ኢሳይያስ እና አብይ!
ለመጀመሪያ ጊዜ የኢሳይያስን ስም የሰማሁት የአስር አመት ልጅ ሆኜ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ከአባቴ ከገብረአብ ሃብተጽዮን ጋር ወደ አዲሳባ ወደ አንድ የኤርትራውያን ጠበል ጠዲቅ (ማህበር) ሄደን ሳለ ሸምገል ያሉ ኤርትራውያን በሹክሹክታ ሲነጋገሩ እሰማ ነበር። ዝምተኛ ነበርኩ። መልኬ ደግሞ የዋህ እና ጅል ስለሚያስመስለኝ ያስተዋሉኝ አይመስለኝም።
በተፈጥሮዬ ትምህርት ቤት መሄድ የማልወድ፣ ማንኛውንም ስልጠና የምጠላ እንደ አውሬ ነጻ ፍጥረት ነበርኩ። በጠባይ ደረጃ እንደ በግ ነኝ። ማለትም ሊያርዱት ሲያስቡ የሚተባበር - አንገቱን የሚያመቻች። ተፈጥሮዬ አሁንም አልተለወጠም። ከሰለጠኑ ፈረሶች ይልቅ ያልተገሩ የሜዳ አህዮችን አደንቃለሁ። ዞረም ቀረ ትምህርት ቤት መሄድ ብጠላም ጭንቅላቴ የሰማውን ነገር ልቅም አደርጎ የመመዝገብ ችሎታው እጅግ አደገኛ መሆኑን አውቅ ነበር።
እና ትዝ ይለኛል።
ሽማግሌዎቹ ኤርትራውያን ማህበርተኞች በትግርኛ ሲጨዋወቱ "ኢሳይያስ አፈወርቂ" የሚል ስም ይደጋግሙ ነበር። በወቅቱ የእግርኩዋስ ጨዋታ ወሬ የገነነበት ስለነበር ኢሳይያስ የእግር ኩዋስ ተጫዋች ነበር የመሰለኝ።
ኢሳይያስን ለመጀመሪያ ጊዜ የጨበጥኩት ስሙን ከሰማሁ ከአርባ አመታት በሁዋላ ሲሆን፣ ኢሳይያስን ያስተዋወቀኝ ደግሞ አብይ አህመድ ነበር። መቸም ሁለቱ ሰዎች በህይወት ባይኖሩ ኖሮ ይህን ታሪክ የሚያምነኝ ባልተገኘ ነበር።
ነገሩ ወዲህ ነው. . .
አንድ ቀን አንድ እንግዳ ለማግኘት ወደ አስመራ ፓላስ ሆቴል ሄድኩ። አብይ አስመራ የመጣበት ቀን ነበር። ሪሴፕሽኑ አካባቢ ከእንግዳው ጋር እየተጨዋወትን ሳለ አሳንሰሩ ተከፈተ እና ሰዎች ሲወጡ አየሁ። በቅድሚያ ያየሁት ወርቅነህ ገበየሁን ነበር። ረጅም ስለሆነ ይሆናል በቅድሚያ የለየሁት። ቁመቱ 1.95 ሲሆን ኢሳይያስ 1.93 ነው። ከወርቅነህ በመቀጠል አብይን አየሁት። ወርቅነህ ሲያየኝ የሆነ ነገር ተናግሮ እየሳቀ መጥቶ ጨበጠኝ። ከአብይ ጋር አይን ለአይን ስንገጣጠም እንዳወቀኝ ፊቱ ላይ አየሁ። ተጨባብጠን ትከሻ ለትከሻ ስንሳሳም እንዲህ አልኩት፣
"ወደ ስልጣን ከመምጣትህ በፊት መጀመሪያ ስላንተ የነገረኝ ዶክተር ግሩም ላቀው ነው። ጅማ እና ቢሾፍቱ ላይ ተገናኝታችሁ እንደነበር ነግሮኛል። የአገር መሪ ከመሆንህ በፊት ስለ 'የቡርቃ ዝምታ' ያወራችሁትንም ነግሮኛል።" አልኩት።
(ነገ ይቀጥላል. . .)