አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ሶማሌ ክልል ከመጓዝ ጨርሶ እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለተጓዥ ዜጎች መረጃ በሚያቀብልበት ድረ-ገፅ በትናንትናው ዕለት ባወጣው ማስጠንቀቂያ በክልሉ የብጥብጥ ፣ የሽብርተኝነት ፣ የእገታ እና የተቀበረ ፈንጂ ሥጋት እንዳለ ገልጿል።
ማስጠንቀቂያው ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ እና ጉጂ ዞኖች፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ምዕራብ ኦሮሚያን ወደሚያዋስኑ አካባቢዎች ለመጓዝ ያሰቡ እቅዳቸውን እንዲያገናዝቡ መክሯል። የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ እንዳለው በተጠቀሱት አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች ግጭት እና ብጥብጥ ሊኖር ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ በኬንያ፣ ሱዳን፤ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ የድንበር አካባቢዎች ተመሳሳይ ስጋት እንዳለ አስታውቋል። ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚጓዙ ዜጎቹም በአደጋ ጊዜ ለመድረስ ውስን አቅም እንዳለው ይዘረዝራል።
የካናዳ እና የብሪታንያ መንግሥታትም እንዲሁ ሰሞኑን ለዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል። የካናዳ መንግሥት እስካሁን ድረስ ፅኑ ባደረገው ማስጠንቀቂያ ዜጎቹ ወደ ኬንያ፣ ሱዳን፤ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ድንበሮች እና የደንከል በርሃ ጨርሶ እንዳይጓዙ ያስጠነቅቃል።
የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ወደ ጋምቤላ ክልል እና ሶማሌ ክልል ከመጓዝ እንዲታቀቡ ዜጎቹን አስጠንቅቋል። መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እና ከኬንያ ከምትዋሰንባቸው ድንበሮች መቶ ኪሎ ሜትሮች ያነሰ እንዳይቀርቡ ብሏል።