Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 11594
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

የትግራይዋ ዑመራ ከተማ ጉዞዬ የአይን ምስክርነት...... (ከጎንደር እስከ ሑመራ) - በሀወኒ ዳበሳ

Post by sarcasm » 22 Mar 2021, 21:02

የትግራይዋ ዑመራ ከተማ ጉዞዬ የአይን ምስክርነት......

አርብ መጋቢት 3, 2013 ዓ.ም ሌሊት 11፡30 የተመደበልኝ መኪና እና 10 የአማራ ልዩ ኃይል አባላትን የያዘ ቡድን ጥበቃ እንዲያደርግልን በሌላ መኪና በድምሩ ሁለት መኪናዎች ካረፍኩበት ሆቴል ወደ ምዕራብ ትግራይ ዑመራ ከተማ ለስራ ጉዳይ ሊወስዱን መጡ። የሁመራ ኤርፖርት ዝግ ስለሆነ። ጎንደር ድረስ በአውሮፕላን መጥቼ ከዛ ወደ ሁመራ በመኪና 250 ኪ.ሜ መሄድ ግዴታዬ ነበር።

ጉዞውን ስጀምር በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው። አንድም ድንገተኛ ጥቃት ሊፈፀምብን ይችላል የሚለው ስጋት ነበረኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጦርነቱን አሻራ ለመታዘብ መቻል፣ በአካባቢው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት እና የተሰጠኝን ስራ ሰርቼ መመለሴን ደግሞ እንደ Adventure ቆጥሬዋለሁ።

ጉዞውን የጀመርኩት በፀሎት ነበር። የአማራ ልዩ ሀይል አባላት ትህትናቸው መልካም ነበር። ተግባቢም ነበሩ። ከፊታችን ጥበቃ እያደረጉልን ከሚሄዱ አባላት በተጨማሪ ሁለት የልዩ ሀይል አባላት በእኛ መኪና ውስጥ ነበሩ። ከጎኔ ጥበቃ ያደርግልኝ የነበረው አንዱ የልዩ ሀይል አባል፣ ስለምናልፍባቸው አካባቢዎች ስም እና ታሪክ እያወጋኝ መንገዳችንን ቀጠልን። የአካባቢው የሰሜን ጎንደር ተወላጅ ነው።

ጉዟችንን ቀጠልን። በሹፌራችን መረጃ መሰረት ወደ 150 ኪሎሜትሮችን ተጉዘን፣ ቀድሞ የትግራይ እና የአማራ ወሰን የነበረችው እና በዚህ ጦርነት ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበችው ዳንሻ ከተማ ደረስን። በዚያም ቁርስ እንድንበላ በዛውም ትንሽ እረፍት እንድናደርግ ተብሎ ዳንሻ ከተማ ላይ ቀድሞ የአማራ ክልል ወሰን የነበረውን ተሻግረን አሁን በአማራ ልዩ ሀይል ቁጥጥር ስር ወዳለው የምዕራብ ትግራይ አካል ዳንሻ ከተማ ወረድን።

ዳንሻ ወትሮውን የሞቀች ከተማ እንደነበረች ታስታውቃለች። አሁን ግን የተዘጉ የንግድ መደብሮች በቁጥር ይበልጣሉ። አብዛኞቹ የተዘጉት የንግድ ተቋማት በተለምዶ የትግርኛ ስም ያላቸው ናቸው። ከአንዲት ቤት ጎራ ብለን ቁርስ አዘዝን። በዛም የልዩ ሀይል አጃቢዎቻችን እጀባ አልተለየንም ነበር።

ከቁርስ በኃላ በቅርበቴ የነበረችውን ቡና የምታፈላ ልጅ ቡና እንድትሰጠኝ ጠይቄያት በዚያው ጨዋታ ጀመርን። አማራ እንደሆነች እና ከአራት አመት በፊት ከበለሳ ወደዚህ ስፍራ እንደመጣች አጫወተችኝ። ከጦርነቱ በፊት ህወሓት በትግርኛ ብቻ እንዲያወሩ እንደሚያስገድዳቸው። አማርኛ ማውራት ክልክል እንደነበር ነገረችኝ። ይህን ስትነግረኝ ይደርስባቸው የነበረው ጫና አናደደኝ። ቀጠለች... ፊትዋ በደስታ ተሞልቶ ፈገግ ብላ አሁን ግን የአማራ ልዩ ሀይል ቦታውን ከተቆጣጠረ በኃላ ነፃነታቸውን እንዳገኙ ነገረችኝ። ፊቷ ላይ ያለው ደስታ ደስ ይላል። አላቆመችም ጨዋታዋን። አሁን ግን በሁለቱም አማራ የሆኑ እና በእናቱ ወይም በአባቱ አማራ የሆነ እንዲቆይ፣ በሁለቱም ትግሬ የሆኑ ግን በስፋት ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ እንዳለ ፈገግታዋ ሳይቀንስ አጫወተችኝ። ይሄን "የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር" ከምዕራብ ትግራይ እስካሁን ከ700 ሺህ በላይ የተጋሩ ተወላጆች ተፈናቅለዋል ያለው ትዝ አለኝ። አንዲት እናት ከዳንሻ እስከ ደደቢት ነጠላቸውን ብቻ ይዘው እንደተሰደዱ ለBBC Amharic የሰጡት መግለጫም ትውስ አለኝ። በዚህም ልቤ እጅግ አዘነ።

ወደ መኪናችንን ተመልሰን ጉዟችንን ልንቀጥል ተነሳን። አሁን ፍርሀቴ ጠንከር አለ። ምክንያቱም የምዕራብ ትግራይ ምድር ላይ ከመቶ ኪሎሜትር የሚበልጥ ርቀት እስከ ሁመራ እንጓዛለን። ይህ ማለት ደግሞ የህወሓት የደፈጣ ጥቃት ሊገጥመን ይችላል በሚል ስጋት ነው።

ጉዟችንን ቀጠልን። የአማራ ክልል በተቆጣጠረው የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ላይ መዋቅሩን ዘርግቷል። በየርቀቱ "በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር አስተዳደር የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት.....አስተዳደር" የሚል ተለጥፏል። ቀድሞ በትግርኛ ይፃፉ የነበሩ የንግድ ተቋማት፣ የመንግስት ተቋማት እና ሌሎችም ድርጅቶች አሁን በአማርኛ እንዲሆኑ ተደርጓል። አንዳንድ ልብ ያልተባሉ አነስተኛ ተቋማት ላይ ግን አሁንም የትግርኛ ማስታወቂያዎች ተለጥፈው እንዳሉ ናቸው።

መቼም ምድሩ ለም ነው። እርግጠኛ ነኝ እኔም ሆንኩ እናንተ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ለም መሬት አትጠብቁም። ሙቀቱ ግን አያድርስ ነው። እንደው ነፋሻማ ሆኖ እንጂ 43 ዲግሪ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት ይቻላል። በጉዞዬ ላይ ብዙ የጦርነቱ አሻራዎች ይታያሉ። በከባድ መሳሪያ የተደበደቡ ህንፃዎች፣ በአየር ጥቃት የተመቱ ታንኮች (ከስር ምስሉን ካያያዝኩት በተጨማሪ አራት የተቃጠሉ ታንኮች ተመልክቻለሁ) ፣ ከባድ ውጊያ አሰተናግደው በፍንዳታ ያረሩ ሰፊ የሳር ሜዳዎች በተወሰነ ርቀት ውስጥ ይታያሉ። ከጎኔ ያለው የዐማራ ልዩ ሀይል ጓድ በየጦርነት አውድማዎቹ የነበሩ አስክሬኖች ለረጅም ጊዜ ሳይነሱ ቆይተው እንደነበር አጫወተኝ። ረጅም መንገድ ከተጓዝን በኃላ በመንገዳችን ላይ መስቀለኛ ቦታ ላይ ደረስን። ወደ ግራ ይዘን ከሄድን ከ17 ኪ.ሜ በኃላ ወደ ማይካድራ፣ ወደ ቀኝም ተቀራራቢ ርቀት ከተጓዝን በኃላ ወደ ሁመራ እንደምንገባ ሹፌራችን ነገረን። ያው ጉዟችን ለሁመራ ስለሆነ ወደ ቀኝ ታጥፈን።

ሁመራ መግቢያው ላይ ከባድ ጦርነት እንደነበር ብዙ አሻራዎችን መታዘብ ይቻላል። ሁመራ ደረስን። መግቢያው ላይ አዲስ እንደሆነ የሚያስታውቅ ማስታወቂያ ተለጥፏል። እንኳን ወደ ሰሜን ጎንደር ዞን ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ወረዳ የዑመራ ከተማ በደህና መጣችሁ ይላል። አስፋልቱን ይዘን ጉዟችንን ቀጠልን። ከተማው ፀጥ ብሏል። ቦታው በአማራ ልዩ ሀይል ቁጥጥር ስር ከሆነ በኃላ በአማራ ልጆች ከተከፈቱ ውስን እና አነስተኛ የምግብ እና የቡና መሸጫ ቤቶች በስተቀር አንዳችም ክፍት የሆነ ነገር የለም። ጭርታው ያስፈራል። ስራችንን ከመጀመራችን በፊት የዞኑ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ደብዳቤያችንን ለከንቲባው እንዲመራልን እና ተጨማሪ ጥበቃ እንዲመድብልን ወደ እርሱ ቢሮ መድረስ ነበረብን። በሙቀት ምክንያት የመንግስት ስራ የምሳ ሰዐት ከ6 ሰዐት እስከ 9 ሰዐት ስለሆነና እኛ ደግሞ የደረስነው 5፡30 ሰዐት ስለነበር እየተጣደፍን ነበር ወደ ፅ/ቤቱ የሄድነው። በመንገዳችን ላይ አንድም የተከፈተ የንግድ ተቋም የለም። ባንኮች ዝግ ናቸው። ብቸኛ የተከፈተ ያየሁት አንድ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ነው። ታዲያ ብር ለማውጣት የተሰለፈውን የህዝቡን የሰልፍ ርዝመት አትጠይቁኝ።( መቼም በዚህ ወቅት ብር ለማስገባት አይሰለፉም ብዬ ነው።)

ዑመራ ጭርታዋ ያስፈራል። የውስጥ መሠረተ ልማትዋ ጥሩ ነው። በመንገዶቹ ጠርዞች ላይ የትግራይ ባንዲራ ቀለሞች የሆኑት ቢጫና ቀይ ተቀብተዋል። የዞኑ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ቢሮ ደረስን። እንደምንመጣ ቀድሞ መረጃው ስለነበራቸው ለከንቲባው ለማስመራት ጊዜ አልወሰደብንም። ደብዳቤያችንን አስመርተን እና ጊዜያዊ አስተዳዳሪውን አመስግነን ስንወጣ በመተላለፊያው ኮሪደር ላይ አንዲት የተጋሩ እናት እድሜዋ ሀያዎቹ ውስጥ ከሆነች ልጅዋ ጋር በእጃቸው ሁለት ቦታ የተቀደደ ወረቀት ይዛ ሁለቱም ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ። ልቤ በሀዘን ተነካና ቀረብ ብዬ ምን ሆናችሁ ነው? አልኳት። ልጅትየዋ ከቶውኑ አማርኛ አትችልም። እናትየዋ ግን በተሰባበረ አማርኛ ተጋሩ ስለሆንን ከዚህ ከተማ ለቅቀን እንድንወጣ ቀነ-ገደብ ተሰጥቶናል። ይሄ ወረቀት የተወሰነ ንብረቴን ይዤ እንድወጣ ቀነገደቤ የተራዘመበት ነው። ያለእርሱ መንቀሳቀስ አልችልም። እርሱንም አንድ የልዩ ሀይል ኃላፊ ቀደደብኝ። ጫናው በረታብን። መኖሪያ ቤታችን ላይ ያልሆነ ነገር ይፃፋል። በመንገድ ላይ በሄድን ቁጥር ጁንታ እንባላለን። እንዲህ የሚያስለቅሰኝ የተደራረበ ብሶቴ ነው አለች። በጣም አዝኜላት ይዣት ከልጅዋ ጋር የጊዜያዊ አስተዳዳሪው ቢሮ አስገባኃት። እንደገባን ልጅትዋ ፈጥና እና ስሜታዊ ሆና በትግርኛ ስታወራ አስቆማት እና ትግርኛ አልችልም በአማርኛ አውሪ! ብሎ ተቆጣት። ትግርኛ ግን ይችል ነበር። በኃላም ተቀመጡ ሲላቸው ሊያናግራቸው እንደሆነ ስላየሁ ቢሮውን ለቅቄ ወደ ከንቲባው ቢሮ አመራን።

ከንቲባውም ቢሮ ጉዳያችን አልቆልን ቀጥታ ወደ ስራችን ገባን። በስራዬ ላይም አንዲት የአካባቢው ነዋሪ የሆነች አማርኛ እየሰባበረች የምትናገር ተጋሩ ወጣት ሴት ቀረበችኝ። ፈገግ ያለ ፊት ሳሳያት እና እንድትቀመጥ በዐይኔ ስጋብዛት መጥታ አጠገቤ ተቀመጠች። ሀበን እባላለሁ አለችኝ። እኔ ደግሞ ሀወኒ እባላለሁ አልኳት። የስሜን ትርጉም ጠየቀችኝ። ኦሮሚኛ እንደሆነና "የተመኘኋት" ማለት እንደሆነ፣ አባቴ እንዲህ ያለኝ ሴት ልጅ ይመኝ ስለነበረ ነው አልኳት። ደስ አላት። እናንተ ኦሮሞዎች ለእኛ ጥሩ ናችሁ አለችኝ። አመሰገንኳት እና አያይዤ የጦርነቱ ወቅት ምን ይመስል እንደነበር ጠየቅኋት።

በጣም አስፈሪ ጊዜ ነበር አለችኝ። ሶስት ቀን ሙሉ ያለማቋረጥ ከባድ ጦርነት ነበር አለችኝ። ለአፍታ እንኳን የተኩስ ድምፅ አልቆመም ነበር። ሁላችንም የምንሞት መስሎን ነበር አለችኝ።ከባድ መሳሪያ በገፍ ይተኮስ ነበር። ቤታችን ውስጥ ረባዳማ ስፍራ ላይ ነበር የምንደበቀው። ወደ ውጪ መውጣት የለም። ውሀና መብራት ተቋርጧል። አራተኛ ቀን ላይ ግን የነበረው የሚዘገንን ነበር። መሸናነፍ ስላልቻሉ የዑመራ አስፋልቶቹ እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ በአካል በጣም ተቀራርበው ሳንጃ የታከለበት ሰቅጣጭ ግብግብ ውስጥ ገቡ። ይህንንም በበራችንን እና በመስኮታችን ቀዳዳዎች አጮልቀን እንመለከት ነበር። ዘግናኝ ነበር። ያን ጊዜ ነው የኤርትራ ወታደሮችን ያየሁት አለችኝ። ብዙ አስክሬኖች በጎዳናው እና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ወደቁ በስተመጨረሻ ከዕለቱ ዘጠኝ ሰዐት አካባቢ የትግራይ ጦር ሀይል ከዳው። ተኩሱም፣ የአካል ግጥሚያውም ጋብ አለ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች ከዐማራ ልዩ ሀይል ጋር አካባቢውን መቆጣጠር ጀመሩ አለችኝ። በነገራችን ላይ ኤርትራ ከዑመራ ከተማ በመኪና አምስት ደቂቃ ብቻ ርቀት ላይ ከተከዜ ወንዝ ማዶ ነው ያለችው። የዕለቱ ጉዳዬን ሰርቼ እንደጨረስኩ ድንበሩን አይቼ አልፋለሁ የሚል ዕቅድ ይዣለሁኝ።

ሀበን ማውራቷን ቀጠለች። እኔ ግን ልቤ ታወከ። በተለይ ሳንጃ ተጠቅመው የአካል ለአካል ፍልሚያ መደረጉ በጣም ልቤን አሳዘነኝ። ሁለት ወንድሞቼ ኃላፊነት በጎደላቸው መሪዎች ምክንያት ጦር ሲሰባበቁ ፣ ቃታ ሲሳሳቡ እና ሳንጃ ሲማዘዙ ማሰቡ ልቤን አወከው። የንግድ ሱቆች ከጦርነቱ ከአራት ወር በኃላም ለምንድነው የማይከፈቱት? አልኳት። ምክንያቱም የሱቆቹ ባለቤቶች ተጋሩ ናቸው። አብዛኛው ለቅቆ እንዲወጣ ታዞ ለቅቆ ወደተቀረው የትግራይ ክፍል ተሰዷል። ብዙዎች ታስረዋል። የተወሰነ ንብረት ይዘን ለመሄድ ያሰብን ጊዜያዊው የዐማራ ክልል መስተዳድር እንድንወስድ እስኪፈቅድልን ጊዜያዊ ወረቀት ተሰጥቶን በየሳምንቱ ከንቲባ ፅ/ቤት ቀርበን እያራዘምን ነው የምንኖረው። እኛም ተራው ደርሶን የተወሰነ ዕቃችንን እንኳን መውሰድ ከቻልን ከዚህ ለቀን እንሄዳለን። እስከዛው ግን እየደረሰብን ያለው ዕንግልት አያድርስ ነው። ከመቻል ውጪ አማራጭ የለንም አለችኝ። አሳዘነችኝ። ሀበን ተወልዳ ያደገችው ሁመራ ነው። አሁን ግን በትውልድ ሀገሯ ባይተዋር ሆናለች። የጦርነት ክፋቱ በሴት ልጅ ላይ መበርታቱ!

በቀደመው ዘመን የዐማራ ልጆች በህወሓት አስተዳደር ከፍተኛ በደል ደርሶባቸዋል። በጨቋኝ ስርዐት ውስጥ ነበሩ። ዛሬ ነገሮች ተገልብጠው ተበዳይ በዳይ ሆኗል። በዳይ ደግሞ ተበዳይ። እርግጥ በቀደመው አስተዳደር ከደረሰባቸው ግፍ ቁጣቸው የበረዱ ባይሆንም፣ ይህ አካሄድ ግን ነገም የማያባራ መበቃቀል እንዲኖር ነው የሚያደርገው። እዚህ ጋር ሳላነሳ የማላልፈው፣ የትግራይ ተወላጆችን ማፈናቀሉ እስከ ላይ ድረስ በዐማራ ክልላዊ መንግስት መዋቅር ተዘርግቶለት በተደራጀ እና በፈጠነ መልኩ እየተከወነ ያለ አሳፋሪ ተግባር ነው። ያው አብዛኞቹ በአዲስ አበባ የሚገኙ Mainstream ሚድያዎች በታሪክ አጋጣሚ በአማራ ተወላጆች የተያዙ ስለሆኑ በአማራ ክልል አማካይነት የሚፈፀሙ ግፎች ዝቅ ተደርገው ወይም ባላየ ታልፈው ነው የሚቀሩት።

የአማራ ክልል መስተዳድር በአካባቢው "ህዝበ-ውሳኔ" ማድረግን በፍፁም እንደማይቀበል አስታውቋል። ዶ/ር ዐቢይም ከፊቱ ምርጫ ስላለበት እና የዐማራ ህዝብን ድምፅ ላለማጣት ሲል የአካባቢውን የትግራይ ተወላጆች መስዋዕት ማድረግ መርጧል። ከምርጫው በኃላ ግን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫናም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቤቱታን ባላየ ማለፍ ስለማይችል በአካባቢው ላይ "ህዝበ ውሳኔ" ይደረግ ብሎ የአማራ ክልል መንግስት ላይ ጫና ማድረጉ አይቀርም። ይህንንም እነ አቶ አገኘሁ ተሻገር ቀድመው ስለተረዱት እና ወደ "ህዝበ-ውሳኔ" መግባታቸው የማይቀር መሆኑን ስለተረዱት በጊዜ በአካባቢው ከ83% በላይ የሆኑትን የትግራይ ተወላጆች በፍጥነት በማስወጣት እና የዐማራ ተወላጆችን በገፍ የማስገባት ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ በዐማራ ክልል መንግስት ስም የተዘጋጁ የነዋሪነት መታወቂያ በገፍ በማደል የDemographic ለውጥ ዘመቻ ላይ ተጠምደዋል።

እኔ በተወሰነ መስመር ላይ ስለተንቀሳቀስኩ የኤርትራ ወታደሮችን ባላይም ሀበን እንደነገረችኝ ከሆነ የኤርትራ ወታደሮች አሁንም አብረዋቸው ነው የሚኖሩት። በተለይም እስከ ተከዜ የሚያዘልቀውን የከተማውን ዋና መንገድ ለዐማራ ልዩ ሀይል ለቀው፣ የውስጥ ለውስጥ መጋቢ መንገዶችን ይዘው ነው ያሉት። በኤርትራ ወታደሮች ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈፀም መስማቷን፣ እርሷ ግን ከዚህ የእኛ ስራ አጋጣሚ ውጪ ወደ ደጅ ወጥታ ስለማታውቅ ምንም ነገር ገጥሟት እንደማያውቅ፣ ለወደፊቱ ግን እዚህ እስካለች ድረስ በብዙ እንደምትሰጋ አጫወተችኝ።

ስራዬን ከከባድ ሙቀት ጋር ከቀኑ 10፡30 ላይ ጨረስኩ። በስራ ሪፖርቴ ላይ የተካተቱ አንዳንድ አሳዛኝ ዕውነታዎችን በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ብከት ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ከመስሪዬ ቤቴ Protocol አንፃር ፈፅሞ የተከለከለ ስለሆነ አላነሳውም። ወደ ተከዜ ለመሄድ አስቤ ለአጃቢዎቼ ወደዛ እንድንሄድ ብጠይቃቸው፣ ሰዐቱ በጣም እንደሄደ እና በተቻለ ፍጥነት እስከ 12 ሰዐት ድረስ አሁን በዐማራ ልዩ ሀይል ቁጥጥር ስር ያለውን የዳንሻ ድንበርን አልፈን በፌዴራል መንግስቱ የሚታወቀውን የዐማራ ወሰን ውስጥ መግባት እንዳለብን ነግረውኝ፣ ውሀዬን ይዤ ወደ መኪና ገባሁ።

የትግራይ ተወላጆችን ሀበሳ፣ ሀበን ስለነገረችኝ ከመሳሪያ ያለፈ የእጅ በእጅ ጦርነት፣ የእነ ሀበንን እና ሲያለቅሱ የነበሩትን የተጋሩ ሴቶች ዕጣ ፈንታ፣ ዶ/ር ዐቢይ እንደቀላል የሚጠቀማቸው ተለጣፊ ስሞች (የቀን ጅብ፣ ጁንታ) ታች ድረስ ወርደው ምስኪኑ ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን የስነ ልቦና ጫና፣ ቀጣዩ የኢትዮጵያ እና የትግራይ ዕጣ ፈንታን፣ ህወሓት በመጨረሻ የሄደው የተሳሳተ መንገድ ምን ያህል የትግራይ ህዝብን ዋጋ እንዳስከፈለው....እያሰብኩ ወደ ጎንደር የሚያደርሰውን መንገዴን ከተረበሸ መንፈሴ ጋር ተያያዝኩት።

ሀወኒ ዳበሳ ቀልቤሳ ነኝ፣ ከተከዜ ወንዝ ወዲህ ማዶ.....


https://www.facebook.com/tdebele1/posts ... 5370176884

free-tembien
Member
Posts: 1702
Joined: 02 Jul 2015, 20:56

Re: የትግራይዋ ዑመራ ከተማ ጉዞዬ የአይን ምስክርነት...... (ከጎንደር እስከ ሑመራ) - በሀወኒ ዳበሳ

Post by free-tembien » 22 Mar 2021, 21:36

brother eden, this is clearly a bad fiction. this is too aligned with tplf narrative to be true. this is fake news.

sarcasm
Senior Member
Posts: 11594
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

Re: የትግራይዋ ዑመራ ከተማ ጉዞዬ የአይን ምስክርነት...... (ከጎንደር እስከ ሑመራ) - በሀወኒ ዳበሳ

Post by sarcasm » 28 Sep 2021, 17:56

The engineers of the ethnic cleansing of Tigrayans in Western Tigray should be tried at ICC.

Axumezana
Senior Member
Posts: 19180
Joined: 27 Jan 2020, 23:15

Re: የትግራይዋ ዑመራ ከተማ ጉዞዬ የአይን ምስክርነት...... (ከጎንደር እስከ ሑመራ) - በሀወኒ ዳበሳ

Post by Axumezana » 28 Sep 2021, 18:29

As a correction Amharic was spoken freely in Humera up to the start of the war. Amhara shop owners were speaking in Amharic freely. In the areas that are inhibited predominantly by Amharas people were freely speaking in Amharic. This is an eye witness account!

Post Reply