ዛሬ በዋናነት ይህን ርእስ የቻልኩትን ያህል እንድል ከገፋፋኝ ዋናው ምክንያት በአክቲቪስት ዳንኤል ብርሃኔ በኩል የተሰነዘረው የህወሃት የመልስ ምት የማነሳቸው ጉዳዬች ስላሉኝ ነው::
ዳንኤል ብርሃኔ ሰኞ እለት December 30 2019, መልስ ለዶክተር አብርሀም በፃፈው ፅሑፍ ምን ያህል ተጠንቅቆና ተጠቦ እንደፃፈው ለመረዳት ብዙ ምርምር አያስፈልግም:: ፅሁፉ በተለያዩ ተዘርዝረው የቀረቡ የፕሮፖጋንዳ አምዶች የተዋቀረ ሲሆን አብርሀም በላይ ምን ያክል ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነ ውይይት ማድረጉ ገላጭ ፅሁፍም ነው ማለት ይቻላል::
1) ዳንኤል ብርሃነ ዶክተር አብርሃም በላይን ከከሰሰበት የመጀመርያው ነጥብ ልነሳ:: ዳንኤል ከንቱ የሆነ አብርሀም እንዳለው "extension” ጨምረው የህወሃትን አገዛዝ ለማስቀጠል እየተጉ ካሉ ፊታውራሪዎች ቅድምያ ተሰላፊ መሆኑን ልግለፅ: ዶክተር አብርሀም በንግግሩ ሁሉም የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ንግግሮች ወርቅ ነበሩ አላለም:: ሊታረሙ የሚገባቸው ጎጂ ቃላቶችና አባባሎች እንደነበሩ በግልጽ አስቀምጦታል ታድያ ዳንኤል ብርሃኔ ከአብርሃም በላይ የሰላ ትግራዋይ ለመምሰል አብርሃም ያላለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች እንከን እንደሌላቸው አድርጎ ለመሳል ለምን ፈለገ?
2) አብርሀም በግልፅ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሉት በበለጠ ባልተባለው ተቀጥሎ ስልጣን ለማስቀጠል ሲባል ሆን ተብሎ ተጣሞና ተቀጥሎ የተነገሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች እንቁጠር ቢባል ብዙ ናቸው:: አብርሀም ጥሩ ምሳሌ ሰጥቶ ነበር::
ለምሳሌ... ሌባ የህወሃት መሪዎች ሲባል የትግራይ ህዝብን ሌባ ብሎ አለ ብለው እነ ዳንኤልና መሰሎቹ ሲያራግቡ እንደነበሩ የሚካድ አይመስለኝም:: በአጠቃላይ በባለፈው ስርአት የተሰሩ መጥፎ ነገሮች ሲነሱ የትግራይ ህዝብ ስምን ለማጉደፍ ሆን ተብሎ እየተሰራ ነው የሚሉን የህወሃት አባላትና ቅልብተኛ አክቲቪስቶች እንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሙሉ ህዝብን እንደማይወክል አጥተዉት አይመስለኝም ነገር ግን እንደዛ ላላሉ ምልመላ ገላቸውን ሰለሚቀሩ ስልጣናቸውን ማራዘም ስለማይችሉ በውል ለነሱ የተባሉትን ንግግሮች ወደ ህዝቡ በማሻገር የመልስ ምት ፖለቲካዊ ግንባር ነድፈው እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ህዝብ የተረዳው ሃቅ ነው::
3- በዶክተር አብርሃም አፅንኦት ሰጥቶ ካነሳቸው ጉዳዬች አንዱ የኢትዮ-ኤርትራ ግኑኝነት በተመለከተ ነበር:: ዳንኤል ብርሃኔ መሰረታዊውን የሁለቱ አገሮች ሁልንተናዊ የግኑኝነት ጭብጥ ላለመንካት በመፈለግና የተለመደውን የ"extension” አጣጥሞ የማቅረብ ብርቱ ሙያውን መሰረት በማድረግ ዶክተር አብርሃምን ሲወቅስ ታዝብያለሁ :: በህወሓት በኩል "no war no peace policy” በኤርትራ የውጭ አገር ግኑኝነት ተግባራዊ ሲያደርግ የኤርትራ ህዝብ መሰረታዊ ጥቅሞች ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደነበር በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል:: ይባስ ብሎ የራሱ የሆነውን የትግራይ ህዝብ እንኳ በፖሊሲው እየደረሰበት የነበረውን መከራና ግፍ በአግባቡ ለመገንዘብ የስልጣን ጥሙ ዘግቶት እንደነበረው ሌላ ምስክር መጥራት የሚያስፈልግ አይሆንም:: ዶክተር አብርሀም በንግግሩ እንዳነሳው የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰላም በዋናነት መሻት የነበረበት ህወሓት ነበር:: የሚከፈለውን መስዋእትነት መክፈል የነበረበት እንዲሁም ህወሓት የተባለው ፓርቲ ነበር:: ነገር ግን ቀታ ነገሩ ሲመረመርና ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሚጀምርበት ጊዜ የተባለው ምን ነበር ? ትግራይን ያገለለ የሰላም ንግግር አንቀበለዉም በማለት የነበረውን “ No war No peace policy” የማስቀጠል ፍላጎት አልነበረምን? ዶክተር አብርሀም አካባቢውን ጠንቅቆ ከሚያውቁ እንዲሁም የችግሩን ክብድት በአግባቡ መዝነው መፍትሄ ለማምጣት እንደሚፈልግ ሰው ያነሳው ሃሳብ ህሊና ላለውና የሁልቱንም ህዝቦች መሰረታዊ ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ ድርጅት ሆነ ግለሰብ ሃሳቡን አጣጥሎ ይቃወመዋል የሚል እምነት የለኝም:: የራሱን ፍላጎት ዘወትር በማስቀደም የህዝብ ጥቅም ጉዳዩ ላልሆነ አካል ግን የዶክተር አብርሀም በቅን ልቦና የተሞላ የዳበረ ሃሳብ ምኑም አይደለም:: አንድ ነገር በደንብ ግልፅ ሊሆን ይገባዋል:: የኤርትራ መንግስት ከህወሃትና አመራሮቹ የበለጠ ጠላት የለዉም- ይሄ ጥሬ ሃቅ ነው:: እነዚህ አመራሮች የነበሩ ስህተቶች አርመው ለመማር ዝግጁ ያልሆኑ እንደሆኑ ደግሞ በተግባር አሳይተዉታል:: ስለዚህ ኢሳያስ አፈወርቂ አገሩን ወክሎ እንዴት ብሎ ነው ህወሓትን በስልጣን ላይ እያለ ወደ ትግራይ ደስ ብሎት ሊመጣ የሚችለው?
4) ዳንኤል በፅሁፉ ሲቀጥል አብርሀምን የህውሐት አማራጫቾችን በእድሜያቸው ምክንያት መውቀስ እንደማይችል ብዙዎቹ አሁን ያሉት የህወሃት አመራሮች እኩያዎቹ ወይም ከሱ የሚያንሱ እንደሆኑ ይገልፃል:: ይህንን ሃሳብም ላይ ከተዘረዘሩ ሃሳቦች ያላነሱ ተጣሞ የቀረበ የተለመደው ዶክተር አብርሀም እንዳለው " extension” የተቀጠለበት ከንቱ ቀረርቶ ነው:: ህወሓት እንደ ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ከአንጋፋ የፓርቲው ባለንብረቶች ተፅእኖ ነፃ ያልሆነ ድርጅት እንደሆነ ዶክተር አብርሀም ጠንቅቆ ይረዳዋል:: ዳንኤልም በደንብ ያውቀዋል:: ፓርቲው በግልፅ በዋናነት የሚመራው በነባር ታጋዬች ውስጣዊና ውጫዊ የተፅእኖ ፓለቲካ መሆኑ ለማንም ትግራዋይ ግልፅ ነው:: የ85 ዓመቱ ትግራዋይ ሙጋቤ ስብሃት ነጋ እና ወገኖቹ የትግራይን ፓለቲካ በነሱ ቅርፅ ለመፃፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛው የክልሉ የአመራር እርከኖች ያሉት ዋናውን የመወሰኛ ስልጣኖች የተያዙ በነባር ታጋዬችና ዘመዶቻቸው እንደሆኑ እየቆጠርን ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን:: ዳንኤል እሚፈልገው እሱ ከሆነ:: አሉ የተባሉት ወጣት አመራሮችም ራሳቸውን ሆነው ውሳኔ ሲያስተላልፉ የታየበት ወይም በልዩነት የወጡበት ጊዜ አይተንም ሰምተንም እናውቅም:: ስለዚህ ዳንኤል ብርሃኔ የቀድሞ የTPLF አንጋፋ አመራሮች ፓርቲ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ያነሰ እጅ ነው ያላቸው ብሎ ለመከራከር መሞከሩ ግልፅ ያለውን ራሳቸው እንኳ የማይክዱትን ሃቅ ሊከላከልላቸው እየሞከረ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል::
5) ዶክተር አብርሀም በግልፅ እንዳስቀመጠው ህወሓት ውስጣዊው ችግሮችን ለመደበቅ ሲባል ውጫዊ ችግሮች በማግዘፍ ህብረተሰቡ በተለያዩ ጠላቶች እንደተከበበ የውጭ ሃይሎች ሊያጠፉት እንደሆነ እየሰበከ እድሜውን ለማስረዘም ብቸኛ የሆነ ስትራተጂ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ግልፅ ነው:: ከሁሉም በላይ በጣም የሚያሳዝነው የህወሃት ተወካይ የሆኑ አባላቱ በፌደራል ደረጃ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አብረው የካቢኔ አባላት ሁኖ እያገለገሉ ባሉበት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የትግራይ ህዝብ እንዲሁም የህወሃት ጠላት ናቸው በማለት የወጣቱን ስሜት ለመቀስቀስ የሚከድበት መንገድ በትግራይ ህዝብ ክብርና አስተሳሰብ የሚቀልድ የማናለኝበት መንገድ መሆኑን መታዘብ ይቻላል::
እንደተለመደው ሁሉም የትግራይ ሚድያዎች በውስጥ ትእዛዝ ዶክተር አብርሀምን ቃለመጠይቅ እንዳታደርጉለት በማለት ቀጭን ትእዛዝ በአቶ ኣለም ገብረዋህድ በኩል እንደሚያስተላልፉ መናገር ይቻላል:: ብቻ ዳንኤልን አትደንግጥ ብሉልኝ:: ከዶክተር አብርሀም የባሱ ሌሎች የትግራይ ልጆች እንዳሉ ማሰብ ያስፈልጋል:: በቅርብም ይጠብቃቸው ዘንድ ምክሬ እለግሳለሁ: