Page 1 of 1

ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ!

Posted: 19 May 2020, 13:40
by Hameddibewoyane

ከሁሉ አስቀድመን በመቐለ ከተማ በጠራራ ፀሀይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ በታጠቁ ሀይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳድ የትግራይ ህዝብ መፅናናትን እንመኛለን::

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተዉ ገዳይና አሰከፊ የሆነዉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከህዝብ ጋር በመሆን የመከላከል እና ህዝብን የማዳን ስራ እተሰራ ይገኛል፡፡ በዚሁ ሁኔታ መንግሰትና ፓርቲያችን ዘርፈ ብዙ የሆኑ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወንና በመተግበር ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጉልህ ዘርፈ

ብዙ አወንታዊ ዉጤቶች ባሻገር የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች አብይ ፈተና ሆነዋል፡፡ በተለይም በግጭት አትራፊዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚፈጥሩትና በሚቀሰቅሱት ግጭቶችና ሁከቶች ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ሲቀጥፍ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ድርጊት ለህዝቦች ሆነ ለሀገራዊ አንድነት የማይበጅ እንዲሁም አሳዛኝ ድርጊት ነዉ፡፡

ህዝባችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች ህዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደምንገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።

ሆኖም መንግስት ከህዝብ ጋር በመሆን ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም የስጋት ደረጃና መጠኖችን በመመርመርና በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ፀረ ለውጥና ጸረ-ኢትዮጵያዊያን ሃይሎች ሆን ብለዉና አቅደዉ በተሳሳተ መንገድ ህዝቡን በማደናገርና ወደ ጥፋት ጎዳና ለመምራት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ይህንን አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ለግላዊ ጥቅማቸዉና ፍላጎታቸው ለማሟላት ህዝብንም ሆነ ሀገርን የሚጎዱ አስነዋሪና አጸያፊ ተግባሮችን በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰነባብቷል።

የትግራይ ህዝብ የቅርብ ሆነ የሩቅ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ጭቆናንም ሆነ አፈናን የሚፀየፍ ለኢትዮጵያ

አንድነት መስዋእት የከፈለ ህዝብ ነው። በትግሉና በመስዋእትነቱም ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ጉልህ ህዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ የተወጣና በመወጣትም ላይ ያለ ህዝብ ነዉ።

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋእትነት የሰላምና ዴሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ አለም

ብቻ እየሆነበት መጥቷል።

ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ህይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ዉስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነዉ፡፡ በሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነዉ የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የሀዘንና ውጥረት ድባብ ዉስጥ ይገኛል። ይህ ክቡር የሰው ህይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በህግ አግባብ ለማስጠበቅ ሃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈፀመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል። ይህም ድርጊት ብዙ መስዋእት ለከፈለ የማይገባዉ ነዉ፡፡ በመሆኑም የወጣቱ ግብረመልስም በክልሉ ሰላምና ዲሞክራሲ ጉዳይ

ላይ የኔ ጉዳይ ነዉ የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጐቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልፅ አሳይቷል።

እንደሚታወቀዉ በአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማሰፈፀም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና በህግ የማስከበር ተግባር ላይም የፀጥታ አካላት የላቀ ሰብአዊነት፣ ታጋሽነትና፣ ፍፁም ህዝባዊነትን የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል። የዲሞክራሲና የተሻለ የሰብአዊ መብት አያያዝ ልምድ ጉዳይ ከአስተምህሮት ስርፀትና ግልፅ ተጠያቂነትን ከማስፈን አሰራር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ሲሆን፤ ዜጎች በመንግስታቸው የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ክስተቶች አፈናና ግልፅ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል።

በተለይም እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ህይወታቸዉን

እስከመቅጠፍ የደረሰ የሃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው። ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው እርምት እርምጃ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን::

ይህ እኩይ ተግባር በተለይ በክልሉ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ፣ ይህን መሰል የአፈና ተግባር የክልሉ ወጣት ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መልኩ አጥብቆ እንዲታገለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በአጠቃላይ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉና በሀገር ደረጃ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ድጋፉ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

"ወደ ህዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ" እንደሚባለው፣ የገዢዎች የውድቀት ምልክት የሚጀምረዉ ወደ ህዝብ መተኮስ የጀመሩ እለት ነው። ስለሆንም በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ ባጋጠመው ክስተት፣ በክልሉ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የክልሉ ገዢ ፓርቲና መንግስት አካሄዱን ቆም

ብሎ እንዲመረምር አስገዳጅ ማንቂያ ደወል ነው። የትግራይ ብልፅግና ፓርቲም ጉዳዩን በአፅንኦት እንደሚከታተለውና ለሚመለከታችሁ ሁሉ በጥብቅ ያሳስባል።

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም የትግራይ ወጣት እና ለውጥ ፈላጊ ሃይል ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሆን የለውጥ ሂደቱን እንዲያፋጥኑ ከፓርቲያችን ጋር እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን:: ፓርቲያችን የትግራይ ህዝብ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሚገባዉን ጥቅም እንዲረጋገጥ እና ሃገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ይሰራል፡፡ በጥቂት ገዥ የህወሓት ቡድን በተለይ በዝምድና እና ጥቅም ትስስር እንዲሁም በሥልጣን ጥማት ምክንያት ትግራይን ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ለመነጠል የሚደረግ ስራም ሆነ ሴራ በጥብቅ የምንታገለዉና የምናወግዘዉ መሆኑን በጥብቅ እናሳዉቃለን::

በመጨረሻም ለሟች የዘለዓለም እረፍት፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ከልብ እንመኛለን።

ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ግንቦት 11/2012