"ኢትዮጵያ የከሸፈች ሀገር እየሆነች ነው" ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ
10 ሚያዚያ 2019 አሁን ምይ ይል ይሆን?
በደርግ ስርዓት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ "ኢትዮጵያ በቀውስ አፋፍ ላይ ናት" የሚል ጽሑፍ ፅፈው በተለያዩ ድረ ገፆችና በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ነበር። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሻለቃ ዳዊት የጽሑፋቸው አላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማስረዳት እንደሆነ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ እየወደቀች ነውም ብለዋል።
ሻለቃ ዳዊት፡ የጽሁፌ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማስረዳት ነው። በሃገሪቱ የሚከናወኑ ብዙ ነገሮች ስላሉ ህዝቡ ተወጥሮ ያለው በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ላይ ነው። እነዚህ ሁሉ ግን ተደምረው በጠቅላላ የሃገሪቱ ስእል ምን ይመስላል የሚለውን ለማሳወቅ ነው የፈለግኩት። እናም በደህንነት ረገድ፣ በኢኮኖሚና በአጠቃላይ በአመራር ደረጃ ያለውን ስንመረምረው ጠቅላላ ኢትዮጵያ የከሸፈች ሃገር ( failed state) ወይም ከቁጥጥር ውጪ የሆነች አፍሪካዊ ሃገር እየሆነች ነው። ቁጥሮቹን በሙሉ ጽሁፌ ላይ አስቀምጫለው።
እኔ ያደረግኩት በሜዳ ላይ የሚታዩትን ሃቆች አውጥቶና ስእሉ ሲደመር የኢትዮጵያ አቅጣጫ ምን ይመስላል? የሚለውን ለመመለስ ነው የሞከርኩት። አቅጣጫው አደገኛ አቅጣጫ ነው። አመራሩ አስፈላጊና ከባድ ውሳኔ ካልወሰነ በስተቀር አዘቅት ውስጥ ገብታ ምናልባትም የእርስ በርስ ጦርነት ሊያመጣ የሚችል ሁኔታ ይፈጠራል። ይህንን ለማስቀረት መደረግ ስለላባቸው ነገሮችም ጠቁሜያለው።
ምናልባት መደረግ ያለባቸው ነገሮች አስቸጋሪና ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በከባድና አስቸጋሪ ጊዜ ከባድና አስቸጋሪ ውሳኔ መወሰን ያስፈልጋል። በእንደዚህ አይነት ጊዜ ያሉ አመራሮችም መጥፎ ሁኔታ ላይ እንዳለን ሲያውቁ መደረግ ያለበት ውሳኔ መራራ ሆኖ፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያድን ይሆናል እንጂ ስለፍቅር በመናገርና ህዝቡን በማባበል፤ ተስፋ በመስጠት ያጋጠመንን ችግር መፍታት አይቻልም ለማለት ነው።
ሃገሪቱ አዲሱ አስተዳደር ከመምጣቱ በፊት ከነበረው የባሰ ሁኔታ ውስጥ ናት ማለት ይቻላል?
ሻለቃ ዳዊት፡ አዎ፤ በጣም እንጂ፤ በትክክል። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን በመፈናቀል ደረጃ የወሰድን እንደሆነ፤ ድሮም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመምጣታቸው በፊትም ነበረ። አሁን ግን በጠቅላላው በጣም እየባሰ መጥቶ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ በሚባል ደረጃ ብዙ ሰው የተፈናቀለባት ሃገር ኢትዮጵያ ናት። እስከ አራት ሚሊየን ህዝብ ተፈናቅሏል።
በጠቅላላው ደግሞ የሃገሪቱ የደህንነት ሁኔታ ስንመለከት አንድ ሃገር ውስጥ በነጻነት መንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ደግሞ የሚፈጠሩት እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ማዕከላዊ አፍሪካ ባሉ የከሸፉ ሃገራት ነው።
በግለሰብ ደረጃ ስንመለከተው ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በስጋት ነው የሚኖረው። ሲወጣም ሆነ ሲገባ በስጋት ውስጥ ሆኖ ነው። የኢኮኖሚውን ዘርፍ ያየነው እንደሆነ ሌላው ቀርቶ መድሃኒትና ነዳጅ ለመግዛት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ብቻ እንጂ ከዚያ ውጪ ባንክ ውስጥ ምንም መጠባበቂያ እንደሌለ ብሔራዊ ባንክ ተናግሯል።
• ሕዝብ ስለመሪው ምን እንደሚያስብ እንዴት እንወቅ?
ከዚህ በተጨማሪ አሁን እያስተዋልነው ያለነው መሰዳደብና መዘላለፍ በህዝብ መሃል ያለውን ተቃርኖ እያባባሰው ሄዷል። ይሄ ሁሉ የአመራርና የፖሊሲ ጉዳይ ነው። አመራርና ፖሊሲ እስካልተቀየረ ድረስ ይሄ ሊለወጥ አይችልም። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ሃገሪቱ በእኔ እድሜ በኃይለስላሴም፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ እንደዚህ አይነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሳ አታውቅም።
Continue reading https://www.bbc.com/amharic/news-47879359