የአማራ ክልል የደህንነትና ፀጥታ ምክር ቤት መግለጫ
የአማራ ክልል ደህንነትና ፀጥታ ምክር ቤት ማንኛውም የኃይል እንቅስቃሴን የኃይል ርምጃ በመውሰድ መቆጣጠር፣ አንደሚገባ አመለከተ፡፡ ማንኛውም በኃይል ተግባር የተሠማራ ቡድንና ግለሰብ እስከ ጥቅምት 20 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል።
አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:56
ኃይል እንቅስቃሴን የኃይል ርምጃ በመውሰድ መቆጣጠር ይገባል ተባለ
ምክርቤቱ ትናንት ባወጣው መግለ እንዳመለከተው የቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር ማንነትን ሽፋን በማድረግበ ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በሚፈጠር ግጭት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ አካል መጉደሉንና መፈናቀልና እንግልት መድረሱን እንዲሁም ንብረት መውደሙን በስፋት አትቷል፡፡ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ተፈትቶ እያለ በብሔረሰቡ ስም የተደራጀው ኮሚቴ አሁን የተከተለው አቅጣጫ ከሰላም ይልቅ ፍላጎትን በኃይል በብሔረሰቡና በክልሉ መንግስት ላይ የመጫን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደርና ጎንደር ከተማን ጨምሮ እየተፈፀመ ያለው ድርጊት የዚህ መገለጫ መሆኑን መግለጫው ጠቁሞ ይህን ድርጊት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ እናዳልሆነም አመልክቷል፡፡ በመሆኑም «ማንኛውም የኃይል እንቅስቃሴን የኃይል እርምጃ በመውሰድ የሰው ሕይወትና ንብረትን ከአደጋ ማዳን፣ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉትን በኃይል መቆጣጠር፣ ለሕግ ማቅረብ፣ ተመጣጣኝ የኃይል ርምጃን በመውሰድ የኃይል ተግባርን ፍፁም እንዳይቀጥል ማድረግ፣ተገቢ ነው» ሲል ገልጧል፡፡
በተለያየ ምክንያትና ሰበብ ተደናግሮም ይሁን በንቃት በኃይል ፍላጎትን ለማሳካት በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ የነበረውን ኃይል፣ ቡድንና ግለሰብ እስከ ጥቅምት 20 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የክልሉ መንግሥት በድጋሜ ይቅርታ ማድረጉም በመግለጫው ተመልክቷል። በጉዳዩ ዙሪያ ዶይቼ ቬለ ያነጋራቸው በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማዕረግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን በበኩላቸው መንግስት ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል መግለጫ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
የመግለጫውን ወቅታዊነት በተመለከተም አቶ መርሐጽድቅ ከዚህ በላይ መታገስ መንግስትን ዋጋ ያስከፍለዋል በመሆኑም መግለጫው ወቅቱን ጠብቆ የወጣ ነው ብለዋል፡፡
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ቻላቸው ታረቀኝም መግለጫው ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ዜጎችን ከሞት፣ ከመሰደድና ከእንግልት እንደሚታደጋቸው አመልክተው፤ ችግሮች ካሉም በውይይትና በሰላም መፍታት ያስፈልጋል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግስት በተሳሳተ መንገድ የሚሄዱ ወገኖችንም በይቅርታ እንዲመለሱ መፍቀዱ መልካም እድል መሆኑን አቶ ቻላቸው ተናግረዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ የጦር የመሣሪያ የታጠቁ ሰዎችንም ክልከላ ማድረጉ ተገቢና ወቅታዊ ርምጃ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቻላቸው “መንግስት ትጥቅ ሊያስፈታ ነው” የሚለው ስሞታም ሚዛን አይደፋም ብለዋል። ወደ ግጭት የገቡ ቡድኖች እና ግለሰቦች በአስቸኳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመመለስ ያሏቸውን ልዩነቶች እንዲፈቱም የአማራ ክልል ደህንነትና ፀጥታ ምክር ቤት ጥሪ አስተላልፏል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ
https://www.dw.com/overlay/media/am/%E1 ... 0/50875366