ለረጅም ጊዜ በፈረንሳይ - ፓሪስ ከተማ የኤርትራ አምባሳደር ሆና ካገለገለችው፣ ከተከበረችው ክቡር አምባሳደር ሃና ስምኦን ጋር January 19 2020 በመርከብ ወደ ግብጽ አቅጣጫ ተጉዘን ነበር።
በመጉዋዝ ላይ ሳለን እንደው የልብ የልባችንን ስንጨዋወት በመካከሉ እንዲህ ስል ጠየቅሁዋት፣
"ሃኒቾ! አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ?"
እየሳቀች በመገረም አየችኝ።
መቸም "የተከበሩት አምባሳደር ሃና ስምኦን" ብዬ መጀመር አይጠበቅብኝም። የሻእቢያ ሰዎች እንዲህ ያለ ነገር አያውቁም። አንድ ተራ ወታደር ጄኔራል ስብሓት ኤፍሬምን "ወዲ ኤፍሬም" እያለ ሲጠራው መስማት የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ - አደግ እንደመሆኔ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያሉ ነገሮች በጣም ያስደነግጡኝ ነበር። ቀስበቀስ ግን ለመድኩዋቸው። እንዲያውም ተመቸኝ። ሃና እንዲህ አለች፣
"ትችላለህ። ጠይቀኝ!"
"ለመሆኑ በትግሉ ጊዜ በቀጥታ ውጊያ ላይ ተሳትፈሽ ነበር?"
ይህን የጠየቅሁዋት ቀበጥ የአዲሳባ ልጅ ነበረች ብዬ ስላሰብኩ፣ ቀበጥ የሊሴ ገብረማርያም (የፈረንሳይ ትምህርት ቤት ተማሪ) ናት ብዬ ስላመንኩ ነበር። ቤተሰብዋ የተቻለው እንደነበር ስላወቅሁ ነበር። ሃና መልስ ሰጠች፣
"ውጊያ ላይ ተሳትፌያለሁ። ማን ያልተሳተፈ አለ?"
ይህን ብላ ፈገግ አለች። በግራ በኩል የጥርሶችዋ ብልጭታ ተፈጥሮአቸው ልብ ይመታል።
ጥያቄዬ ቀጠለ፣
"በጥይት ተመትተሽ ታውቂያለሽ?"
ስቃ ዝም፣
"ስንት ጊዜ ተመታሽ?"
"ሶስት ወይም አራት ጊዜ ይሆናል።"
"ምንሽ ላይ ተመታሽ?"
"አንዱ ከጉልበቴ በታች ነው። ጥይቱ በዚህ ገብቶ በዚህ ወጣ" ብላ እግርዋን ነካካች።
"ልንካው?" ስል ጠየቅሁዋት።
ፈቀደችልኝ።
ሃዋርያው እና ተጠራጣሪው ቶማስ ሚስማር የገባበትን የእየሱስ ክርስቶስ እጅ በሌባ ጣቱ እንደነካው ሁሉ እኔም በሃና ስምኦን እግር ጥይት የገባበትን ጠባሳ በጠቁዋሚ ጣቴ ነካሁ።
"ሌላው እንዴት ነበር?" ስል ጠየቅሁዋት።
"RPG ነበር። ፍንጥርጣሪው መላ ደረቴን አለበሰው። አንገቴን ጭምር። እስካሁን ያልወጣ ፍንጣሪ ሰውነቴ ውስጥ አለ።"
እንዲህ ብዙ አወራን።
የRPG ፍንጣሪ የገባበት ደረትዋን ገልጣ እንድታሳየኝ ልጠይቃት አሰብኩና ተውኩት። ማለትም አፈርኩ። በተፈጥሮዬ አይናፋር ነኝ። እና አምባሳደር ሃና ደረትዋን ለማየት ብዬ ተንኮል ያሰብኩ እንዳይመስላት በሚል ጥያቄዬን ዋጥሁት።
ሆኖም እንደ ሰሜን ሱዳን ድመት ለስለስ ብዬ እንዲህ ስል ጠየቅሁዋት፣
"አሁን ያወራነውን ልጻፈው?"
ሃና እየሳቀች እንዲህ አለች፣
"አንተን ማመን መቸም በጣም አስቸጋሪ ነው። በርግጥ ያወራነውን ልትጽፈው ትችላለህ። ችግር የለውም። ዳሩ ግን ቅመም መጨመር አይፈቀድም!"
ሞቅ ያለ ሳቅ ሳቅሁ።
ቅመም ያልገባበት ጽሁፍ ልጽፍ እንደማልችል ሃና ገብቶአታል። በዚህም አደንቅሁዋት። ቅመም ያልገባበት ጽሁፍ ግን ከቶ እንዴት ስነ-ጽሁፍ ሊባል ይችላል?
----------
(ፎቶግራፍ:
- ግራ - ጸሃይነሽ።
- ቀኝ - አምባሳደር ሃና።
- ከሁዋላ የሚታየው ምጽዋን ከደርግ ነጻ ያወጣው ሰራዊት፡ሲሆን ሻማ በማብራት የተሰዉ ጉዋዶቹን በማስታወስ ላይ ነው።
- ሁለቱ የሻእቢያ ታጋዮች በኮረዳነታቸው ዘመን፣ በጦርሜዳ፣ ከደርግ ወታደሮች ጋር ላብ-በላብ ሳይሆን ደም - በደም እስኪሆኑ ድረስ በመትረየስ ሙዚቃ ደንሰዋል።)
Please wait, video is loading...

