መቀሌን ለቆ የመውጣት የመንግስት ውሳኔ የዘገዬና በአስገዳጅ ሁኔታዎች የተደረገ ቢሆንም ትክክለኛ ነው! ወታደሩ ምንም አይነት የትግራይ ህዝብ ድጋፍና ደጀን ሳይኖረው እንደ ቅጠል መርገፍ የለበትም። የትግራይ ህዝብም በረሃብ ማለቅ የለበትም። አሁን ሁሉም ወገን ከጅምላ እብደት፣ ከእልክና ከበቀል ስሜት በመራቅ ሰከን ብሎ ስህተቱን መገምገም፣ የሰላም አማራጮችን መመልከትና፣ እንደ ሀገር ከገባንበት ቀውስ የመውጫ መንገዶችን ማፈላለግ ያሻል። እጅግ ሲበዛ ደም ከተቃባናቸው ኤርትራውያን ጋር እርቅና ሰላም ማውረድ ከተቻለ ከትግራዮች ጋርስ ሰላም ማውረድ ለምን አይቻለንም?
የሚበቃንን ያህል ተጨፋጭፈናል ፤ በየጠርዙ ሁነን በዚህ ጉዳይ አንደራደርም ያልን ሁሉ ዛሬ ከድርድርና ከውይይት ውጭ የእኛን ሀሳብ በሌሎች ላይ መጫን እንደማይቻል ተረድተናል፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሀይል ለመፍታት መሞከር የአጭር ግዜ መፍትሔ እንጅ ዘላቂነት ያለው መረጋጋት እንደማያመጣም ካለፈው ታሪካችን ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታም መራር የሆነ ትምህርት ወስደናል።
አሁን ከጉልበትና ከመሳሪያ ውጭ ያሉ አማራጮች የሚሞከሩበት ግዜ ነው። መንግስት የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በመፍታት ለሀገራዊ መግባባት ያለውን ዝግጁነት ያሳይ። ፖለቲካ በግለሰቦች መካከል በሴራ መጠላለፍን ያካተተ ቢሆንም በህዝብ ላይ የሚሰራ የሴራ ፖለቲካና ሸፍጥ ግን ብዙ ርቀት አያስኬድም። በመሆኑም መንግስት ለሰላምና ለሀገራዊ መግባባት ቅድሚያ እንዲሰጥ ማበረታታት አለብን። የፖለቲካ ሀይሎችም ከአጥፍቶ መጥፋትና ከዋልታ ረገጥ ፖለቲካ ይውጡ።
ይብቃን! መገዳደል ይብቃን! ደም መፋሰሱ ይብቃን! መጨፋጨፍ ይብቃን! አንዱ አንዱን ማሳደድ ይብቃን! በሀሳብ ልዩነት ምክንያት በጠላትን መተያየት ይብቃን! ረሃብ ይብቃን! ስደት ይብቃን! ጥላቻ ይብቃን! በከንፈር መሸነጋገሉን ትተን ልባችንን ለእውነተኛ እርቅ ለሀቀኛ ውይይትና ለሁለንተናዊ ሀገራዊ መግባባት እናዘጋጅ። ዛሬ እንኳ ከዚህ ሁሉ ጥፋትና ውድመት በሁዋላ አርቲስቱ እንዳለው ሰከን እንበል እንጅ።
Please wait, video is loading...