ኢትዮጵያውያን በኤርትራ!
የኢትዮጵያ የጥበብ ሰዎች ለአንድ ሳምንት ኤርትራ እንደሚመጡ ስሰማ በሶስቱም ከተሞች ለመገኘት አስቤ ነበር።
ማለትም. . .
ከረን - ምጽዋ - አስመራ።
ሁዋላ ግን ዝግጅቱ በቴሌቪዥን በቀጥታ እንደሚተላለፍ ሳውቅ አሳቤን ቀየርኩ። እናም የከረን እና የምጽዋውን ዝግጅት በከፊል በኤርትራ ቴሌቪዥን አየሁ። ከሃመልማል እና ከስለሺ ደምሴ በቀር የማውቃቸውን አርቲስቶች አላየሁም።
የአስመራው ዝግጅት የት እና በስንት ሰአት እንደሆነ አላወቅሁም ነበር።
እና ዛሬ እሁድ ማለዳ እንደወትሮው ከልጆቼ ጋር በቲራቮሎ ጎዳና ላይ ስንሸራሸር ሁለት አረንጉዋዴ አውቶብሶች ከፊቴ ሲመጡ አየሁ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ባንዴራ ለብሰው ስለነበር አይኖቼ ተሳቡ። ወዲያውኑ ከአውቶብሱ መስኮት አንዳንድ እጆች ሰላምታ አቀረቡልኝ። እኔም ምላሽ ሰጠሁ። የሚያውቁኝ ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር።
እኔን የሚያውቁኝ እንግዲህ እነ ደረጀ እና ሃብቴ ነበሩ። እነ ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ እነ ጃምቦ ጆቴ፣ እነ ሃዊ ተዘራ ናቸው። እንዳልመጡ አውቄያለሁ። ከሃጫሉ ጋር አሜሪካ ሲልቨር ስፕሪንግ ተገናኝተን ነበር። ከጃምቦ ጆቴ ጋር በስልክ አውርተናል። እንደኔው የቢሾፍቱ ልጅ ነው። ሃዊ ተዘራን አግኝቻት አላውቅም። በጣም እንደምወዳት ግን ሰምታለች። "የኢትዮጵያ የጥበብ ሰዎች መጡ" ሲባል እኔ የማውቃቸው ይመጣሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር።
ለቡና ቁርስ የሚሆን እሸት በቆሎ ገዝተን ከልጆቼ ጋር ወደ ቤት እንደተመለስኩ ዶክተር ሳምሶን አባይ ደወለልኝ። መንደፈራ የህጻናት ሃኪም ሲሆን፥ በጣም ወዳጄ ነው። ታላቅ ወንድሙ ጌድዮን ይባላል። አሜሪካ ይኖራል። በአንድ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነው። እና ሳምሶን ደውሎ እንዲህ አለኝ፣
"ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች እየፈለጉህ ነው። ስልክ ልስጥህ?"
"ማነው የፈለገኝ?"
"አላውቅም። ስልክ ግን ሰጥተውኛል።"
እና ሳምሶን ስልክ ሰጠኝ።
ወዲያው ደወልኩ።
ስልኩን ላነሳው ሰው ስሜን በቀጥታ ስነግረው ወዲያውኑ እንደ ጥይት ጮኽ።
አህ!
ለካስ ጌቾ ነበር።
ጌታቸው ሃይለማርያም።
እኔም በስሜት ጮህኩ። ጥቂት አወራን እና ቀጥሮ ያዝን። በመቀጠል ሌላ ስልክ ተደወለልኝ።
የሴት ድምጽ ነበር።
ሃመልማል አባተ አይደለችም፣
"ማነሽ አንቺ?" አልኩ።
"እመቤት ወልደገብርኤል የምትባል ሴት ታውቃለህ?"
እንዲህ ስትለኝ ልወድቅ ምንም አልቀረኝ።
በየዋህነቱ ዘመን እመቤት በጣም ወዳጄ ነበረች። ገና ወደ ጥበብ ለመግባት ዳዴ ስትል ጀምሮ ጉዋደኛሞች ነበርን። እኔ 24 ነበርኩ። እስዋ ምናልባት 18 ብትሆን ነው። ያንጊዜ እኔና እመቤት ቁጭ ብለን ስናወራ ሰለዘር ምንም አሳቡ እንኩዋ አልነበረንም። ስለ ጥበብ ያበድን ንጹህ ወጣት ወፎች ነበርን።
የእመቤትን ድምጽ ስሰማ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት። የጥንትዋ እመቤት አልተለወጠችም። እንዲህ አለች፥
"አውቶብስ ውስጥ ሆኜ ከልጆችህ ጋር አየሁህ። ፈልጉልኝ ብዬ ሰዎችን በጠበጥኩ። ከኔ ቀድሞ ግን ጌች ስልክህን አገኘ። እንዴት ነው የማገኝህ?"
በረጅሙ ተነፈስኩ።
አህ!
እንደ ልጅነታችን ይሻል ነበር!
ምን ያህል ዘመን አለፈ? ስንት ነገር ተለዋወጠ? ለመሆኑ እመቤት ዘርዋ ምን ይሆን? አሁን ይህን ማሰብ ያስጠላል። ምክንያቱም እመቤትን የማውቃት ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ነበር። እመቤት ለኔ ዘር የላትም። ቅድስት ይገዙ፥ ሌንሳ ሲሜሶ ዴንጋ የመሳሰሉ ዘራቸውን የማላውቃቸው የልጅነት ጉዋደኞችም ነበሩኝ ። በእኔና በእመቤት መካከል ከቶ ፖለቲካ ሊገባ አይችልም።
እነሆ! ዛሬ ማምሻውን ሲኒማ ሮማ እሄዳለሁ። ጌቾ እና ኤሚን አገኛቸዋለሁ። የጥንቱን ውብ ዘመን እያነሳን ከመሳቅ በቀር ፖለቲካ ልናወራ እንደማንችል ግልጽ ነው።