዐማራ መሆናቸውን ስታይ፣ እየተቆፈረ ያለው ጉድጓድ ብሔር እንዳለው ይገለጥልሃል። ከቦታቸው ተሸረው "አማካሪ" በሚል የዳቦ ስም ‘ስልጠና ግቡ’ መባላቸው እንኳ “ዶሮን ሲያታልሏት…” ነው፡፡
በግልባጩ፣ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ቻይና ለትምህርት እንደሚላኩ ሲነገራቸው፣ ለኦሮሚያ ብልፅግና አመልክተው ‘አትንኳቸው፣ የሹም ዶሮ ናቸው!’ ተብለው የቀጠሉት ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ፡- ተፈራ ቶሌራ የፋይናንስ ዲቪዥን ም/ስ/አስፈጻሚ፣ ፍቃደ ምርከና የIT ኃላፊ፣ ጥበበ ቦጋለ የሠው ኃይል ልማት ዲቪዥን ም/ስ/አስፈጻሚ፣ ዮሴፍ ዮናስ የፕሮሞሽንና ገበያ ልማት ዲቪዥን ም/ስ/አስፈጻሚ ሲሆኑ፤ ለዐይነት ደቡቡ የጠቅላላ አገልግሎትና ንብረት ዲቪዥን ም/ስ/አስፈጻሚ ጌታሁን ቲማ ተቀላቅሏል፡፡
በሪፎርሙ መሰረት ምደባውን ለማሰለጥ ሦስት ከአመራሩ፣ ሁለት ከሠራተኛው በድምሩ አምስቱ የተመረጡትም (እቴነሽ ኃ/መስቀል፣ ሠለምን በረደድ፣ ቶላ ዳበሳ፣ አሠፋ በቀለና መሳይ ሁሬሳ) ሰዎች ቢሆኑ፤ ከእቴነሽ በቀር ሁሉም ሹመት በማግኘታቸው፤ ወዴት ያጋድላሉ? የሚለውን ለማወቅ ዳመራው እስኪወድቅ አትጠበቅም፡፡
ኢቢሲን አድክም የሚያደርገው ደግሞ፣ በአንደ በኩል ካሜራ ማኖቹ በተበጣጠሰ ‘ኒክ ማይክ’ ድምፅ እየተቆራረጠባቸው ለመሥራት ሲገደዱ፤ በሌላ በኩል፣ ለዐዲሶቹ ተሿሚዎች 10 ሱዙኪ መኪና (እያንዳንዱ በ1.3 ሚሊዮን ብር) መገዛቱ ነው። ሠርግና ልደት በድሮን በሚቀረጽበት ዘመን፣ ተቋሙ የነበሩት ሁለት ድሮኖች በብልሽት ከአገልግሎት ውጪ ቢሆኑም፤ ገንዘቡ በቅንጦት መኪና መባከኑን ቀጥሏል፡፡
ሌላው ፈገግ የሚያሰኘው ክስተት፣ ከትላንት በስቲያ ዶ/ር ዐቢይ በጽሕፈት ቤታቸው የክልል ርዕሰ-መስተዳድሮችንና ሁለቱን ከንቲባዎች በሰበሰቡበት ወቅት ከኢቢሲና ፋና በቀር፣ የሌሎቹን ካሜራ ማኖች “የሰው መልክ ታበላሻላችሁ! ካልቻላችሁ ከፋና ተማሩ። ሁለተኛ የክልል ካሜራዎች እዚህ እንዳይመጡ!” ብለው ሲያበቁ፣ ወደ አዳነች አቤቤ እየተመለከቱ “የናንተም እዚያው የዞናችሁን የወረዳችሁን ይስሩ። EBC ይበቃል ለዚህ፤” ማለታቸው ነው፡፡ ጠቅላዩ ስብሰባው ሲያልቅ ኢቢሲና ፋናም ቢሆን የቀረጹበትን ሚሞሪ ካርድ ከካሜራዎቻቸው አውጥተው ካስረከቧቸው በኋላ ነው፣ ወደመጡበት እንዲመለሱ የፈቀዱላቸው፡፡
እውነት ይሆን እንዴ ‘ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጠፉ ፎቶዎቻቸውን ሳይቀር ራሳቸው ይመርጣሉ፣ ኤዲት ያደርጋሉ’ ሲባል የነበረው?
ባልተያያዘ ዜና፣ ባለፈው ሳምንት አንድ ሰውን ከእነ ህይወቱ እሳት ውስጥ በመገፍተርና አሳቅይተው በመግደል የተጠረጠሩ 17 የመከላከያ አባላት፤ እንዲሁም በቦታው ከነበሩ 27 የሲዳማ ልዩ ኃይል ውስጥ 4ቱ ለመገላገል መሞከራቸው ስለታወቀ፤ 23ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ፍትሕ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡ ነውረኝነትና ጭካኔ በተጠናወተው መንገድ ህይወቱ ያለፈው ግለሰቡ፣ መጀመሪያ ከጀርባው በአንድ ጥይት ተመቶ እንደነበረም ታውቋል፡፡
አልጨረስንም፡፡