(SMN 07/02/2012 ዓ.ም)
የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ የሲዳማ ብሔር ሕዝበ ውሳኔን ለማስፈጸም ያስችላል ያለውን የሕግ ማዕቀፍ አጸደቀ።
የሕግ ማዕቀፉ የጸደቀው በ168 ድጋፈ በ55 ተቃውሞ በ23 ድምፀ ታቅቦ ነው። የጉባኤው አባላት ለውሳኔ በቀረበውን የሕግ ማዕቀፍ ከማፅደቃቸው በፊት በርካታ ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በቀረበው የሕግ ማእቀፍ መሠረት የሀዋሳ ከተማ ተጠሪነቱ አዲስ ለሚቋቋመው ክልል ሆኖ፤ ነባሩ ክልል ግን ወደፊት አማራጭ የአስተዳደር ከተማውን እስኪያመቻች ድረስ ለሁለት አገራዊ የምርጫ ጊዚያቶች ከተማውን ከአዲሱ ክልል ጋር በጋራ እንደሚጠቀም ተመልክቷል። በነባሩ ክልል ባለቤትነት ስር የቆዩ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ሀብቶችን በተመለከተም በአገሪቱ የንብረት ክፍፍል ሕግ መሠረት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሲዳማ ብሔር ሕዝበ ውሳኔን ለማስፈጸም ያስችላሉ ያላቸውን አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች አንዲቀርብለት በተደጋጋሚ የክልሉን መንግሥት መጠየቁ ይታወሳል። በደቡብ ክልል የሲዳማ ብሔር የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት ለቦርዱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በሕዝበ ውሳኔው የሁሉንም አካላት ጥቅምና ፍላጎት ለማጣጣም የሚያስችሉ አስተዳደራዊና የሕግ ማዕቀፎችን በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ በቅርቡ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ምንጭ:- Dw Amharic
https://www.facebook.com/pg/sidamamedia ... e_internal