
የህወሓት ክፋትና ውሸት ልክ እንደ ሽቶ ለምደንዋል!!Seyoum Teshome
ህምምምም... እዚህ ሀገር በጣም ከሚያበሳጩኝ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋንኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃን ተብዬዎች የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪና ሥራ መረዳት አለመቻላቸው ነው። ይበልጥ የሚያበሳጨው ደግሞ ህወሓቶች ይህን ጠንቅቀው መረዳት እና በአግባቡ መጠቀም መቻላቸው ነው። "ህወሓት የኢትዮጵያ ካንሰር ነው" ስላቸው "የትግራይ ህዝብን ስለምትጠላ ነው" ይሉኛል። ይሄን ግዜ ምድረ አክቲቪስት ስዩም "የትግራይ ህዝብን ይጠላል-አይጠላም" በሚል አታካራ ይገጥማል። እኔ ያልኩት ግን "ህወሓት የኢትዮጵያ ካንሰር ነው" ነበር። ይህን ስል መከተል ያለበት "እንዴትና ለምን?" የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው። በሌላ ቀን ደግሞ "ህወሓት ብሔራዊ የደህንነት ስጋት (National Security Threat) ነው" ብዬ ስናገር አንድ የአምቦ ወዳጄ "አንድ ክልልን የሚያስተዳድር የፖለቲካ ፓርቲን 'ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ነው' ብለህ ትፈርጃለህ?!?" ብሎ ዘራፍ አለበኝ። ይህ ወዳጄ ሆነ አብዛኞቻችሁ የህወሓት አባላት እና አጨብጫቢዎች በእያንዳንዱ ቀን የሚናገሩትን እና የሚያደርጉትን ማሰብ፣ ማስታወስ እና መረዳት ተስኗችኋል። ምክንያቱም በእየለቱ በሚሰሩት ክፋት እና በሚናገሩት ውሸት የአብዛኞቻችሁ አዕምሮ ደንዝዟል። ይህን በማለቴ ይቅርታ! ነገር ግን ውሸትና ክፋት ልክ እንደ #ሽቶ ነው። መጀመሪያ ላይ በጣም ይሸታል። እየተደጋገመ ሲሄድ ግን ሽታው ይለመዳል። በመጨረሻ አፍንጫችን ሽቶውን ተላምዶ ማሽተት ያቆማል። ክፋትና ውሸትም ልክ እንደ ሽቶ መጀመሪያ ላይ ሲከሰት ብዙዎችን ያስቆጣል፥ ያስደነግጣል። እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ክፋትና ውሸቱን እየተላመደ ይመጣል። በመጨረሻ በእውን መከሰቱን ይዘነጋዋል። እኛም የህወሓቶችን ክፋትና ውሸት እንደ ሽቶ ሽታ ተላምደን ለምደንዋል። በመሆኑም በእየለቱ የሚሰሩትንና የሚያደርጉትን ማሰብ፣ ማስታወስና መረዳት ተስኖናል። ይሄ ደግሞ ለእነሱ በደምብ ተመችቷቸዋል። በእየለቱ እየዋሹ በየቦታው ያሸብራሉ!! ህዝቤ ሰው ሲሞትና ንብረቱ ሲቃጠል ብቻ ከእንቅልፉ ይነቃና ሬሳ እየቆጠረ ያላዝናል፥ ያለቅሳል። የህወሓትን ስራና ተግባር ልብ ብሎ ላስተዋለ ሰው ግን አሸባሪ ድርጅት እንደሆነ ጠንቅቆ ይረዳል። ይኼው ነው!!

