Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum

MatiT
Senior Member
Posts: 11549
Joined: 16 Feb 2013, 10:18

Re: የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭና የአገር ውስጥ ብድሮች ዕዳ 1.5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። ' ህውአት ኢትዮጵን የማትወጣበት በዘርና በእዳ ውስጥ ቀብሯታል'

Post by MatiT » 19 Aug 2019, 11:13

የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ የብድር ዕዳ ይፋ ሆነ
18 August 2019
ዮሐንስ አንበርብር
እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም. ድረስ ያለው የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭና የአገር ውስጥ ብድሮች ዕዳ 1.5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ብድር ዕዳ 111.9 ቢሊዮን ብር ነው

የሌሎቹ የልማት ድርጅቶች የውጭና የአገር ውስጥ አጠቃላይ የብድር ዕዳ 594 ቢሊዮን ብር ደርሷል

ማዕከላዊ መንግሥትና የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልመለሱት ዕዳ 412.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል

መንግሥት ከንግድ ባንክ የወሰደውን ብድር መመለስ ባለመቻሉ በየዓመቱ እስከ 25 ቢሊዮን ብር ወለድ እየከፈለ ነው

የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮችን የዕዳ መጠን የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ፡፡ ሪፖርተር ከሚኒስቴሩ ያገኘው ዝርዝር የዕዳ መግለጫ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ አገሪቱ እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያለባት ያልተከፈለ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ 1.5 ትሪሊን ብር ወይም 52.57 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

ከተጠቀሰው አጠቃላይ የአገሪቱ ዕዳ ውስጥ 26.93 ቢሊዮን ዶላር ወይም 769.08 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ የውጭ አበዳሪዎች ተገኝቶ ያልተከፈለ ዕዳ ሲሆን፣ የተቀረው 730.5 ቢሊዮን ብር ወይም 25.6 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ከአገር ውስጥ የመንግሥት ባንኮች ማለትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፣ እንዲሁም ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና (ጡረታ) ፈንዶች ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡

አገሪቱ ካለባት የውጭ ዕዳ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥት (Centeral Government) ዕዳ 449.7 ቢሊዮን ብር (15.73 ቢሊዮን ዶላር) ሲሆን፣ ቀሪው 319.3 ቢሊዮን ብር (11.17 ቢሊዮን ዶላር) ደግሞ የተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መንግሥት በገባላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ (Loan Guarantee)፣ ሌሎች ሁለት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ፣ በራሳቸው ከውጭ አበዳሪዎች በቀጥታ ተበድረው ያልከፈሉት ዕዳ ነው፡፡

ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ ከውጭ የተበደሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም መሆናቸውን ያመላከተው መረጃው፣ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ከውጭ አበዳሪዎቻቸው ያለ መንግሥት ዋስትና በቀጥታ ተበድረው እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያልከፈሉት ዕዳ 3.9 ቢሊዮን ዶላር ወይም 111.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሎሎቹ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገቡላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ በመጠቀም ከወሰዱት የውጭ ብድር ውስጥ እስከ ማርች 2019 ድረስ ያልከፈሉት የዕዳ መጠን 207.38 ቢሊዮን ብር (7.27 ቢሊዮን ዶላር) መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ ከላይ የተገለጸው እስከ ማርች 2019 ድረስ አገሪቱ ያለባትን አጠቃላይ የውጭ ብድር ዕዳ የሚያመለክት ሲሆን፣ እስከተገለጸው እ.ኤ.አ. ተመሳሳይ ወቅት ድረስ የተመዘገበው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ዕዳ ደግሞ 730.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃው ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ የአገር ውስጥ ብድር ዕዳ የሚመለከተው ማዕከላዊ መንግሥትንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ነው፡፡ በዚህም መሠረት የማዕከላዊ መንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ 343.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ 386.8 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለባቸው መረጃው በዝርዝር ያመለክታል፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ካለበት 343.5 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ዕዳ ከፍተኛው መጠን ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ ብድር የተወሰደ፣ እንዲሁም በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አማካይነት ከሁለቱ የሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና (የጡረታ) ኤጀንሲዎች፣ ማለትም ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የጡረታ ፈንድና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ መሆኑን ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደ ቅደም ተከተላቸውም 182 ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፣ 98.2 ቢሊዮን ብር በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አማካይነት ከሁለቱ የጡረታ ፈንዶች፣ እንዲሁም 26.5 ቢሊዮን ብር ከንግድ ባንክ ብድር ነው፡፡ የተቀረው በመንግሥት ቦንድ ሽያጭ አማካይነት ከልማት ባንክና ከሌሎች ምንጮች ተወስዶ እስከተገለጸው ወቅት ድረስ ያልተከፈለ የማዕከላዊ መንግሥት ዕዳ ነው፡፡ ከ730.5 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የአገር ውስጥ ዕዳ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመለከተው ተቀንሶ የሚቀረው 386.8 ቢሊዮን ብር ዕዳ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮ ቴሌኮም ወጭ ያሉትን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሚመለከት እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ልማት ድርጅቶቹን የተናጠል ዕዳ ዘርዝሮ አያስቀምጥም፡፡ ከልማት ድርጅቶቹ አጠቃላይ ዕዳ ውስጥ 386 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደ ሲሆን፣ 800 ሚሊዮን ብር ደግሞ የልማት ባንክ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

የመንግሥትን አጠቃላይ የዕዳ መጠንና ዝርዝሮቹን ከያዘው ሰነድ የተለያዩ ከፍተኛ ሥጋቶችን መመልከት የሚቻል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጤንነት አደጋ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡

ሰነዱ ከያዛቸው አኃዞች ምልከታ መረዳት የሚቻለው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በቀጥታ፣ እንዲሁም የመንግሥትን የዕዳ ክፍያ መተማመኛ ሰነድ (ቦንድ) በማስያዝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወሰዱት የረጅም ጊዜ ብድር፣ እንዲሁም ማዕከላዊ መንግሥት ከዚሁ ባንክ ተበድሮ ያልመለሰው የገንዘብ መጠን ድምር እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ 412.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ነው፡፡

እንደ ባንክ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ውጤታማነት መለኪያ ከሆኑት አንዱ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት መጠን፣ ባንኩ ከሰጠው አጠቃላይ ብድር መጠን ጋር የሚኖረው ምጣኔ ስለመሆኑ የባንክ ሙያ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ ማርች 2019 ድረስ የነበረው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 496 ቢሊዮን ብር ነበረ ሲሆን፣ ለግሉ ዘርፍ ያበደረውን ሳይጨምር እስከ ተጠቀሰው ወር ድረስ ለማዕከላዊ መንግሥትና ለልማት ድርጅቶች አበድሮ የተመለሰለት የብድር መጠን 412.5 ቢሊዮን ብር መሆኑ የባንኩን ጤንነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡

ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ይፋ ያደረገው ባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ አጠቃላይ መጠን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 541.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የሰጠው አዲስ ብድር 129 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ከሰጠው አዲስ የብድር መጠን ውስጥ 106.8 ቢሊዮን ብር መንግሥት የወሰደ ሲሆን፣ ቀሪው 22.2 ቢሊዮን ብር ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ነው፡፡

ባንኮች የሚሰጡት ብድር ስብጥር (Loan Portfolio) የገንዘብ ተቋማት ጤንነትን ለመለካት የሚያገለግል መሣርያ መሆኑን የሚገልጹት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች፣ አንድ ባንክ የሚሰጠው ብድር ሰፊ ስብጥር ወይም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ተበዳሪዎች መሆን እንዳለበት፣ የተበዳሪዎች ስብጥር ሰፊ መሆን በተበዳሪዎች ላይ ሊደርስ የሚችል የንግድ ኪሳራ መጠንን በዚያው ልክ በመቀነስ፣ በባንኩ ብድር ላይ ሊፈጠር የሚችል ተጋላጭነትን ለመከላከል እንደሚያስችል ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ንግድ ባንክ የሰጠው 412.5 ቢሊዮን ብር ለመንግሥትና ለአራት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች መሆኑ የብድር ክምችቱ በአንድ አካባቢ የተከማቸ እንዲሆን በማድረግ፣ ባንኩ ላይ ከፍተኛ ሥጋት እንዲያጠላ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በላይ የብድር ስብጥሩን እጅግ ጠባብ ያደረገው ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ከተሰጠው ብድር ውስጥ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ የተሰጠ መሆኑን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

ሪፖርተር ያገኘው አጠቃላይ የአገሪቱ የብድር ሰነድ መረጃ እንደሚሳየው፣ ማዕከላዊ መንግሥትም ሆነ የልማት ድርጅቶቹ ያለባቸውን የንግድ ባንክ ብድር ላለፉት አምስት ዓመታት ከፍለው እንደማያወቁ፣ ነገር ግን ከ17 ቢሊዮን እስከ 25 ቢሊዮን ብር ወለድ ላለፉት ዓመታት በየዓመቱ እየከፈሉ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡ ባንኩ ለስኳር ፕሮጀክቶች ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ቢሰጥም፣ በርካቶቹ ፕሮጀክቶች በማኔጅመንት ችግር መጠናቀቅ ባለመቻላቸው መንግሥት ባሉበት ሁኔታ በሽያጭ ወደ ግል ሊያዘዋውራቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች በብድር የፈሰሰውን 11 ቢሊዮን ብር ያባከነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ብድሩን መክፈል እንደማይችል በመግለጽ፣ ይህንን ጨምሮ በአጠቃላይ 57 ቢሊዮን ብር እንዲሰረዘለት ሰሞኑን ለመንግሥት ጥያቄ እንደቀረበ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ንግድ ባንክ ለመንግሥትና ለልማት ድርጅቶቹ የሰጠው ብድር ከፍተኛ መሆኑና የብድሩ መመለስን በተመለከተ ስለሚነሳው ሥጋት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና፣ ሥጋቱ ትክክለኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ባንኩ ለመንግሥትም ሆነ ለግሉ ዘርፍ የሰጣቸው ብድሮች እንደሚመለሱ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተበዳሪ የሆኑ የልማት ድርጅቶች ብድሩ እንዲሰረዝላቸው ስለጠየቁ ይሰረዛል ወይም ባንኩ ገንዘቡን ያጣል ማለት እንዳልሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ “ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እንዴት እንደምንሄድበት እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም ብድሩን ያበደርነው የመንግሥትን ዋስትና ይዘን ነው፤” ብለዋል፡፡

የአገሪቱን አጠቃላይ ብድር የያዘው መረጃ የሚያስገነዝበው ሌላው ጉዳይ፣ መንግሥት በአነስተኛ ወለድ የውጭ ብድር ቢያገኝ እንኳን በርካቶቹ የውጭ ዕዳዎቹ የክፍያ ጊዜ በማለፉ ወይም በመድረሱ ምክንያት የሚያገኘው አዲስ ብድር ተመልሶ ለዕዳ ክፍያ እየዋለ መሆኑን ነው፡፡ ለአብነት ያህል የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር እ.ኤ.አ እስከ ማርች 2019 ድረስ 2.2 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ብድር ያገኘ ቢሆንም፣ ለተገኘው አዲስ ብድር የአገልግሎት ክፍያ፣ ክፍያቸው የደረሱ ብድሮች ዋና ብድርና ወለዶች ተከፍሎ ወደ አገር የገባው የአዲሱ ብድር የተጣራ መጠን 700 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው፣ መንግሥት ካለበት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ብድር ውስጥ 182 ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የተበደረው መሆኑ አሳሰቢ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ መንግሥታት ከብሔራዊ ባንኮቻቸው በቀጥታ መበደር የሚችሉ ቢሆንም፣ የብድር ጣሪያው በሕግ መወሰን እንደሚገባውና ብድሩ በተወሰደበት በዚያው ዓመት መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲከፈል በሕግ ካልተደረገ በስተቀር፣ ውጤቱ ገንዘብ እንደማተም እንደሚቆጠር ይህም ኢኮኖሚው ያላመነጨው ተጨማሪ ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲሽከረከርና የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ያለ ገደብ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደርበት ሥርዓት አለ ማለት፣ ብሔራዊ ባንክ ማክሮ ኢኮኖሚውን ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ማስተዳደር አለመቻሉን እንደሚያሳይ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ መውሰድ የሚችለው የቀጥታ ብድር ጣሪያ በ2000 ዓ.ም. እንዲነሳ ከተደረገ በኋላ፣ ከብሔራዊ ባንክ ያለ ገደብ እየተበደረ መሆኑ አሁን ለሚስተዋለው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የራሱ ድርሻ ማበርከቱን አክለዋል፡፡

አንዳንዶቹ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች እስከ አንገታቸው ድረስ በዕዳ የተዘፈቁና ተጨማሪ ካፒታል እንዲያገኙ ቢደረግ እንኳን መዳን የሚችሉ ባለመሆናቸው፣ በሽያጭ ወደ ግል ተዘዋውረው እንዲተርፉ ማድረግ ለመንግሥት የቀረው ብቸኛው አማራጭ መሆኑን፣ ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውይይት ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ የሚሸጡትም ድርጅቶች ከላይ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁ መሆናቸው የተገለጸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡

FacebookTwitter


Post Reply