ዛሬም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች! ለምን? እንዴትና በምን?
ይበል ካሳ(Josef Kassa) from Ethiopian Press Agency
ሐቅን እንደ መግቢያና መግባቢያ
ኢትዮጵያ ከፍ ሲል ከአዳም ዝቅ ሲል ከኖህ፣ በጣም ዝቅ ሲል ደግሞ ከሰብታህ የሚጀምር፤ ከራሱ ከሰው ልጅ ዕድሜ እኩል የሚቆጠር የረጅም ዘመን የሃገርነትና መንግስትነት ታሪክ ያላት ጥንታዊ ሃገር ናት-ሐቅ፡፡ ከማንም ቀድማ ለዓለም የስልጣኔ እርሾን የጣለች፣ የራሷ የሆነ ወግ፣ ባህልና ስልጣኔ ያላት፤ በፍትሕና በእኩልነት የምታምን፣ ከሁሉም ጋር በመከባበርና በመተባበር መኖርን የምትመርጥ፣ በፍቅርና በትህትና እንጅ በእብሪት ተሸንፋ የማታውቅ ሃገር ናት ኢትዮጵያ-ሐቅ፡፡ ብትጎለብት በኃይሏ የማትመካ፣ ደካማን ለማገዝ እንጅ ለማዘዝ ክንዷን የማታነሳ፣ አልፋ የማትነካ አልፎ ለመጣባት ደግሞ ክብሯን የማታስነካ፣ በኃይል ሌላውን ወርራ የማታውቅ ኃይል አለኝ ብሎ ሊወራት የመጣ ወራሪን ደግሞ አሸንፋ እንጅ ተሸንፋ የማታውቅ ታላቅ ሃገር ና ኢትዮጵያ-ሐቅ፡፡ በመሆኑም በገዛ ክንዷ ለዘላለም ነጻነቷን አስከብራ በክብር የኖረች፣ አብዛኛው ታሪኳ በአስደናቂ የጀግንነትና የክብር መዝገብ የተሞላ በዚህም ከዜጎቿ አልፋ በዓለም ሁሉ የታወቀች ታላቅ ሃገር ናት ኢትዮጵያ-በሁሉም ዘንድ የታወቀ ገዥወ ሐቅ ይኼ ነው!
ክብርና ዝናው ተከፍሎበታል
ታዲያ ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም ዙሪያ እንዲህ በክብር፣ በኩራት፣ በጀግንነት መታወቅ የቻለው ከምን ተነስቶ ነው? ይህ ስምና ዝና እንዲሁ ዝም ተብሎ የተገኘ ነውን? እርሷ ስለፈለገች ነው በዚህ ስምና ዝና በዓለም ዙሪያ የታወቀችው? ወይንስ የዓለም ህዝብ በችሮታ ሰጥቷት ይሆን? ሁሉም አይደለም፡፡ የክብር፣ የኩራት፣ የጀግንነት ስሟ ዝም ተብሎ የተገኘ አይደለም፣ የዓለም ህዝብ በችሮታ የሰጣትም አይደለም፡፡ ይህ ስምና ዝና በምኞት ሳይሆን በሥራ የመጣ፣ በተግባር የተፈጸመ፣ በመፈለግ ሳይሆን በመሆን የተገኘ እውነተኛ ስም ነው፡፡ ይህ ስምና ዝና፣ ይህ አኩሪ የጀግንነትና የክብር ታሪክ እንዲሁ በቀላል ሳይሆን ውድ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘ ነው፡፡ ምክንያተቱም በአንድ ነገር ላይ ከራስ አልፎ በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ድርጊቱ በተግባር ተደርጎ፣ አድራጊውም አስመስሎ ሳይሆን ድርጊቱን በተግባር ፈጽሞ፣ በሃሳብ ሳይሆን በተግባር ሆኖ መገኘት አለበትና፡፡ እናም የሃገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ስምና ዝና የእኛም የልጆቿ የክብር፣ የኩራት፣ የጀግንነት ስማችን ዝም ተብሎ የተገኘ አይደለም፣ የዓለም ህዝብ በችሮታ የሰጠንም አይደለም፡፡ የምንኮራውና የምንከበረው በከንቱ መከበርና መወደስ ስለምንፈልግ አይደለም፡፡
ታላቋ ሃገራችን ኢትዮጵያና እኛ ኢትዮጵያውን በጀግንነታችንና በኩሩነታችን በዓለም ህዝብ ዘንድ የታወቅነው የጀግንነትን ጠባይ በገቢር ገልጠን፣ የሚያኮራ ምግባር ፈጽመን በእርግጥም ኩሩ ሆነን ስለተገኘን ነው፡፡ በምኞት ሳይሆን በተግባር አድርገው፣ ተመችቷቸውና ሁሉም አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ሳይሆን የሚገጥማቸውን ፈተና ሁሉ ፊት ለፊት በጽናት በመጋፈጥ በእሳት ተፈትነው አልፈው፣ ከሌላ አካል በመጠበቅ ሳይሆን እንዲሆንላቸውና እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ሁሉ በራሳቸው አድርገው፣ ከኋላ ሆኖ በመከላከል ሳይሆን ከፊት እየቀደሙ በመዋደቅ አባቶቻችንና እናቶቻችን በሠሩት አኩሪ ታሪክ ነው በታወቅንበት ስም መታወቅ የቻልነው፡፡ በፈጸሙት አኩሪ የጀግንነት ገድል፣ በየዘርፉ ባስመዘገቡት ዘመን አይሽሬ ድል፣ በወርቅ ቀለም ጽፈው ባወረሱን ታሪክ የማይሽረው አኩሪ ጀግንነት፣ በሥራ ተጽፎ በድርጊት ታትሞ በተሰጠን ሕያው የታሪክ መጽሐፍ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በጀግንነትና በኩሩነት በዓለም ላይ ልንታወቅ የቻልነው፡፡ አባቶቻችንና እናቶቻችን በተግባር ሠርተው፣ ተከብረው ስላስከበሩን፣ ኮርተው ስላኮሩን ነው በታወቅንበት የክብርና የጀግንነት ስም መታወቅ የቻልነው፡፡ ጥበብን ከጀግንነት አዋህደው ታላቅ ሃገርን የፈጠሩ፣ የመሩና ያወረሱን ጀግኖች እናትና አባቶቻችን ጀግንነትን በተግባር ፈጽመው፣ ከማንም በላይ ተፈትነው ማንም የማይችለውን ችለው፣ በክብራቸውና በማንነታቸው የመጣባቸውን ሁሉ ድል አድርገው አሸንፈው፣ በእርግጥም የሚያስከብርና የሚያኮራ ታሪከ ሠርተው በማሳየታቸው ነው በክብርና በጀግንነት መታወቅ የቻልነው፡፡
ዛሬም እናሸንፋለን! ለምን?
መውደቅ መነሳት፣ ማግኘት ማጣት፣ መውጣት መውረድ፣ መብለጥ መመበለጥ፣ መቅደም መቅረት፣ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪይ ነው፡፡ ታሪክ ስንልም በዋነኝነት የሰው ልጆችን የሚመለከት ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ ታሪክ በተለያዩ ቦታወች የሚኖሩ የሰው ልጆች በተለያዩ የዘመን ማዕቀፎች ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የግሪክ ታሪክ፣ የአሜሪካ ታሪክ… ወዘተ ስንል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰዎች(የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ)፣ ግሪክ ውስጥ ያሉ ሰዎች(የግሪክ ሕዝብ ታሪክ)፣ የአሜሪካ ሰዎች(ሕዝብ) ታሪክ ማለታችን ነው፡፡ እናም መውጥትና መውረድ፣ መውደቅና መነሳት በግለሰብ ህይወት ብቻ ሳይሆን በሃገራት ታሪክ ውስጥም አለ፡፡ በዚህም በአንድ የዘመን ክፈፍ ውስጥ ኃያል ይባል የነበረ ሃገር በሌላ ዘመን ተመለረሶ ከተራ ተርታው ሃገራት ምድብ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የብዙ ሃገራ ታሪክ በአጠቃላይ የዓለም ታሪክ የሚነግረንም ይህንኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክም ከዚሁ የተለየ አይደለም፤ እርግጥ ነው እንደ ብዙወቹ ሃገራት(ከብዙወችም ቀድማ) ስልጣኔን ጀምራ፣ በስልጣኔ አብባና ጎምርታ፣ ከሁሉም በላይ ከፍ ከፍ ብላ በዕድገት ማማ ላይ በአሁኑ ዘመን ነባራዊ የዕድገትና የልዕልና መለኪያ ስትመዘን በብዙ ወደኋላ መቅረቷ አይካድም፡፡ ይሁን እንጅ ሃገራት እንደ ሃገር፤ ሕዝባቸውም እንደ ሕዝብ በየትኛውም ዘመን ከከፍታቸው የማይወርዱበት የየራሳቸው ዘመን አይሽሬ የታላቅነት መገለጫ፤ የየግላቸው ተፈጥሯዊ የልዕልና ሥሪት አላቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ታሪኳን ስንመረምር በማንኛውም ዘመን የማያስሰው ተፈጥሯዊው የኢትዮጵያ ማንነታዊ ሥሪት ነጻነት ነው፡፡ ከዓለም ኃያላን መካከል አንደኛዋና ቀዳሚዋ በነበረችበት ጊዜ ያኔም፣ ከመጨረሻወቹ መናኛወቹ መካከል ተቀምጣ ዛሬም… ነገም ኢትዮጵያ በነጻነቷ ቅንጣት ከቦታዋ ተንሸራታ አታውቅም፡፡ ለክብሯና ለነጻነቷ ትናንትናም፣ ዛሬም፣ ነገም ሁሌም ኃያል ናት! በዘመኑ የነበሩ ታላላቅ ግዛተ አጼወችን ኃያላን የሚባሉትን ሳይቀር በጦርነት አሸንፎ ያስገበረውና መላውን ዓለም በቁጥጥሩ ሥር አውሎ ለመግዛት ተቃርቦ የነበረው በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በጦረኛነቱ አቻ ያልተገኘለት ታላቁ እስክንድር እንኳን ኢትዮጵያ ሲደርስ ነበር ግስጋሴው የተገታው፡፡ ይህንን በተመለከተ ዕውቁ ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በሚለው መጽሐፉ መግቢያ ላይ የሚከተለውን አሰፍሯል፡፡ “ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል የተደጋገመ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን አገራቸውን በሌላ ባዕድ ሳያሲዙ ባላቸው ኃይል ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ በአውሮፓም ሆነ በእስያ ወይም በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያስፋፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያውን ግን ለማንም ሳይበገሩ ሳይገብሩ እስካሁን አገራችንን አስከብረው ቆይተዋል፡፡
ይህ መጽሐፍ ጨምሮ እንደሚያመለክተው አውሮፓን፣ እስያንና አፍሪካን ጭምር አስገብሮ ይገዛ የነበረው ከታላላቅ የዓለም ኃያላን ነገሥታት መካከል አንዱ የሆነው ዝነኛው የሮማው አውግስቶስ ቄሣርም በ29 ዓመተ ዓለም ላይ ኢትዮጵያን ለማስገበር ከፍተኛ ቁጥር ለው ጦር አዝምቶ ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር መዋጋቱንና በመጨረሻም በኢትዮጵያውያን ተሸንፎ ተመልሷል፡፡ ከከርስቶስ ልደት በኋላ በሮማ የነገሠው በታሪክ እጅግ ጨካኙ ንጉሥ በመባል ሚታወቀው ኔሮም የአውግስቶስ ቄሳር ላይ የደረሰውን ሽንፈት ለመመለስ ከሰማንያ ከሁለት ትውልድ ጊዜ በኋላ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ54 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያ ላይ ጦር አዝምቶ በድጋሜ ድል ሆኖ መመለሱን የእኛን ሳይሆን የራሳቸው የምዕራባውኑን ታሪክ ጸሀፊዎች ዲዮ ካሲዮንና ፕሌኒን ጠቅሶ ጳውሎስ ኖኞ ጽፏል፡፡
ከጥንት ከቅድመ ዓለም ጀምራ እስከ የቅርብ ዘመኖቹ አድዋና የፋሽስት ወረራ ለሦስት ሺሕ ዓመታት በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ ደጋግማ የዘመተችው ኢጣሊያም ያተረፈችው ሽንፈትን፣ ውርደትንና ውድቀትን ብቻ እንደሆነ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጣሊያንም ሆነ አስራ ስድስት ጊዜ ሞክራ አስራ ስድስት ጊዜ በተሸነፈችው ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ፣ በኦቶማን ቱርክም ሆነ በዚያድባሬዋ ሶማሊያ… ክብሯንና ነጻነቷን ለመድፈር በሞከረ ማንኛውም ኃያል ነኝ ባይ ወይንም እብሪተኛ ምድራዊ ኃይል ኢትዮጵያ በታሪኳ ተሸንፋ አታውቅም፡፡ ክብርና ነጻነት ለኢትዮጵያ ሲመቻት የምታጠልቀው ሲቸግራት የምታወልቀው የጌጥ ዕቃዋ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ በየትኛውም ሁኔታ ለድርድር የማታቀርበው፣ እንደ ዓይኗ ብሌን ሁል ጊዜ የምትጠብቀው የማያልቅ የማረጅ ውድ የዘወትር ልብሷ ነውና!
እኛም ዛሬ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ስንል ከገዛ ማህፀኗ ተወልዶ “ክብሯን ረግጨ በኃይል አንበርክኬ እኔ ብቻ እገዛታለሁ፣ ካልሆነ አፈርሳታለሁ” ብሎ እየወጋን እንዳለው አሁናዊው ጠላታችን እንደ ትሕነግና ሌሎችም እንደሚሉት ከአጉል እብሪትና ከተራ ጉራ ተነስተን ሳይሆን ደግመን ደጋግመን በተግባር ካደረግነው የራሳችን የአሸናፊነት ታሪክ ተነስተን ነው፡፡ ምክንያቱም አላዋቂዎችና የትንሽነትና ታህተ ሰብዓዊነት፣ የአጥንት ቆጠራና የኢምክንያታዊና ግዑዛዊ መንገኝነት ፖለቲካ መስራችና አቀንቃኝ የሆኑት ትሕነግና መሰሎቻቸው እንደሚሉት ታሪክ ተራ ተረት ተረት ሳይሆን የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚቻል ሰዎች በተግባር ሆነውና ችለው ያረጋገጡበት፣ ዛሬን ከትናንትናና ከወደፊቱ ጋር የሚያገናኝ፣ የአሁኑና መጭው ትውልድም መሆንና ማድረግ እንደሚቻል በወሬ ሳይሆን በድርጊት የሚማርበት ህያው የድርጊት ቤተ ሙከራ ነውና! ታሪክን በትክክል ያጠኑ እውነተኛ አዋቂወችና ታላላቆቹ የዘርፉ ሊቃውንት የሚሉትም ይህንኑ ነው፡፡ “ታሪክ ማለት የሰዉ ልጅ ስለ ራሱ የሚያውቅበት ግላዊ ዕውቀት ነው… ሰዎች ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ለማወቅ የሚያስችለው ብቸኛው ፍንጭ ሰዎች ከዚህ ቀደም የሠሩት ሥራ ነው፡፡
ስለሆነም የታሪክ ዋነኛው ፋይዳ ̔ሰው ምን ሠራ?҆ የሚለውን ለእኛ ለሰው ልጆች ማስተማርና በዚህም ‛ሰው ምንድነው?҆ የሚለውን እንድናውቅ ማድረግ ነው” ይለናል አር. ጂ. ኮሊንግውድ፡፡ እናማ ታሪክ አሸናፊነትን በተግባር የምንማርበት የመቻል ቤተ ሙከራ ነውና፣ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ማድረግ የቻሉትን እኛም ማድረግ እንችላለንና ኢትዮጵያ ዛሬም ታሸንፋለች! እናማ የአሸናፊነት፣ የነጻነትና የጀግንነት አኩሪ ታሪካችን ሁለ ነገራችን የተመሰረተበት፣ ማንነታችን የተገነባበት ሥጋና ደማችን፣ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን አጠቃላይ ሕዝባዊ ሥነ ልቦነችን የተሠራበት፣ በየትኛውም ጊዜ የማይለወጥ፣ በማንኛውም ጊዜ የማያስስ የታላቋ ሃገራችን የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ሥሪት ነውና እኛም አሁን ማሸነፍ እንችላለን፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ታሸንፋለች! ማለት ስለሆነ ከምንም በላይ ታሪክ ሥነ ልቦና ነው፡፡ እናም እኛም አባቶቻችን አሸናፊዎች እንደነበሩ፣ በዚህም በዓለም ላይ ተከብረው አንደኖሩ እኛንም አስከብረውና አኩርተው እንዳኖሩን እኛም ከሃዲውንና ዋናውን አሁናዊ የህልውና ጠላታችን ጨምሮ የክብራችንና የነጻነታችን ጠላት የሆኑ ማናቸውንም የዘመናችንን ጠላቶች ማሸነፍ እንችላለን፤ ኢትዮጵያም ዛሬም ጠላቶቿን አሸንፋ በክብርና በነጻነት ከፍ ብላ ትኖራለች!
እንዴትና በምን?
ኢትዮጵያ ዛሬም እንደምታሸንፍ ከተግባባን በዛሬው ዘመን ላይ የምንኖር እኛ አሁኖቹ ኢትዮጵያውን እንዴትና በምን ነው እንደ አባቶቻችንና እናቶቻችን የገጠመንን ክፉ የህልውና ጠላት አሸንፈን በክብርና በነጻነት መቀጠል የምንችለው የሚለውን በጣም በጥቂቱ ለማመላከት እንዲፈቀድልኝ ዝቅ ብዬ በኢትዮጵያዊ ትህትና እየጠየኩ ጽሁፌን በዚሁ አጠናቅቃለሁ፡፡ እጅግ የቅርቡንና በዓለም ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ልጅ ፍጡር ዘንድ እንድንከበርና እንድንኮራ ያደረገንን አንዱንና ዋነኛውን የነጻነትና የክብር ታሪካችን በማሳየነት በማንሳት ልጀምር፡፡ እብሪተኞች እንደ ሰው የማይቆጥሩት የጥቁር ህዝብ “ምንጊዜም የበላይ ነን” ብሎ የሚያምነውን የነጭ ወራሪ በጦር ሜዳ ገጥሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፍንና እናም ለጥቁር ሕዘብ ሁሉ ኩራት የሆነውን ከዚያም አልፎ ለመላው ሰው ልጆች ሁሉ የሰውነት ክብርን ያጎናጸፈውን አኩሪ ታሪክ የሠራነው አድዋ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን! በዚህም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው የሰው ዘር በሙሉ፣ ከራሳቸው ከነጭ ዘር የተገኙ ጭቁን ህዝቦች ሁሉ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ምክንያት፣ ድል አመላካች፣ የአሸናፊነት ምልክት የሆንንን ኢትዮጵያና እኛ ኢትዮጵያውን ነን! ታዲያ ይህን እንዴት ልናደርገው ቻልን? አጭርና ግልጽ መልሱ፡- በተባበረ ክንዳችንና በአንበሳ ልባችን ነው፡፡
እንዴት ለሚለው፤ በአሁኗ ኢትየጵያ የምንገኝ እኔና የእኔ ትውልድ ጀግንነታችንና ኩሩነታችንን አስጠብቀን ለመቀጠል እንደ አባቶቻችን በአንድነት መመከትና በጀግንነት ዋጋ በመክፈል የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ በቅርቡ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት፤ ይህንን የምናደርገውና እንደ አባቶቻችን አኩሪ ታሪክ መስራት የምንችለው “በፌስቡክና በወሬ” ሳይሆን በሥራና በተግባር መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ክብራችንን ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ እንደ አባቶቻችን በጀግንነት ታግለን በድል መወጣት ስንችል ነው እኛም በኩራት ኢትዮጵያም በክብር መኖር የምትችለው፡፡ ትውልዱ እንደቀደምቶቹ አባቶቹና እናቶቹ ጀግና ነኝ ለማለትና ኩሩ ሆኖ ለመገኘት በምኞት ሳይሆን በተግባር ማድረግ የሚገባውን አድርጎ መገኘት፤ የራሱን ዘመን ሥራ ሠርቶ ጀግንነትን ፈጽሞ እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ፣ እንደ እናት አባቶቹ አኩሪ ታሪክ ፈጽሞ በኩራት በክብር ለመኖር የሚያስችለውን ታሪክ አድርጎና ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ዛሬም ታሸንፋለች፤ ለዘላለምም በክብር ትኖራለች!
-
Josef Kassa
- Member
- Posts: 2
- Joined: 19 Nov 2021, 07:32