Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 11594
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

በመዘጋጀት ላይ ያለው የዶ/ር አቢይ በዓለ ሲመት ንግግር

Post by sarcasm » 03 Oct 2021, 07:20

ተጻፈ በያሬድ ጥበቡ

መልካም 2ኛ በዓለ ሲመት:

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ቅዳሜ ከሰአት በኃላ እነዚህን ቃላት በአይፎን 12 ፕሮ ስልኬ ላይ ስተይብ ከፊት ለፊቴ በቆመው አዲስ ሳምሰንግ ቲቪዬ ላይ የምወደው ብራይድ ኦፍ ኢስታንቡል የተሰኘው የቱርክ ድራማ 185ኛ ምእራፍ እየተጫወተ ነው:: የቱርክ ድራማ ነብሴ ነው:: የፀሀፊዎቻቸው ጥልቀትና የተዋናዮቻቸው ውበት ይመስጠኛል:: ከአንድ ትውልድ በኃላ እንደርስባቸዋለን ብዬ አስባለሁ:: ለዚሁም ምክንያት የሆነኝ የቱርኮቹ የትረካ ጥንካሬ ከረጅም ሥልጣኔያቸው የመነጨ ነው ብዬ ስለተረዳሁና አናንሳቸውም ብዬ ማሰብ ስለወደድኩ ነው:: አሁን ፊልሜ አልቆ የተአምር ግዛው በባይተዋር ጎጆ እየተጫወተ ነው:: ባለፉት 30 የኢህአዴግ አገዛዝ ዓመታት እጅግ የተዋጣልን ነገር ቢኖር ዘፈናችን ይመስለኛል:: ቱርኮቹ እኛ ላይ ለመድረስ አንድ ትውልድ ይፈጅባቸው ይመስለኛል:: ታምርና ዳዊት ፅጌ ምስክር ናቸው:: በሥነጥበብ ዘርፍ የሚታየው እመርታ የኢህአዴግ አገዛዝ ዓመታት የጭለማ ብቻ እንዳልነበሩ ይጠቁም ይመስለኛል:: ምናልባት በንፉግነት ወይም ለብሽሽቅ ጭለማ ብቻ አድርገን ማየት የመረጥን ይመስለኛል::

የታምር ዘፈን ሲያልቅ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው የኢሬቻ በዓል ላይ የተገኙ ቄሮዎች ጃዋር ይፈታ: በቀለ ገርባ ይፈታ: ፍትህ ለትግራይ: ዳውን ዳውን አቢይ እያሉ ሲፈክሩ የሚያሳይ የዩቱብ ቪዲዮ እንግዳቤቴን እየቀወጠው ነው:: ከአራት ዓመታት በፊት ዳውን ዳውን ወያኔ ይል የነበረው ቄሮ ዛሬ በአቢይ አህመድ ሁለተኛ በዓለ ሲመት ዋዜማ ዳውን ዳውን አቢይ ማለቱ ትርጉሙን ለተረዳው የትዬለሌ ነው:: ሩቅ ነው: ጥልቅ ነው:: ምናልባትም የአዲሱን ሥልጣን ተጠባቂ ጉዞ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል:: እንዴት ቢሆን ነው በቄሮ ትግል የመጣው ሥልጣን እዚህ ቅርቃር ውስጥ ራሱን ማግኘት የቻለው?

እነዚህን ጥያቄዎች እያሰብኩ ሳለ አሁን አቢይ ምን እያደረገ ይሆን የሚል ሀሳብ ውልብ አለብኝ:: ደግሞም ለአፍታ ወደመጀመርያው በዓለ ሲመቱ ንግግር ዥው ብዬ ሄድኩ:: ያ ንግግር ከላይ ከደመናዎቹ የወረደ ነበር:: ሃገሬውን አስተሳስሮ በአንድነት ያቆመ ተአምር ነበር:: ልቦና ንፁህ ሲሆን ቃል ከአማልእክቱ እንደሚነጠቅ ይጠቁም ይመስለኛል:: እዚያው በዝያው አሁን አቢይ የሁለተኛ በዓለ ሲመቱን ንግግር እየቀመረ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ:: ግን ልቦናው ከአማልክቱ መገናኘት መቻሉን ተጠራጠርኩ:: ምክንያቱም ከመጀመርያው በዓለሲመት ወዲህ ብዙ ሆኗል:: በኦሮሚያ ክልል ብዙ ሺህ አማሮች በማንነታቸው ተጨፍጭፈዋል:: በትግራይ በተቀሰቀሰው ጦርነት እናቶችና ወጣት ሴት ልጆቻቸው ክብራቸው ሲገሰስ: ወጣቶች በኤርትራ ወታደሮች በግፍ ተረሽነዋል:: በነዚህ ሁሉ የግፍ ፍፃሜዎች አቢይ ከተርጣሪዎቹ አንዱ ሆኗል:: በዚህም ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ተቃውሞና ኩነና ደርሶበታል:: የመንቀሳቀስ መብቱም ላይ እገዳ ተጥሎበታል:: ከዓለም የተረፉት ወዳጆቹ ሩስያ: ቱርክና ኤርትራ ሆነዋል:: አነዚህ ሁሉ ጉዳዮች በአቢይ አእምሮ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያደርጉ ይመስለኛል:: ስለሆነም በማዘጋጀት ላይ ባለው የበዓለ ሲመት ንግግር ላይ ጫና ማድረጋቸው አይቀርም:: ምን ዓይነት ንግግር ቢያደርግ ቀልባችንን ከገዛው የመጀመርያው ንግግሩ ጋር የተቀራረበ ንግግር ማድረግ ይችል ይሆን ብዬ ለማሰብ ሞከርኩ::

ከሁሉ በላይ ወደሃቀኛ ልቦናው: ወደህሊናው ቢመለስ ለራሱም ለሃገሩም አዲስ እድል የሚከፍት ይመስለኛል:: አቢይ በሁለተኛ በዓለ ሲመት ንግግሩ ላይ ከህሊናው የታረቀ መሪ ለመሆን መወሰን ይኖርበታል:: ባለፉት ሦስት ዓመታት ደጋግሞ ከተመላለሰባቸው የግማሽ እውነት: የቆርጦ መቀጠል: የእልህና የጭካኔ መንገድ ሆን ብሎና አስቦበት ለመመለስ መወሰን ይኖርበታል:: ይህ ከባድ ውሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል: ምክንያቱም የጥፋት መንገዱን አይዞህ የሚሉ ዲያቆናት:ፈላስፋዎችና ዋሽቶአደር የማህበራዊ ሚድያ ጠበብት በዙርያው ስለተኮለኮሉ የነርሱን እገዳ አልፎ ከህዝቡ ጋር በሃቅ መገናኘት ዳገት መስሎ ሊታየው ይችላል:: ሆኖም ሃገሩን የሚወድና በታሪክ ፊት በቀና የሚነሳ መሪ ሆኖ መገኘት ከፈለገ ከዚህ ቡድን አስተሳሰብና እስር ራሱን ማላቀቅ ይኖርበታል:: ይህንንም ለማድረግ ሲችል ሃገራችንን ወደትክክለኛ ሰላማዊ ፍኖት ሊመራ ይችላል ብዬ ማሰብ እወዳለሁ::

አቢይ በሁለተኛው በዓለሲመት ንግግሩ ወቅት:

ሀ) ጦርነቱን የሚሸከም ኢኮኖሚ ኢትዮጵያ እንደሌላትና: በዚህ ላይ የምእራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከተጨመረበት የመዳቀቅ ችግር ሊመጣ ስለሚችል ይህን አደጋ ለመታደግ ጦርነቱን በድርድር ከተገኘ የተኩስ ማቆም ስምምነት ለመፍታት ፈቃደኛ መሆኑን:

ለ) ድርድሩም በተለያየ መንገድ የትግራይ ህዝብ እንደመሪ ድርጅቱ እንደተቀበለው ካሳየው ህወሓት ጋር እንደሚሆን

ሐ) የትግራይ ህዝብ በደረሰበት የሰብአዊ ቀውስና ረሃብ መንግስት የተሰማውን ሃዘን ገልፆ ይህን ችግር ለመፍታት በአፋጣኝ የአለምአቀፍ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደርስ መንግስት በሁሉም መስክ እንደሚተባበር:

መ) በኢኮኖሚው መስክ ኢህአዴግ ከ1994 የመጀመርያው ተሃድሶ ጀምሮ የቀየሳቸውና በተግባር ተፈትነውም የሁለት አሃዝ እድገት አስገኝተው ዓለምን ያስደመሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በጎደሉበት እየሞላና በተጣመሙበት እያቃና ለመቀጠል መንግስት የሚወስን መሆኑን

ሠ) በሃገር አንድነትና ሉእላዊነት ጉዳይ እሁን ተንሰራፍቶ ከሚታየው የዜጋና የዘውጌ ማንነቶች ውጥረት ሆን ብሎ በመራቅና በመደመር እሳቤ በመመራት የብሄረሰቦች የወል መብትና የዜጎች የግል መብት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚጠበቅባት ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ለማቆየት መንግስት የድርሻውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ:

ረ) ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እስክንድርን: ጃዋርን: በቀለን: አቦይ ስብሃትን ወዘተ ለሃገር ሰላምና እርቅ ሲባል መንግስት ለመፍታት መወሰኑን:

እነዚህንና መሰል ክብደት ያላቸውን ቁምነገሮች በዚያ ለዛ ባለው ብእራቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢናገሩ እንደገና ተስፋ ስንቀን ለመነሳት ምክንያት ልናገኝ እንችላለን ብዬ ማሰብ እወዳለሁ:: ባለፉት 3 ሰአታት ጣቶቼ በትየባ ብዛት ፈለግ እስኪያወጡ መድከሜ አሁን ለምወዳት እናት ሃገሬ ማድረግ የምችለው ይህ በመሆኑ ነው:: ጠቅላይ ሚንስትሩ አንብበው ለንግግራቸው ግብአት አድርገው የሚጠቀሙበት ሃሳብ ያገኙ ይሆናል ብዬ ማሰብ እወዳለሁ::

አስቀድሜ ቀጣዩ የሥልጣን ዘመንዎ የትህትና: የሃቅ: የእዉነተኛ ሃገር ፍቅር : አርቆ የማስተዋል ዓመታት እንዲሆንልዎት መመኘት እወዳለሁ:: እምቢተኛ ሆነው በለመዱት ያለፉት 3 ዓመታት የውድመት መንገድ መቀጠልን ከመረጡ ግን እኛም በለመድነው የሰላማዊ ተቃውሞ እንድንቀጥል ያስገድዱናል:: ቴሌቪዥኔ ያማል ቅኔውን እየዘፈነ ነው:: በዘቢባ ድምፅ ልለያችህ:: መልካም ምሽት!

Please wait, video is loading...