


Abebe Gellaw
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አንድነትን ፈላጊ መሆኑ ብዙም አያጠያይቅም። ጽንፈኛ ብሄረተኞች የህዝብን ሰላም እያወኩ የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ በጣሉበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ጥራትና ብቃት ያላቸው ለህዝብና ለቆሙለት አላማቸው የታመኑ ህዝቡን የማደራጀትና የመምራት ብቃት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጎልተው መውጣት ነበረባቸው።
ባለፉት በርካታ አመታት የአንድነት ሃይሉን ለመወከል፣ ታግሎ ለማታገል ትንሽም ቢሆን ተስፋ ተጥሎበት የነበረው አርበኞች ግንቦት ሰባት ባለቀ ሰአት በራሱም ላይ አምነውት እስከ "በረሃ" ህይወታቸውን ለትግል ለመገበር በተከተሉት ላይ ሳይቀር ታሪክ ይቅር የማይለው ጉዳት አድርሶ፣ ኢሳትንም በመከራ ከደረሰበት ከፍታ አውርዶና አልከስክሶ ከሰምኩ አለ። በእርግጥ ድርጅቱ ከነበረበት የአመራር ውጥንቅጥ አንጻር የትም ሊደርስ እንደማይችል ግልጽ ነበር።
በዚህ ድርጅት ዙሪያ ከልባቸው ለህዝባቸውና ለአገራቸው ነጻነት ታግለው ያታገሉ እንደነ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉ በአርያነት የሚጠቀሱ ኢትዮጵያውያን፣ በርካታ ቅን አሳቢ አባላትም በአለም ዙሪታ ተሰባስበው የነበረ ቢሆንም የዛንው ያህል የቁጭ ይበሉ ፖለቲካ አራማጆችም ከልማት ይልቅ ለጥፋት ብዙ ቆምረውበታል።
ለ"አዲሱ" ኢዜማም ትልቅ ፈተና የሚሆንበት ከሰምኩ ብሎ ማስክ የቀየረው የግንቦቴ ልምድ ያካበቱ ቁማረተኞች ከበስተጀርባ የሚያራምዱት ለዘመኑ የማይመጥን ቁማርና የፍለጠው ቁረጠው ፖለቲካ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ትግል ተራ ሰበካና ቁማር ሲሆን ያታክታል፣ እምነት ያሳጣል።
ለማንኛውም የአንድነት ሃይሉን የሚወክል ከተራ የፖለቲካ ቁማር፣ ከአስመሳይነትና ቡድንተኛነት የጸዳ ታግሎ የሚያታግል ድርጅት ትናንትም ዛሬም አለመገኘቱ ትልቅ ኪሳራ ማድረሱን አምነን መቀበል ግድ ይለናል።
ስለዚህም ነው ሰሞኑን ደውሎ ኢዜማን ባደባባይ ደግፍ ብሎ ለነዘነዘኝ አንድ ቅን የግንቦት ሰባት ካድሬ በደፈናው በፈረንጅኛ ያልኩት "Give me a break!" ነበር።
