Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 4639
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

መንግሥተ ገነት ዘእንስሳት ወአራዊት + (ከፈገግታ በላይ)* + ከጌታቸው ኃይሌ

Post by Meleket » 30 Jan 2020, 09:47

ይህችን ከዓመታት በፊት የተጣፈች ቁምነገረኛ ጥሑፍ ፕሮፌሰሩን እያመሰገናችሁ ተዝናኑባት እስቲ!!! ፕሮፌሰሩ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብተው ዳግም እንዲጽፏት ቢጠየቁ እንዴት ይጽፉት ነበር!?! :mrgreen:
መንግሥተ ገነት ዘእንስሳት ወአራዊት + (ከፈገግታ በላይ)* + ከጌታቸው ኃይሌ
እግዚኣብሔር ሰማይና ምድርን ከፈጠረ በኃላ ገነትን የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሞልቶባት “በውስጧ ያለውን ሁሉ ጨምራችሁ ግዟት ንዷት፥ ጠብቋት፥ ተንከባከቧት” ብሎ ለኣዳምና ለሔዋን ሰጣቸው። ሲሰጣቸው ሕግ ኣውጥቶ፥ ፍርድ እንዳያጓድሉ፥ ያንን ሕግ እንዳይጥሱ፥ ከጣሱ የገነት መንግሥታችውን እንደሚያጡ ኣስጠንቅቆ ነበር። ግን ገነትን የሚያህል ነገር ማጣት ምን እንደሆነ ኣልገባቸውም ይሁን፥ ወይም እግዚኣብሔር ጨክኖ ኣይጨክንባቸው መስሏቸው ይሁን ኣይታወቅም፥ የበለጠ ክብር ኣምሯቸው ሕጉን ጣሱ። “የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዲሉ ከገነት ተባረሩ፤ በዚያው ሳቢያ ገነትም ያለ ገዢ ቀረች።

ገነት ያለ ገዢ ስለቀረች በኣራዊቱና በእንስሳቱ መካከል ሽብር፥ ዝርፊያ፥ በጠቅላላው ሥርዓት ኣልባነት ነገሠ። በዚህ ጊዜ አያ አንበስ ተነሣና፥ ጋማውን ኣንዥርግጎ፥ “ይኼ ሥርዓት ኣልባ ሕይወት መቆም አለበት። ከዛሬ ጀምሮ ንጉሣችሁ እኔ ነኝ፤ ስትምሉ “አንበስ ይሙት”፥ ስትፎክሩ “የኣንበስ ባርያ”፥ ስትበደሉ “በኣንበስ አምላክ” በሉ፤ ጠዋት ተነሥታችሁ ለግጦሽ የምትወጡት ታማኝነታችሁን ለማረጋገጥ ሁላችሁም መጀመርያ ወደ “ዋሻ መንግስት” እየመጣችሁ እግር ከነሣችሁ በኋላ ይሁን” ብሎ ሕግ አወጣላቸው። አራዊት እንስሳት ስለሆኑ “ቤተ መንግሥት” በማለት ፈንታ ‘ዋሻ መንግሥት’፥ “እጅ ከነሣችሁ በኋላ” በማለት ፈንታ “እግር ከነሣችሁ በኋላ” ኣላቸው።

እውነትም ንጉሠ ነገሥት አፄ አንበሳ የገነትን ጸጥታ አስከበረ፤ ሽብር፥ ዝርፊያ፥ ሥርዓት አልባነት ቀረ። ግብሩን ግን አልቻሉትም። ንጉሠ ነገሥት አንበሳ በግብር መልክ ከነሱ ማህል የፈለገውን እየዘረጠጠ ይበላል። እነሱ ቀኑን ሙሉ ሣር ሲግጡ፥ ቅጠል ሲበጥሱ፥ ከእሾህና ከጥሻ ጋር ሲታገሉ እሱ ተኝቶ ይውላል። ከእንቅልፉ የሚቀሰቅሰው ረኅብ ብቻ ሆነ፤ ብድግ ይልና አጠገቡ ያገኘውን ዜጋ ይጥላል። “እባክህ አትፍጀን፤ እንደኛ ሣርና ቅጠል ብላ” ቢሉት፥ ሱስ ኣይለቅምና እምቢ አለ። እንዲያውም ይግረማችሁ ብሎ ከነሱ ማህል አንዳንዶቹን ደጋፊዎቹ ለማድረግ ሥጋ አስለምዶ የሚበላቸው የወገን ጠላት አበዛባቸው፤ እንዳያድሙበት እነዚያ ጥቅመኞች የማያላውሱ ሆኑ። “እርስ በርስ መባላት ይቅር” ብለው አብረው የሚያድሙ አራዊትና እንስሳት ቍጥር በዚያው መጠን ተቀነሰ፤ አሳባቂው በዛ።

ሣር-በላ አራዊቱና እንስሳቱ ኑሮ መረራቸው፤ ገነት ገነትነቷ ቀረ። የጨነቃቸው ሁሉ “አዳም ቶሎ ና” ማለት ጀመሩ። አዳም ቢመጣም ለራሱም በማን ዕድሉ? ቁፋሮው፥ እርሻው፥ ጕልጓሎው፥ አጨዳው ላቡን ጨርሶበታል። በዚህ ላይ ልጆቹ እርስ በርሳቸው እስከመጋደል እየተጣሉበት የተፈጠረበትን ቀን መርገም ጀምሯል። አዳም እንኳን ቶሎ ሊመጣ ቀርቶ ጥሪያቸውንም አልሰማ። ቢመጣም ገና የዛሬ አምስት ሺ ከአምስት መቶ ዓመት በኋላ ከሞት ተነሥቶ ለሌላ ዓይነት ሕይወት ነው እንጂ እነሱን ለማዳን ሊደርስላቸው አልተፈቀደለትም።

አንድ ቀን አያ አህዮ አፄ አንበሳ እንደተኛና ሥጋ ያስለመዳቸው ደጋፊዎቹ ወሐ ለመጠጣት ወደ ወንዝ እንደወረዱ ሲያይ፥ እነዝሆንን፥ እነአውራሪስን፥ እነቀጭኔን ሰብስቦ፥ የኣንበሳና የደጋፊዎቹ ራት ከመሆን የሚድኑበትን ዘዴ እንዲመካከሩና በኣድማ እንዲነሡ ሐሳብ አቀረበላቸው። ሐሳቡን ከአያ አህዮ በፊት ሌሎችም ሲያብላሉት የቆዩት ጉዳይ ነው፤ ግን እስከዚያች ዕለት ድረስ፥ ማንም አውሬ፥ ማንም እንስሳ እንዲህ ደፍሮ በይፋ አልተናገረውም። ዛሬ ድንገት ጉዳዩ በይፋ ሲወጣ ሁሉም ተደናግጠው፥ አፄ አንበስ ሥጋ መብላት ያስተማራቸው እነ አያ ጅቦ፥ እነ አቶ ተኵላ፥ እነ አያ ምጥማጥ እዚያ መኖር አለመኖራቸውን ለማወቅ ግራና ቀኝ እየተገላመጡ ማየት ጀመሩ። አያ ኣህዮ ነገሩ ገብቶት፥ “አይዟችሁ፤ ሰላም መሆኑን አይቼ ገምቼ አድብቼ ነው የጠራኋችሁ” ሲል አጽናናቸው፤ አበረታታቸው።

ወጣት አሳማ ተነሣና፥ “አያ አህዮ ሆይ፥ ይክንን ሐሳብ ደፍረህ ስላወጣኸውና ስላደፋፈርከን እናመሰግንሃለን። እኔ መቸም እስከ እርጅና አልኖርም ብዬ ተስፋ ቆርጨ ነበር፤ ብሮጥም ስድበለበል ከአምፋሩ ሳልደርስ እንደምያዝ አውቀዋለሁ። ለሁላችንም የዛሬይቷ ቀን የተቀደሰች ናት፤ እድሜ ላንተ፥ በዚች ቅጽበት በብዙዎቻችን የተስፋ ጮራ ተፈነጠቀብን። ዘመናችን ያፈራህ ደፋር የገነታችን ጀግና ነህ። በዚያ ላይ የትዕግሥት ባለጸጋና የማዳማጥ ችሎታ ያለህ መሆንህ ለማንም የታወቀ ነው። ስለዚህ በሐሳብህ ተስማምተን አንተን እንድናነግሥ ሐሳብ አቀርባለሁ” ብሎ ቁጭ አለ። ድኩላ ንጉሥ መለወጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ቢያምንበትም፥ የአያ አህዮን መንገሥ ከልቡ አልደገፈውም። “ለመሪነት ትዕግሥት አስፈላጊ ቢሆንም፥ ብቻውን አይበቃም፤ ሌላ ሌላ ተሰጥዎም ያስፈልጋል” ሲል ቅሬታውን ገለጸ።

አያ አህዮ ለካ መሪነቷን፥ በዙፋን ላይ መቀመጧን ፈልጓት ኖሮ፥ “ምንም አይደለም፤ የድኩላ ፍራቻ ይገባኛል። ሕግ ማስከበር ይሳነኝ መስሎት ነው። እርግጫ መቻሌን፥ ስቆጣም ድምፄ የሚያስደነግጥ መሆኑን ልብ ባይለው ይሆናል” አለና ስጦታውንና ችሎታውን ለማስመስከር ሁለቱን የኋላ እግሮቹን ወደኋላና ወደሰማይ ወርወር ወርወር አድርጎ ድምፁን ባፉም በኋላውም አስገመገመው። በዚያች ሰዓት መሪ ለመሆን ብዙዎች ቢያምራቸውም፥ ሥልጣንን ከአንበሳ እጅ ማላቀቅ በቀላሉ የማይቻል መሆኑን ስለገመቱ፥ በዚያ ላይ ሴራቸውን ሰላይ እንዳያውቅባቸው ስለሰጉም ክርክሩን ጊዜ ወስደው ብዙ ሳይገፉበት በአያ አሳማ ሐሳብ ተስማምተው ሥልጣንን እንዴት ከአፄ አንበስ እንደሚያወጡ መላ መምታት ጀመሩ።

“መንግሥት መገልበጥ በማስፈለጉና እኔ እንድመራችሁ ከተስማማችሁ እሱን ለኔ ተዉልኝ፤ ዘዴው ቀላል ነው። የሰበሰብኳችሁ ምን እንደማደርግ ቀደም ብዬ አስቤበት ነው። ዝርዝሩን አሁን እንዳልነግራችሁ፥ “ካፉ ከወጣ አፋፍ” እንደሚባለው ወሬው ከአንበስ ጆሮ ገብቶ ይጠነቀቃል፤ እንዲያውም ሊያጠፋን ይችላል” አላችው አያ አህዮ። በመጨረሻ ሁሉም በቀረበው ሐሳብ ሁሉ ተስማምተው ተለያዩ።

በማግስቱ ግጦሽ ከመጀመራቸው በፊት እንደተለመደው የገነት አራዊትና እንስሳት ንጉሡን እጅ ለመንሣት ወደ “ዋሻ መንግሥት” ግቢ ሄዱ። አድመኞቹ አያ አህዮን በዓያናቸው ቢፈልጉት አላገኙትም። “የአንበስ ቁርስ እንዳይሆን ቁርስ እስኪበላ ማረፋፈዱ ይሆን ወይስ አድማችን መሰማቱን ጠርጥሮ እኛን አጋፍጦ መጥፋቱ ነው?” እያሉ ብዙ አሰቡ። ለነገሩ እንኳን በሌሎቹ ቀናት ምን ጊዜ ይመጣ እንደነበረ አያስታውሱም፤ ከትናንት ጀምሮ ግን አያ አህዮ እንደተራ እንስሳ የሚታይ አይደለም። “የት ገባ? የት ወጣ?” የሚባል እንስሳ ሆኗል። እሱ ያረፈደው ለካ እነዚያ አፄ አንበሳ ሥጋ-በላ ያደረጋቸው ጥቅመኞች ሁሉ እግር ነሥተው እስከሄዱ ድረስ ኖሯል።

ሁሉም ከሄዱ በኋላ አያ አህዮና አያ ዝሆን መጡ። ንጉሠ ነገሥቱን ተኮፍሶ አገኙት። ለጥ ብለው እጅ ነሡት። ተመልሰው ሊሄዱ ሲዘጋጁ መጀመሪያ አያ አህዮ ፊቱን አዞረ። አያ ዝሆን ግን ከንጉሡ ትእዛዝ እንደሚቀበል ብጤ ኰስማና ታዛዥ መስሎ ከፊቱ ቆሟል። አያ አህዮ ፊቱን ያዞረው ቀደም ብለው የተመካከሩትን ለመፈጸም ነበረ። በምክክሩ መሠረት አያ አህዮ ድንገት በሁለቱ የኋላ እግሮቹ አንበሳውን ልብ እራሱን መታው። አንበስ ባላሰበውና ባልጠረጠረው ምት ልቡ ተሰውሮ ወደኋላው ሲዘረር ኰስማና ቢጤ ዝሆን “ዘራፍ” ብሎ ራሱ ላይ ቆሞ የራሱን አጥንት አደቀቀው፤ ወዲያው እልፍ ብሎ በአንበሳው አንጎል የተጨማለቀው እግሩን በሳሩ ላይ ጠራረገና “እፎይ” አለ።

በሥጋት ተወጥረው የነበሩ አድመኞች ሁሉ ወሬውን ሲሰሙ፥ አያ ዝሆን እስኪቀናበት ድረስ ለአያ አህዮ ጨፈሩለት፥ ዘፈኑለት። “ሺ ኣመት ንገሥ” ተባለ። እያንዳንዱ እየተነሣ “አዳም “ግዛ አብያለሁ” ብሎ ነገሠብን፤ አንበሳ “ንጉሣችሁ እኔ ነኝ” ብሎ ነገሠብን፤ አህያን ግን የመረጥነው እኛ ስለሆንን ክብር ይሰማናል” ብለው ፈነጠዙ። በነሱ ቤት ዲሞክራሲ መጀመሩ ነው። አህዮ በአንበሳ ዙፋን ላይ ተቀመጠና የኣስተዳደር ፍልስፍናውን ለዜጎቹ በአጭሩ ገለጸላቸው።

“ከዛሬ ጀምሮ በመሪና በተመሪ መካከል የደረጃ ልዩነት ቀርቷል። “ሺ ዓመት አስተዳድረን” ብላችሁ እንጂ “ሺ ዓመት ንገሥ” የምትሉትን አልቀበልም። አፄ፥ ንጉሥ፥ ልዑል፥ መስፍን የሚባሉ ተራ ዜጋን ከመሪው የሚለዩ የጌትነት መጠሪያዎች ካፋችን ብቻ ሳይሆን ከመዝገበ ቃላችን ጭምር ተፍቀዋል። የኔን ልጆች “ልዑል ግልገል”፥ “ልዕልት ውርንጪላ” ብሎ ሲጠራቸው የተገኘ መላሱ ይቆረጣል። አንዳችን ለሌላችን ጓደኞች ስለሆንን የምንጠራራው “ጓድ አህያ”፤ “ጓድ ውሻ” ወዘተ እየተባባልን ይሁን” አለ።

ሁሉም አጨበጨቡ። “አየ ፓለቲካ! አይ ባህያ ላይ ታይቶ የማይታወቅ አስተዋይነት!” እያሉ መሪያቸውን አደነቁ። እንግዴህ አሁን የመጀመሪያው ብሔራዊ የሥራ አጀንዳ እንዴት አድርጎ እነዚያን አንበስ ያባለጋቸውን ሥጋ-በላ አራዊት መቆጣጠር እንደሚቻል በውይይት ዘዴ መፈለግ ነው። ውይይቱ ለጥቂት ወራት በእኩልነት ሲካሄድ ቆይቶ ነበር። ነገር ግን ዜጎች ለባህል በመገዛት አያ አህዮ ባለፈ ባገደመ ቁጥር ነወር ስለሚሉ፥ ያ የተሾመ ዕለት በንግግሩ ያሳመረው እኩልነት ተረሳና አቅሙ የተመጠነ መሆኑን ረሳ፤ ከኩራቱ የተነሣ የሌሎቹን ሐሳብ መስማት ቀርቶ ሁሉንም ነገር ብቻውን ይወስን ጀመረ።

በማህል ቤት ኣንድ ሶሎግ ውሻ ተነሥቶ ለመናገር ጉሮሮውን ጠራረገ፤ መፍትሔ የሚያመጣ መስሏቸው በጉጉት ሲያዳምጡ፥ እንዲህ አለ፥ “እንዴት ነው መሪያችን እንደ ተራ ዜጋ “ጓድ” የሚባለው? “ታላቁ ጓድ” እንዲባል ሐሳብ አቀርባለሁ” አለ። ጉባኤው በሶሎጉ ንግግር ቢሳቀቀም ሐሳቡን ማንም ሊቃወም አልደፈረም። እንዲያውም መለማመጡ እየጨመረ ሄደ። ለመንደባለያው አመዱ ቀርቶ የጠጅ ሣር ተጎዘጎዘለት።

ያ ሶሎግ ውሻ ጥቂት ወራት ቆይቶ፥ እንዲህ ሲል ሌላ ነገር አመጣ፤ “እንዴት ነው መሪያችን እንደ ተራ ዜጋ ብቻውን የሚሄደው? ምንስ ቢሆን አህያ አይደለም? አጃቢ ያስፈልገዋል። እነ አያ ጅቦ ገና እግራችን አልገቡም። ደግሞስ አንዱ ተነሥቶ መንግሥት ለመገልበጥ ቢያስብ፥ አጃቢ ከሌለ ምን ይመክተዋል? እኛ የአንበሳን መንግሥት የነጠቅነው ታላቁ ጓድ ብቻውን ቢያገኘው አይደለም? አለዚያማ አህያ አንበሳን ያሸንፋል ብሎ ማን ያስብ ነበር? ደግሞም እኮ ለኛ ክብር ሲባል መሪያችን ወዲያ ወዲህ ሲሄድ የሚያጅበው፥ ሲተኛ የሚጠብቀው ዘበኛ ያስፈልገዋል” አለ። አሁንም ሐሳቡን የተቃወመ አልነበረም። እነ ማን ቢያጅቡት እንደሚገባ ሲያስቡ፥ ታላቁ ጓድ አህዮ፥ “እኔን የሚደፍር እንኳን አይኖርም፤ ለክብራችሁ ያህል ይሁን ካላችሁ ውሾች ያጅቡኝ” አለ። በዚህ ሁሉም ተስማሙ።

ከዚያች ጊዜ ጀምሮ አህዮን ማግኘት አልተቻለም። ባለ ጉዳይ ሁሉ ለውሾች ይሽቆጥቆጡ ጀመር። በውሾች ስለተጠበቀ አንበስ ያባለጋቸው ሥጋ-በላ አራዊት እሱን ማሥጋታቸው ቀረለት። ስለዚህ በነሱ ላይ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ የመፈለጉ ጉዳይ እየተነሳ ሄደ። ሁኔታው እየከፋ ሲሄድ ጊዜ ጥቂቶች እንደምንም ብለው ከታላቁ ጓድ አህያ ፊት ቀረቡና፥ “ታላቁ ጓድ ሆይ፤ ሺ ዓመት አስተዳድር፤ እነሆ አንተ በውሾች ስለተከበብክ አያሠጋህም እንጂ፥ እነዚያ ሥጋ-በላ አራዊት እኛን ዜጎችህን ሊጨርሱን ነው። እነሱን ለማጥፋት የወሰንነውን ውሳኔ ችላ ያልከው እነዚህ አንዴ ሥጋ አንዴ ቀጋ የሚበሉ በሁለት ቢላ-በላ አጃቢዎችህ ውሾቹ በሚሠሩት አሻጥር ይመስለናል” አሉት። በውሾቹ ያሳበቡት የደለሉት መስሏቸው ነው እንጂ ጥፋቱ የሱ መሆኑን አጥተውት አይደለም።

እሱ ግን አልተደለለላቸውም። በጥያቄያቸው ተቆጥቶ ምንም የማያውቁ የሚዳቋና የሰስ ልጆችን “የፍየል ወጠጤዎች ናችሁ” እያለ ከዝሆን ጋራ ሆኖ ረግጦ ፈጃቸው። ለነገሩ እነሱ የፍየል ወጠጤዎች አይደሉም እንጂ፥ ቢሆኑስ የፍየል ወጠጤ መሆን ምን ክፋት አለው? ብለው በትሕትና ቢጠይቁት፥ “አስቀያሚ አመዳም አህያ” ሲሉኝ ሰምቻችዋለሁ፤ እስከመቸ ነው በነሱ ተንቄ መልከ ጥፉ አመዳም አህያ ስባል የምኖረው” እያለ፥ የሰላሙን ጉዳይ ረስቶት ጭንቁ ሁሉ ስለራሱ መናቅ ብቻ ማሰብ ሆነ። ምንም ነገር ቢደረግለት ልቦናውን ወደ ቀና ነገር ማዞር አልተቻለም። ገነት መልኳ ጠፋ። ከአስተዳደር ጉድለት የተነሣ ቅጠሉም ሣሩም ተበልቶ አለቀና ምድር ራቁቷን ሆነች።

አራዊቱና እንስሳቱ የሚያደርጉትን አጡ። አንዳንዶቹ በአያ አህዮ ላይ ሸፍተው ጫካ ገቡና ቡድን ፈጥረው ትግል ጀመሩ። በበግ የሚመራ፥ በፍየል የሚመራ፥ በዝሆን የሚመራ፥ ወዘተ ቡድን ተፈጠረ። ከመሪው ግዝፈት የተነሣ ከሁሉም ተስፋ የተደረገበት በዝሆን በሚመራው ቡድን ነበረ። የትግሉ ዘመን እየጨመረ ሲሄድ የአህዮ ጠላቶች በመተባበር ፈንታ እርስ በርሳቸው መጣላት ጀመሩ። በማህል ቤት አንዳንድ ዝንጀሮዎች፥ ግመሎች፥ አህዮች፥ ጦጣዎች የአራዊትንና የእንስሳትን ድብልቅ ቡድን እየከዱ በዘርና በጎጥ ብቻ መደራጀት አመጡ። የተናቀው የጦጣና የደረጀው የዝንጀሮ ቡድን ሳይታሰቡ መጠናከር ጀመሩ። ከማህላቸው ጦጣና ዝንጀሮ ያልሆነውን ቀስ በቀስ በነቂስ አስወጥተው ኃይላቸውን አስተባበሩ። ወዲያው ከብሔረ ባዕድ ጋራ እየተላላኩ “ዘራችን ከጥንቱ እንደናንተው ነው፤ አያቶቻችን የመጡት እናንተ ከመጣችሁበት ከቀይ ባሕር ማዶ ነው” በማለት እየተዋደዱና እያጭበረበሩ የሚፈልጉትን በስጦታ መልክ ነጠቋቸው። ጦጣን በብልጠት ማን ችሎ። በዚህም ኃይል አግኝተው ሌሎቹን ቡድኖች እየዳጯቸው መጡ።

ሌሎች ቡድኖችን መዳጨት ብቻ ሳይሆን ታላቁ ጓድ አህዮ የዘረጋውን ሥልጣንም አናጉበት። ይኸ ዘር ለይቶ የመተባበር ነገር ያሠጋቸው አራዊትና እንስሳት ታላቁ ጓድ አህዮን በድፍረት እንዲህ አሉት፤ “ይኽን ሁሉ ጥፋት ያስከተለው ያንተ ተራጋጭነትና ምን አለብኝነት ነውና ለምን በፈቃድህ ሥልጣን አትለቅም? አለዚያም ይኽንን የኣህያ አመልህን መለስ አርገው። በአስተዳደርህ ጉድለት የተነሣ መሬት ሳትቀር ፍሬዋን ነፈገች፤ ያንን የምትወደውን ሰርዶ እንኳን ሳይቀር ማብቀል አቅቷት የምናቀርብልህ ከሌላ ሀገር በእርዳታ መልክ እያመጣን ነው” ቢሉት፥ ሥልጣት ጥሞት ይሁን ወይም በሥልጣን በመባለጉ ለፍርድ የሚቀርብ መስሎት ይሁን አይታወቅም “እኔ ሥልጣን ከለቀቅኩ ሰርዶም ቢሆን አይብቀል” ብሎ የጠየቁትን “እንዴት ደፈራችሁኝ” ብሎ አፍንጫ አፍንጫቸውን ረግጦ ፈጃቸው።

የጦጣና የዝንጀሮ የኅብረት ዘመቻ እየገፋ መጥቶ ከበራፍ ሲደርስ አህያ እንደልማዱ ፈረጠጠ። ግብር አበሮቹ እነ ዝሆን እግራቸውን ሰጡ። አህዮ እዚያ ማዶ ሆኖ የጓደኞቹን ወሬ ሲሰማ “እንስሳ እንዴት እግሩን ይሰጣል? አውሬ እንዴት እግሩን ይሰጣል? ቀንዳቸውን ምን ነካው? ጥርሳቸው እንዴት ዛለ?” እያለ እንደሱ ያልፈረጠጡትን ጓደኞቹን “ለምን አልተዋጉም፥ ለምን አልተራገጡም፥ ለምን አልተናከሱም” በማለት ሲያንፋ ይሰማል። በግርግር ገነት “ንጹሕና ታላቅ ዘሮች ነን” ከሚሉ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እግር ገባች።

አራዊቱና እንስሳቱ የአንበስንና የኣህዮን ዘመን ተመልሶ እንዲመጣ ባይመኙትም በዚያን ዘመን ያልነበረ ጉድ ስለመጣባቸው፥ “በአፄ አንበሳ ጊዜ፥ በታላቁ ጓድ አህያ ጊዜ ይኽ አልነበረም” ማለት ጀመሩ። የተቧደኑት ጦጦችና ዝንጀሮዎች የተራቆተ ኋላቸውን እየደበቁ “እኛ እኮ የእንስሳትና የአራዊት ወገን ተባልን እንጂ፥ እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ከእናንተ ይልቅ ለአዳም ልጆች እንቀርባለን። በአድጊ ላይ የተነሣነው በርእዮተዓለም ከእሱ የተለየን ወይም የተሻልን ሆነን አይደለም። በግራ ቢስነቱ ከሆነ ከእሱ ይልቅ እኛ እንበልጣለን” ማለትና አምላክ ለአዳም የሰጠውን የበላይነትና የገዢነት መብት መውረሳቸውን ቀስ በቀስ ማሳየት ጀመሩ። ገነት በሰሜን በኩል ተቆርጣ ለዝንጀሮዎች ጉልማ ተሰጠች፤ የቀረውን ለሁለት ያዙ። የጦጣ ዳኝነትና ፍርድ የተፈረደበትንም የተፈረደለትንም ሁሉንም እኩል አስመረረ። የገነት ልጅን ከገነት ልጅ አለያየ። የጎሪጥ እንዲተያዩ አደረጋቸው።

እንግዲህ አራዊትና እንስሳት ተለያይተን እንቀር ይሆን ወይስ ከኛ ማህል ጦጣን በዘዴ ማን በልጦ፥ እንደሌላው አውሬ መሆኗን አሳይቶ፥ ሁሉ አቀፍ የሆነ አራዊትና የእንስሳት መንግሥት ማቋቋም የሚችል ይነሣ ይሆን?” እያሉ ሲጨነቁ እንዴታ ይቻላል እንጂ!! እንዲያውም ጊዜው ሩቅ ኣይደለም” አለ የበጉ ኮርማ “የጦጣ ብልጣበልጥ ያለ አንድ ቀን አይበልጥ” እንደሚባለው ብልጠታቸው እንደ ተጋለጠ ኣይታችኋል፤ ብቻ ተከተሉኝ አላቸው።

አራዊቱም እንስሳቱም (ሌሎቹ ጦጣዎች ጭምር) በነቂስ ነቅተውባቸው፥ የበጉን ጥሪ ተቀብለው ከበቧቸው። እነሱም መከበባቸውን ዐውቀውት በመሽመድመድ ላይ ሆኑ። እንደ አህዮ እንፈርጥጥ ካለሉ፥ አሁን ያላቸው ሁሉንም የሚበጀው አማራጭ ንስሐ ገብተው፥ ከማንም በላይ አለመሆናቸውን ቢመርራቸውም ተቀብለው ውጠው በጉ (በግዑ) ካስተባበራቸው ከሌሎች ጋራ እየተመካከሩ በእሱም እየተመሩ መንግሥተ ገነትን በጋራ መገንባት ነው።

አሁን እንግዲህ በጉ አራዊቱንና እንስሳቱን እንደ እባብ ብልህ እንደ ርግብ የዋህ ሆኖ በማስተባበር በጦጣ ግዛት ላይ አስነሥቷቸዋል። መንግሥቱም በነቢያት ሳይቀር የተነገረለት የብሔረ ብፁዓን መንግሥት ይሆናል። ከነቢያቱ አንዱ ኢሳይያስ ነው፤ እንዲህ ይላል፤ በበጉ ላይ “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የዕውቀትና እግዚኣብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚኣብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ (ብቻ ሳይመረምር) አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደምትሰማ (ብቻ ሳያጣራ) አይበይንም። ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል። ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል። …. (በበጉ መንግሥትና አመራር፥ አንዱ ሌላውን ማጥፋት ቀርቶ፥) ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፤ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል፥ ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ ….። ላምና ድቡ አብረው ይሰማራሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ይተኛሉ። አንበሳም እንደበሬ ገለባ ይበላል” (ኢሳይያስ ምዕ.11፥ቍጥር2-7)።
………………………..
• ይዞታው የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ተምሳሌት ሲሆን የኣጻጻፍ ዘዴው ከባህልና ከኤዞፕ ተረቶች፥ ከፊልሳልጎስ፥ ከGeorge Orwell, animal Farm የተወሰዱ ናቸው።

Meleket
Member
Posts: 4639
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: መንግሥተ ገነት ዘእንስሳት ወአራዊት + (ከፈገግታ በላይ)* + ከጌታቸው ኃይሌ

Post by Meleket » 17 Jul 2025, 05:36

Meleket wrote:
30 Jan 2020, 09:47

Post Reply