Page 1 of 1

የአማራ ህዝብ ትግል ዳራ እና የትግል አቅጣጫዎች (የመነሻ ሃሳብ ሰነድ, 63 pages document)

Posted: 18 Feb 2022, 18:36
by Wedi
የአማራ ህዝብ ትግል ዳራ እና የትግል አቅጣጫዎች (የመነሻ ሃሳብ ሰነድ)

በመምህርት መስከረም አበራ የተዘጋጀ





የአማራ ህዝብ ትግል ዳራ እና የትግል አቅጣጫዎች (የመነሻ ሃሳብ ሰነድ)

በመምህርት መስከረም አበራ የተዘጋጀ


ይዘት
1. መግቢያ
2. የሰነዱ አስፈላጊነት
3. የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ አብዮተኞች ዕይታ- ከትናንት እስከ ዛሬ
4. ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት፣የዘውግ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ መስተጋብር
5. የዘውግ ፖለቲካ ከ1983-2010ዓም በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳትና የጋረጠው ፈተና
6. በድህረ-ህወሃት የአማራ ህዝብ የገጠሙት ፈተናዎች
7. የአማራን ህዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ማዕቀፍ ውስጥ መመለስ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
8. የአማራ ንቅናቄ አስፈላጊነት እና ተፈጥሮ
9. የአማራ ንቅናቄ ትግል ውስንነቶች
10. የአማራ ንቅናቄ ሃይሎች በትግል ጉዟቸው ከግንዛቤ ሊያስቧቸው የሚገቧቸው አንኳር ጉዳዮች
11. የአማራ ህዝብ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ
12. የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችና የመደራደሪያ ነጥቦች
13. በብሄራዊ የምክክር መድረኩ የአማራ ህዝብ በማን ይወከል?
14. በምክክር መድረኩ የአማራ ተደራዳሪዎች ሊገጥማቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
15. ብሄራዊ ምክክር ለአማራ ህዝብ ሊያመጣው የሚችለው ፋይዳ
16. የአማራ ንቅናቄ የወደፊት ትግል እንዴት መቃኘት አለበት?
17. መደምደሚያ

1. መግቢያ

የአማራ ህዝብ1 ከኢትዮጵያ የሃገረ-መንግስትነት ታሪክ ጋር ጥብቅ የስነ-ልቦና ቁርኝት ያለው ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ለምዕተ-ዓመታት ከአማራ ማንነቱ ይልቅ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ላይ ትኩረት ያደረገ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያራምድ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ባለፈችበት የታሪክ ምዕራፎች ሁሉ ልዩ ተጠቃሚነት ያለው ህዝብ ነበር ማለት አይደለም፡፡ ይልቅስ በሃገሪቱ የተነሱ አገዛዞች በሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ላይ ያደርሱት የነበሩት በደልና ጫና ሁሉ በአማራ ህዝብ ላይም ደርሷል፡፡ በመሆኑም ሌሎቹ የሃገሪቱ ህዝቦችና የአካባቢ መሪዎች የተበደሉ ሲመስላቸው በነገስታቱ ላይ ያካሂዱ የነበረው አመፅ አሁን የአማራ ክልል በተባለው ህዝብና በአካባቢው ባላባቶችም ሲደረግ የኖረ ነው፡፡

የአማራ ህዝብ ነገስታቱ ያደርሱብኛል ያለውን የአስተዳደር ግድፈት፣ ብዝበዛ እና በደል በህዝባዊ ግጥሞቹና የተለያዩ ስነ-ቃላዊ ተግባቦቶቹ ሲገልፅ ኖሯል፡፡ በደሉ ከፍ ያለ ሲመስለውም ነገስታቱን የሚቃወም ግልፅ ዓመፅ ሲያካሂድ ነበር፡፡ ለዚህ ቀዳሚው ተጠቃሽ እማኝ የጎጃም ገበሬዎች አማፅ ነው፡፡ ይህ አመፅ በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች ከተደረጉ አመፆች አንዱ ነው፡፡ በባሌ፣ በጌዲኦ፣ በትግራይ ከተደረጉ አመፆች እኩል በጎጃምም የገበሬዎች አመፅ ተካሂዷል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ዛሬ በበርካታ አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች እንደሚታሰበው የነገስታቱ ስርዓት ለአማራው ህዝብ የተለየ ምቹ ፖሊሲ እንዳልነበረው ነው፡፡

ከገበሬው አመፅ በተጨማሪም በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች እንደ ካዎ ጦና ያሉ የአካባቢ ባላባቶች በንጉሰ ነገስቶች አስተዳደር ላይ ያምፁ እንደነበረው ሁሉ በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ተብሎ በተከለለው አካባቢ የነበሩ ባላባቶችም ያመፁ ነበር፡፡ ለምሳሌ በማይጨው ጦርነት በርካቶቹ የጎጃም፣ የወሎ እና የየጁ መኳንንት ንጉሰ ነገስቱን በመቃወም በጦርነት እንዲሳተፉ የቀረበላቸውን ጥሪ እስከ መግፋት ደርሰው ነበር፡፡ በተመሳሳይ በዛሬው የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ይመሩ የነበሩ ራስ፣ ደጃዝማቾች በአንድ የአማራ ማንነታቸው ህብረት ፈጥረው ሌሎችን የሚወጉ ሳይሆኑ እርስ በእርሳቸው የማያባራ ደም መፋሰስ ያስከተለ ውጊያ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በሸዋው ንጉስ ምኒልክና በጎጃሙ ራስ ተክለሃይማኖት መካከል የተደረገው በደም አፋሳሽነቱ ወደር የሌለው የኢምባቦ ጦርነት ነው፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረዥም የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ አማራው እንደ ህዝብ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪና ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ የመውሰዱ ነገር ከሰላሳ አመት ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኗል፡፡ በዚህ ስሁት እሳቤ ላይ ተቁሞ ህገ-መንግስት ተፅፏል፡፡ በመሆኑም የትናንት ጨቋኝ ተደርጎ የተወሰደውን የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ማሳደድ፣ መግደል፣ ማፈናቀል፣ ንብረቱን የመንጠቁ ወንጀል ህጋዊ ማዕቀፍ አግኝቷል፡፡በመሆኑም የአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ መከራ በህገ-መንግስት የተፈቀደ ተገቢ ተግባር እስከ መምሰል ደርሷል፡፡ ስለሆነም ሰላሳ አመት የዘለቀው በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገው ዘር ማጥፋትን/ማፅዳትን የጨመረ ወንጀል ጠያቂም ተጠያቂም የሌለው ቀጣይቱን የጠበቀ ሰንሰለታማ የወንጀል ትርዒት ሆኗል፡፡

በሃገሪቱ ለውጥ መሰል ነገር በመጣ ቁጥር (የ1983 ዓምን ለውጥ ተከትሎ በበደኖ፣ አርባጉጉ ወዘተ የታየው አሰቃቂ የአማራ ህዝብ ፍጅት)፣ ሌላው ቀርቶ የግለሰቦችን ሞት አይነት ድንገተኛ ክስተት (የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ያስታውሷል) በተከሰተ ቁጥር ሳይቀር የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት እንደ ዋዛ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ አማራው በተወሰነለት ክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ በህይወት የመኖር መብቱ ያለምንም ጠያቂና ከልካይ ይጣሳል፡፡በተለይ በኦሮሚያ ክልል አማራውን የሚጨፈጭፉ ታጣቂዎች በግልፅ ሰልጥነው፣በገፍ ታጥቀው፣ ያለምንም ከልካይ በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ ህፃን አዋቂ ሳይለዩ፣ በቀንም ሆነ በሌሊት "አማራ" ያሉትን ሁሉ ይረሽናሉ፣ ንብረቱን ይዘርፋሉ ያፈናቅላሉ፡፡ አማራው አማራ መሆኑ ብቻ ወንጀል ሆኖ ይህ ሁሉ በደልና መከራ ሲወርድበት ጠበቅ አድርጎ የሚጠይቅ አካል ስለሌለ በወንጀሉ የሚጠየቅም አይኖርምና የአማራው በደል እንደ ተገቢ ነገር ቀጥሏል፡፡

የአማራ ህዝብ ከሰላሳ አመት ወዲህ እያስተናገደው ያለው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የጨመረ በደል ስምረት ያገኘው አማራውን ጨቋኝ አድርጎ የሚያቀርበው አስተሳሰብ ስልጣን በመያዙ ምክንያት ነው፡፡ የአማራውን ህዝብ ጨቋኝ አድርገው የሚፈርጁት እነዚህ ቡድኖች ኢትዮጵያን የሰራውም አማራ ነው ብለው ያስባሉ፡፡በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያም መፍረስና ወደ ተለያዩ ዘውጎች ቅርጫነት መቀየር አልያም ፈርሳ እንደገና መሰራት ያለባት ሃገር ነች ብለው ያምናሉ፡፡ኢትዮጵያን በአማራ በኩል ሲጡሉ የኖሩት እነዚህ አማራ ጠል የፖለቲካ ሃይሎች በህወሃት የትጥቅ ትግል ድል አማካይነት ወደ ቤተ-መንግስት ሲገቡ አማራን የሃገሪቱ መርገም ሁሉ መነሻ አድርጎ የሚያስበውን እሳቤያቸውን የህገ-መንግስትም ሆነ የሌሎች ማህበረ-ፖለቲካዊ ደምባደምብ ማዕቀፎች ሁሉ ማጠንጠኛ አድርገዋል፡፡

እነዚህ ቡድኖች ይህን ሲያደርጉ የአማራው ልሂቅ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል ሁሉ ወደ እርሱ የተወረወረ ለዘመናት ለመንቀል የሚያስቸግር ፍላፃ መሆኑን ሊረዳና አደጋውን በሚመጥን ሁኔታ ሊታገለው አልቻለም፡፡ በምትኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የከሳሾቹንና የአሳዳጆቹን አማራ-ጠል መንገድ ሲያቀና የኖረ/እያቀና ያለ ነው፡፡ ይህ የአማራ አብዛኛው ልሂቅ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታን ያለመገንዘብ አደገኛ አካሄድ የአማራን ህዝብ ከሩብ ምዕተ-ዓመት ለበለጠ ዘመን በህይወት የመኖር መብትን ማጣትን የጨመረ ውድ ዋጋ አስከፍሏል፡፡

ይበልጥ የሚያሳስበው አማራ ጠሉ አስተሳሰብ ስልጣን ከያዘበት ዘመን(1983ዓም) አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የአማራ ህዝብ ያለበት አደገኛ ሁኔታ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ለሰራው ታሪካዊ በደሉ የሚከፈል ተገቢ የታሪክ ማካካሻ ተደርጎ እየተወሰደ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህን አደገኛ ሁኔታ ለመቀልበስ ከአማራ ልሂቃን የሚቀድም አካል አይኖርም፡፡ ስለሆነም ነገሩ ከሆነው በላይ እንዳይከፋና ጭራሽ አማራ የሚባለውን ህዝብ የሚያጠፋ እንዳይሆን መታገል የአማራ ልሂቃን እና ህዝብ ድርሻ ነው፡፡ አመርቂ ትግል ለመታገል ደግሞ የችግሩን አስከፊነት በሆነው ልክ መረዳትና ችግሩን በትክክል ሊያስወግድ የሚችለውን የትግል መስመር መያዝ ያስፈልጋል፡፡

የአማራ ህዝብ ማንነቱን መነሻ አድርጎ የተሰነዘረበትን አጅግ አሰቃቂ የጥፋት በትር ለመመከት በማንነቱ መደራጀት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑ ብዙ ማከራከሩ እያበቃ ነው፡፡ በመሆኑም በርካታ በማንነታቸው የተደራጁ የአማራ ሃይሎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ሆኖም የአማራውን ህዝብ ጊዜ የማይሰጥ አንገብጋቢ በደል ነቅሶ አውጥቶና የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችን በግልፅ አስቀምጦ ህዝቡን ማታገል ላይ ብዙ የሚቀር መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህን ክፍተት ለመድፈን የአማራ ህዝብ ያለበት ጊዜ የማይሰጥ ችግር የሚያሳስበው አካል ሁሉ ሊረባረብ ይገባል፡፡ ይህ ሰነድ የተዘጋጀውም ክፍተቱን በመሙላት በኩል የሚጠበቀውን ስራ ለማስጀመር ያህል ነው፡፡ ሰነዱ በአሁኑ ወቅት እንዲዘጋጅ ያደረገው የወዲያው ምክንያት ደግሞ በሃገራችን በቅርቡ እንደሚካሄድ የሚነገርለት የምክክር መድረክ ላይ የአማራ ሃይሎች የሚወክሉት ተደራዳሪዎች የአማራ ህዝብ ያለበትን ችግር ግዝፈት ለማጤንና ችግሮቹን ለመፍታት ከሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ለመደራደር የሚረዱ መነሻ ሃሳቦችን ለመጠቆም ነው፡፡

2. የሰነዱ አስፈላጊነት

በሃገራችን ዘውግ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ተሰጥቶት የፖለቲካችን ዋነኛ ማጠንጠኛ ከተደረገ ከሰላሳ አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡የዘውግ ፖለቲካው ዋነኛ መሰረት ደግሞ 'የአማራ ዘውግ ሌሎችን ዘውጎች ጨቁኗል' የሚል እሳቤ ነው፡፡ በመሆኑም የአማራ ህዝብ እና የአማራ ማንነት አላቸው የሚባሉ ምልክቶች ሁሉ ለአደገኛ የህልውና አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ የአማራ ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደልና ደክሞ ያፈራውን ንብረቱን እንዲያጣ ሆኗል፣ የማንነቱ መገለጫ የተባሉ ባህሎቹ እንዲጣጣሉ፣ እንዲወድሙና ቀጣይነታቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የአማራ ህዝብ በማንነቱ የመጣበትን አደገኛ ፈተና በማንነቱ ተደራጅቶ ሳይመክት ረዥም ዘመናትን አሳልፏል፡፡ በዚህም ምክንያት በአማራው ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ አደገኛ ትርክቶችን ተከትለው የሚከሰቱ አሰቃቂ ጥቃቶች የሚመከቱበት የተደራጀ ስትራቴጂ ሳይነደፍ ቆይቷል፡፡

አማራው ተጠቂ የሆነባቸው መንገዶች ፈርጀ ብዙ ቢሆኑም የአማራ ህዝብ ከእነዚህ ጥቃቶች የሚድንበትን መንገድ መተለም ቀርቶ በዘውግ በተደራጀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማራውን እንደ አንድ ዘውግ ወስዶ ከዘውጉ ጋር በተገናኘ የሚደርሱበት አሰቃቂ በደሎችን ለማስቆም የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ሰንዶ ማቀረቡ በአማራ ሊሂቃን ዘንድ በቅጡ ያልተሰራበት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በጣም ዘግይተውም ቢሆን በአማራው ስም የተደራጁ የተለያዩ ድርጅቶች ከልዩነታቸው ባሻገር ለአማራ ህዝብ በመቆማቸው ሳቢያ የህዝባቸውን ፋታ የማይሰጥ አንገብጋቢ መከራ ለማቃለል ሲባል የሚጋሯቸውን የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎች አጠናቅረው ለማቅረብ የሚችሉበትን መድረክ መፍጠር አልቻሉም፡፡

በተቃራኒው አማራው በድሎናል የሚሉት ወገኖች ከአንድ ዘውግ ሳይሆኑ እንኳን አማራውን በተመለከተ በጋራ የሚያቆማቸው በርካታ አጀንዳዎችን በፍጥነት ማቅረብ የሚችሉበት መግባባት ላይ ከደረሱ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ በአማራው እና "አማራው በድሎናል" በሚለው ልሂቅ መካከል ያለው ሰፊ የዝግጁነት ልዩነት የአማራን ህዝብ ፈተና የሚያከብድ ብቻ ሳይሆን መከራውን እያባባሰ የሚያራዝም አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ ይህን ለማስቀረት በተለያየ ስም የሚጠሩ የአማራ ሃይሎች ከልዩነታቸው ባሻገር ቢያንስ የአማራ ህዝብን ህልውና ለማስቀጠልና እንደ ሰው ሊከበሩለት የሚገቡትን ሰብዓዊ መብቶቹን ለማስከበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሚይዙት የጋራ አቋም ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሰነድ ያስፈለገውም የአማራ ህዝብን ህልውና ለማስከበር በአማራ ሃይሎች መሃከል ሊኖር የሚገባውን የጋራ አቋም ሊያመጡ የሚችሉ የጋራ የመታገያ አጀንዳዎች እና ከተለያዩ ሃይሎች ጋር ለመደራደር የሚስችሉ ነጥቦችን ለመጠቆም ነው፡፡ በሃገራችን በቅርቡ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች የሚሳትፍ ሃገራዊ ምክክር እንደሚደረግ መንግስት ይፋ ማድረጉ ደግሞ የዚህን ሰነድ አስፈላጊነት አስቸኳይ ያደርገዋል፡፡

3. የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ አብዮተኞች ዕይታ - ከትናንት እስከ ዛሬ

ኢትዮጵያ ረዥሙን የታሪኳን ዘመን ያሳለፈችው በዘውዳዊ አስተዳደር ስርዓት ስር ነው፡፡ ዘውዳዊውን አስተዳደር ለመገርሰስም ሆነ ከዛ በኋላ የመጡ ስርዓቶችን ለመቀየር ግብታዊ አብዮቶች፣ ተራዛሚ የትጥቅና ሰላማዊ ትግሎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህን ትግሎች የመሩ አብዮተኞችና ተከታዮቻቸው የሚታገሉትን ስርዓት በደሎች ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከአማራ ህዝብ/ዘውግና ከአማራ ማንነት ጋር ያቆራኛሉ፡፡2እነዚህ አብዮተኞች የኋላ ኋላ ራሳቸውን ሻዕብያ፣ ህወሃት፣ ኦነግ፣ ኦብነግ ወዘተ አይነት ግልፅ የዘውግ ብሄረተኝነት ቀይረዋል፡፡ የተቀሩት እንደ መኢሶ፣ ኢሰፓ፣ ኢህአፓ፣ ኢጭአህአት፣ ወዝሊግ ወዘተ ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያዊ ምልከታ ያለው ፓርቲ ይዘው ተጉዘዋል፡፡ ሆኖም በሁለቱም ጎራ ያሉ ታጋዮች ይነስም ይብዛ ኢትዮጵያ በፊውዳሉ ዘመን ያለፈችበት ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ በአንድም በሌላ መንገድ ከአማራ ህዝብ ጋር ያገናኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ላለፈችበት ሁለንተናዊ ችግር አማራውን ሃላፊ አድርጎ የማቅረቡ አካሄድ በማታገያ ርዕዮትነት ድምፀት ሲገለፅ "በሃገራችን የብሄር ጭቆና፣ የተዛባ የብሄረሰቦች ግንኙነት ነበር" የሚል ተደርጎ ይቀርባል፡፡ እዚህ ላይ ጨቋኝ ሆኖ የቀረበው የአማራ ዘውግ ሲሆን ተጨቋኙ ደግሞ የተቀሩት የኢትዮጵያ ዘውጎች ናቸው፡፡ አሁን ላይ የአማራ ዘውግ ተወላጆችን ከኢትዮጵያ ዳርቻ ሁሉ የሚያሳድደው አማራ-ጠል ትርክት ውልደቱ ይህ እሳቤ ነው፡፡

የዚህ አማራ-ጠል ትርክት መሃንዲስ ደግሞ አማራው ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡ በእርግጥ የአማራ-ጠል የዘውግ ብሄርተኝትን በኢትዮጵያ ያስጀመረችው በአፄ ምኒልክ መሪነት አሳፋሪ የሸንፈት ማቅን የተከናነበችው ጣሊያን ነች፡፡ 3 ሆኖም በፋሽስት ኢጣሊያን የተጀመረውን አማራን የማጠልሸት ደብዛዛ ጅማሮ በፅሁፍ አጠናቅሮ ለነጥቆ በረሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ማፋፋሚያነት ያቀረበው ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡ ዋለልኝ "On the Question of Nationalities in Ethiopia" በሚል ርዕስ የፃፈው ባለ አምስት ገፅ ፅሁፍ የኢትዮጵያን ድህረ-ዘመናዊ ፖለቲካ በመዘወሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

ዋለልኝ በዚህ ሰነዱ በአብዛኛው የአማራን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የትግሬ ዘውግ የተቀሩትን ኢትዮጵያዊያንን በሁለንተናዊ መልኩ በመጨቆንና በመደፍጠጥ ይከስሳል፡፡ ሁለቱ ጨቋኝ እና ደፍጣጭ ብሄሮች ዋናና ምክትል ሆነው የራሳቸውን ባህል፣ ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የበላይነታቸውን እንደተቀደጁ ይገልፃል፡፡ ይህ ሰነድ ራሱ ፀሃፊው በመንደርደሪያው እንዳመነው በርካታ እንከኖች ያሉበት፣ በቅጡ ያልተብላሉ ችኩል ማጠቃለሎች የሞሉበት፣ ያነሳውን ሃሳብ ውስብስብነት የሚመጥን በቂ/በሳል ትንታኔ ያልተደረገበት፣ ተጨባጭ መንደርደሪያዎችን አስቀድሞ ያላመጣ፣ የይድረስ ይደረስ የተፃፈ ሰነድ ነው፡፡

የዋለልኝ ሰነድ ራሱ ፀሃፊው ያመነው በርካታ ውስንነቶች ያሉት ሆኖ ሳለ የሃገራችንን ፖለቲካ በመዘወሩ ረገድ እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ግዙፍ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከሰነዱ ዋነኛ ውስንነቶች አንዱ በተደጋጋሚ በጨቋኝነት የሚያነሳው የአማራ ዘውግ የተባለው ማን እንደሆነ እንኳን ግልፅ ትርጉም አላስቀመጠም፡፡በጨቋኝነት ፈርጆ ያስቀመጠው አማራ "አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነው" ከማለቱና ሸዋ የሚለውን ቃል በአሻሚ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ ከማሰቀመጡ በቀር ቢያስ በእሱ ፅሁፍ ሁኔታ አማራ የተባለው ዘውግ የሚኖርበትን ቦታ ጨምሮ ሌሎች በአማራነት የሚያስፈርጁ መገለጫዎችን አላስቀመጠም፡፡

ዋለልኝ በሰነዱ "ኢትዮጵያዊነት ማለት አማርኛ በመናገር ይገለፃል" ሲል ያስቀመጠ ሲሆን በእርሱ አገላለፅ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ የማይችለው አማርኛ ተናጋሪ የሃገሪቱ ህዝብ ሁሉ እርሱ ጨቋኝ ነው በሚለው አማራ ዘውግ ውስጥ ይግባ አይግባ ግልፅ አይደለም፡፡ አማራነትን በሃይማኖታዊ ገፁ ሊገልፅበት በሞከረው ትንታኔው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ለአማራ የሰጠበት ትንታኔውም እንዲሁ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን የሚከተል ሁሉ አማራ ሊባል ይችላል ወይ የሚል ተመሳሳይ ጥያቄን የሚያስነሳ ነው፡፡ አማራነትን የኦርቶክስ ሃይማኖትን በመከተል፣ አማርኛ ቋንቋን በመናገር፣ ሸማ በመልበስ አይነት ከመወለድ በኋላ በሚለመዱ ባህላዊ ገፅታዎች ሲገልፅ የቆየው ዋለልኝ በመሃል ደግሞ "አማራ ሆኖ መወለድ እንደ መባረክ ይቆጠራል" ሲል5 አማራነትን ከዘረመል ጋር የሚገናኝ፣በውልደት የሚገኝ ስነፍጥረታዊ ማንነት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡

በተጨማሪም ከአማራው ጎን ጨቋኝ አድርጎ ያቀረበው የትግሬ ዘውግ በቋንቋ ረገድ በቀዳሚነት ትግርኛን እንጅ አማርኛን የሚናገር አይደለምና ኢትዮጵያዊነት ማለት አማራ ሆኖ አማርኛ ከመናገር ጋር ካቆራኘው ትንታኔው ጋር የትግሬ ዘውግ ቦታ የት እንደሆነ ግልፅ እይደለም፡፡ የኋላ ኋላ ደግሞ ትግሬ ከአማራ ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን ብሄረሰቦች ጨፍልቆ ባህሉን ጫነባቸው ማለቱን ረስቶት ኢትዮጵያዊ ለመባል የአማራ ጭምብል (Mask) ማጥለቅ ግድ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሁኔታ ትግሬነት ቦታው የት እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

የዋለልኝ ሰነድ የፅሁፉ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውን አማራ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ትርጉም በግልፅ ለማስቀም እንኳን ጊዜ ያልወሰደ በርካታ ህፀጾች የተሞላ ቢሆንም ሰነዱ የያዛቸው ስሁት ሃሳቦች ከዋለልኝ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ የተነሱ ታጋዮችን ልብ መግዛት ችሏል፤የትግል ፍኖተ ካርታ፣የማታገያ ማኒፌስቶ የሚቀዳበት "ሰፊ ምንጭ" ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የዋለልኝን ሰነድ በተንተራሱ እንደ ትህነግ፣ ሻዕብያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ ወዘተ ያሉ አብዮተኞች እሳቤ መሰረት የዘውዱ ስርዓት ሙሉ በሙሉ የሚዘወረው የአማራ ማንነት ብቻ ባላቸው መሪዎች አለያም ዘውጋዊ ማንነታቸውን ለአማራ አሳልፈው በሰጡ ሌሎች መሆኑ ለጥርጣሬ ቦታ ሳይጠው የሚታመን "ሃቅ" ነው፡፡

ነገሩ ሲብስ ደግሞ ከዘውዱ ስርዓት በኋላ የመጣውን የደርግ ስርዓት ራሱ የአማራ ስርዓት እንደሆነ እርግጠኛ ሆነው ይናገራሉ፡፡ስለዚህ በዘውዱም ሆነ በወታደራዊው ስርዓት "ተከፋንበት" የሚሉትን ጥፋት ሁሉ ለአማራ ህዝብ በዕዳነት ያሸከማሉ፡፡ እነዚህ አብዮተኞች አንዳንዴ ለይስሙላ "የአማራ ህዝብ" እና "የአማራ ገዥ መደብ" የሚል ነገር የሚያነሱበትና ፀባቸው እና ትግላቸው ከአማራ ገዥ መደብ እንጅ ከአማራ ህዝብ ጋር እንዳልሆነ የሚናገሩበት አጋጣሚ አለ፡፡

ከዋለልኝ ደቀመዛሙርት ውስጥ ኮስተር ያለ የትጥቅ ትግል አድርጎ ስልጣን ለመያዝ የበቃው ትህነግ የትጥቅ ትግሉን ሲጀምር "ጠላቴ ጨቋኟ የአማራ ብሄር ነች" ሲል የዋለልኝን ስብከት ከፍሎ የማመን መናፍቅነት ውስጥ ገባ፡፡ ህወሃት የዋለልኝ ደቀመዝሙር መሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም ራሱ የወጣበትን የትግሬ ዘውግ ከጨቋኝነት ከመርገም ለማዳን ሲል ከዋለልኝ እውቀት ላይ ከፍሎ ማወቅን መረጠ፡፡በመሆኑም የአማራ ዘውግን በብቸኛ ጨቋኝነት ፈርጆ የትግሬ ዘውግን በአማራ ጨቋኝነት የሚማቅቅ ዘውግ አድርጎ፣ የዋለልኝን አስተምህሮ ለራሱ በሚጠቅመው መንገድ ከልሶ የትግል ማኒፌስቶ በመፃፍ7 ተራዛሚውን የትጥቅ ትግል አሃዱ አለ፡፡

የዋለልኝን አማራ-ጠል አስተምህሮ አንግቦ ወደ ትጥቅ ትግል የገባው ትህነግ የትጥቅ ትግሉን በድል አጠናቆ ቤተ-መንግስት በመግባቱ የዋለልኝ አስተምህሮ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መንፈስ ሆኖ ዛሬ ድረስ አማራውን እንዲያሳድድ አድርጓል፡፡ ትህነግ ክንዱ የሚችለውን ያህል ደቁሶ በሃይል ከገዛ በኋላ "ብሄር ብሄረሰቦች" ሲል በሰየማቸው ደቀመዛሙርቱ ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም ቢሆን የዋለልኝ መንፈስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በከፍታ ተቀምጦ አማራውን ማሳደዱን ቀጥሏል፡፡

ትህነግም ሆነ ከእርሱ በኋላ ስልጣን የያዙ ደቀመዛሙርቱ በለስ ቀንቷቸው ስልጣን ሲይዙ ፀባቸው እነሱ አማራ ብለው ከፈረጁት ፍጡር እና የአማራ ምልክት ካሉት ጉዳይ ጋር ሁሉ መሆኑን በአማራው ዘወግ ተወላጆች ላይ የሚወስዱት ዘር ማጥፋትን የጨመረ እርምጃ ምስክር ነው፡፡ እነዚህ አማራ በደለን ብለው የተነሱ አብዮተኞች "ኢትዮጵያ ራሷ የአማራ የእጅ ስራ ነች"ብለው ያምናሉ፡፡ስለሆነም በአማራ በኩል ኢትዮጵያን ራሷን ይታገሏታል፡፡ ትግላቸው ኢትዮጵያን ራሷን አፈራርሶ ወደ ብሄረሰቦች ቅርጫነት ሊቀይራት እንደሚችል ማጤንም አይፈልጉም፡፡ቢያጤኑ እንኳን የኢትዮጵያ መፍረስ አለመፍረስ የሰሪዋ የአማራ ብቻ ራስምታት እንደሆነ ያምናሉና የሚያሰጨንቃቸው ጉዳይ አይደለም፡፡

ከአማራ ጋር ያለን ግንኙነት የጨቋኝ ተጨቋን ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት የአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ሰልፈኞች አማራው ይፈልገዋል ብለው ለሚያስቡት ነገር ሁሉ ጠላትነትን ያሳያሉ-ለኢትዮጵያም ጭምር፡፡በአጭሩ በአማራ በኩል ኢትዮጵያን ይጣላሉ፡፡የሚጠሏትን ኢትዮጵያ ለማፍረስ እንደሚሰሩ በግልፅ ሲናገሩም ኖረዋል፡፡ሆኖም እነዚህ ወገኖች በትህነግ በኩል ስልጣን ላይ የመውጣት እድል ሲያገኙ ደግሞ ኢትዮጵያን ከማፍረስ ይልቅ አማራ ቀደም ብሎ ከሰራት የተለየ አድርጎ ሰርቶ መግዛቱ የበለጠ ተመራጭ እንደሆነ አምነው ይህንኑ ሲያደርጉ ኖረዋል፡አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህን ሃሳብ በዕለት ተዕለት ፖለቲካዊ ንግግራቸው ውስጥ አስገብተው ሲገልፁትም 'ከአሁን በኋላ የድሮዋ ኢትዮጵያ ተመልሳ አትመጣም' ይላሉ፡፡ በዚህ አባባል ውስጥ በርካታ ሃሳቦችና ፍላጎቶች አድፍጠዋል፡፡

የመጀመሪያው እሳቤ የድሮዋ ኢትዮጵያ አማራ ለራሱ ጨቋኝነት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ባህላዊ የበላይነት እንድትመች አድርጎ የሰራት፤ ለአማራ ብቻ የምትመች ነች የሚል ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሃሳብ ይህች አይነቷ ኢትዮጵያ ፈርሳ ስትሰራ የቀድሞዋን ኢትዮጵያን ሰርቷል ብለው የሚያምኑትን አማራን በሚበቀል፣ በሚያገል እና በሚቀጣ መንገድ መሰራት አለባት የሚል ነው፡፡ይህ አፍርሶ የመስራቱ አካሄድ በተለያየ መንገድ የሚገለፅ ሲሆን ዋና ዋናዎቸ አማራውን ከመላ ሃገሪቱ በማሳደድ፣ የአማራን ዘር በማፅዳት/በማጥፋት፣የአማራ ተብለው የተፈረጁ መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሃብቶችን በማጣጣል/በማቃለል/በማውደም እንዲሁም አማራውን ከዋነኛ የፖለቲካ ስልጣን በማግለል ይገለፃሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ አማራ ኢትዮጵያን የመስራቱ ምልክቶች ናቸው የሚሏቸውን አማዳት ሁሉ አጥፍተው የሚፈልጓትን አይነት ኢትዮጵያ መስራታቸው ነው፡፡

አሮጌዋን ኢትዮጵያ አፍርሶ አዲሷን ኢትዮጵያ የመገንባቱ ፕሮጀክት ከ1983ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ የቀጠለ ነው፡፡አዲስ በመሰራት ላይ የምትገኘዋ አዲሲቷ ኢትዮጵያ አይነተኛ መልኳ ደግሞ ለአማራው የማትመች ይልቅስ አማራውን ለመቅጣት ታስባ የተሰራች መሆኗ ነው፡፡ለዚህ በርካታ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡የመጀመሪያው ከ1983ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ በዘለቀ ሁኔታ በበደኖ ፣ በወለጋ ፣ በቤኒሻንጉል ፣ በጉራፈርዳ ወዘተ አማራው በማንነቱ ተለይቶ የዘር ማጥፋት/ማፅዳት ወንጀሎች እየተፈፀሙበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም፤ ሌላው ቀርቶ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት የአቶ ጃዋር መሃመድን የተከበብኩ ጥሪ አይነት ድንገቴ ክስተቶችን ተከትሎ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አማራው በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደለ ቢሆንም ይህን ወንጀል የሚመረምር አንድም የወንጀል ፋይል ተከፍቶ የተጠየቀ አካል የለም፡፡ በፍርድ ቤት መጠየቅ ቀርቶ በሞራል ህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ጠበቅ ያለ ውግዘት ከሃይማኖት ተቋማት እንኳን ተሰምቶ አያውቅም፡፡

ይህን አይነቱ የዘር ማጥፋትን ለሚያክል ወንጀል የሚሰጠው የዝምታ መልስ "በአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስራቾች" እሳቤ መሰረት በአማራው ላይ የሚደረገው ማንኛውም ወንጀል ለተዛባው የታሪክ ማስተካከያነት የሚደረግ በጎ እርምጃ ተደርጎ የሚተረጎም መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ በተመሳሳይ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስራቾች እሳቤ "የአማራ ሃይማኖት" ተደርጋ በምትወሰደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የሚደረገው ህገ-መንግስቱን ጭምር የጣሰ ወንጀል በመንግስት በኩል በዝምታ የሚታለፍ ነው፡፡

በተመሳሳይ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመስራት በሚጥሩ አካላት እሳቤ የአማራ ሃይማኖት ተብላ የተፈረጀችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የማይደርስ በህይወት የመኖር መብታቸውን ከመንጠቅ፣ የማምለክ መብታቸውን ጥያቄ ውስጥ እስከማስገባት የደረሰ ወንጀል ይፈፀምባቸዋል፡፡ ይህ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግስት ሹማምንት ሳይቀሩ የሚሳተፉበት ነው፡፡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ የቤተክርስቲያኗ አማኞች "የአማራ/ነፍጠኛ ሃይማኖት ተከታዮች" በሚል በሃይማኖታቸው ተለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡

ይህ ሲሆን የመንግስት ባለስልጣናት በተገቢው ሁኔታ ሃላፊነታቸውን በሚመጥን መንገድ ተንቀሳቅሰው የምዕመናኑን ህይወት ለማትረፍ እንዳልሰሩ በመንግስት ስር ያለው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር በሪፖርቱ ያመላከተው ጉዳይ ነው፡፡ በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ የሃዲያ ዞን መቀመጫ በሆነችው ሆሳዕና ከተማ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች የጥምቀት በዓልን የሚያከብሩበት ቦታ አጥተው ሲቸገሩ የመንግስት ባለስልጣናት እስከ ዘንድሮው ጥምቀት በዓል ድረስ የረዷቸው አልነበረም፤ ከማስፈራራት እና አባቶችን ከማቃለል በቀር፡፡ በዘንድሮው ጥምቀት ከብዙ ዘመን ደጅ ጥናትና እንግልት በኋላ ቤተ-ክርስቲያኒቱ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ አግኝታለች፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሚያሳየው የቀድሞዋን ኢትዮጵያ የአማራ የእጅ ስራ ስለሆነች አፍርሰን እንሰራለን የሚለው እሳቤ ሊፈጥራት እየጀማመራት ያለችው ኢትዮጵያ አማራ-ጠል መልኳ የበዛ መሆኑን ነው፡፡

ኢትዮጵያን አፍርሶ የመስራቱ እሳቤ ሁለት ስህተቶችን አጣምሮ የያዘ አካሄድ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስህተት ከ1983 በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ለአማራው ብቻ እንደ እናት ማህፀን የምትመች አድርጎ የማሰቡ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ይህች ኢትዮጵያ ለአማራው ብቻ የምትመች አለመሆኗን ለማወቅ ቀላሉ መንገድ ወደ አማራ ክልል ጎራ ብሎ ህዝቡ የሚኖርበትን የድህነት ልክ መመልከት ነው፡፡ ሁለተኛው ስሁት እሳቤ አማራን የምትቀጣ አዲስ ኢትዮጵያ ስትፈጠር አማራው ዝም ብሎ ያያልና በዚህ መልክ የታሪክ ስህተት ለማስተካከል ይቻላል ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፈርሳ መስራት ካለባት እንኳን መሰራት ያለባት ሁሉንም እኩል አድርጋ እንድታስተናግድ ተደርጎ እንጅ በአንድ ብሄር ላይ የምትዘምት ኢትዮጵያን መስርቶ ሃገር አድርጎ መኖርን ማሰብ የማያስኬድ መንገድ ነው፡፡

4. ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት፣ የዘውግ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ መስተጋብር

የዘውግ ማንነት እንደ ማህበራዊ ክስተት ከጥንት ግሪኮችና ሮማዊያን ዘመን ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ፖለቲካዊ ሆኖ በዓለማችንም ሆነ በአህጉራችን አፍሪካ የፖለቲካ ስልጣን መያዣ መሳሪያ የሆነው ግን በጣም በቅርቡ ማለትም በ20ኛው ክፍለዘመን መባቻ ነው፡፡8ይህ በርካታ የዓለማችን ምሁራን የተስማሙበት ሃቅ ቢሆንም በሃገራችን የዘውግ ፖለቲከኞች ዘንድ ግን ኢትዮጵያ ከተፈጠረችበት ዘመን ጀምሮ አማራ በዘውግ ማንነቱ ተደራጅቶ ሌሎችን ዘውጎች እየጨቆነ ሲገዛባት የኖረች ተደርጎ ብያኔ ይሰጣል፡፡ ይህ ስሁት ብያኔ ኢትዮጰያን የተቀሩት የዓለም ሃገራት ካለፉበት የታሪክ ምዕራፍ የተለየ የፖለቲካ ቀመር ያላት ሃገር አድርጎ ያስባል፡፡ ከዚህ አልፎ ይህ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የአማራ የበላይነት/ትምክህተኝነት ሌሎችን ለመጨቆን ሲል ራሱን የሚደብቅበት ጎሬ አድርጎ እስከ ማሰብ ይዘልቃል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን መዋጋት አማራን መዋጋት፤ በግልባጩ አማራን ማሳደድ፣ ማሸማቀቅ እና ከሃገራዊ ፖለቲካ ስዕሉ ገሸሽ እንዲል ማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማፈራረስ አድርገው ያስባሉ፤ለዚሁም ይሰራሉ፡፡ በአጭር አገላለፅ አማራውን በማሳደድ ኢትዮጵያዊ ብሄርኝነትን ይዋጋሉ፤ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት በማፈራረስ አማራውን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ገሸሽ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ Read more, 63 pages, pdf