ብልፅግና የሚያወራለት ምክክር ከምርጫ የበሳ የጨረባ ሆኗል። ተሳታፊ ተብለው የሄዱት ራሳቸው ምክክር ተደረገበት የሚባለውን ምን እንደሆነ አያውቁትም!
1) ተሳታፊዎችን በቡድን ከፍለዋቸዋል። በቡድን የተመደቡት ተሳታፊዎች አንድ አጀንዳ ይሰጣቸዋል። የሚሰጣቸው አጀንዳ ደግሞ ቢከራከሩ ለውጥ የማያመጡበት፣ አገዛዙ ላይ ምንም አይነት ጫና የማይፈጥር ከሆነ ብቻ ነው። ከተመደቡበት ውጭ ባለው አጀንዳ አያገባቸውም ተብለዋል። ለአብነት ያህል ከአማራ ተወካይ የተባሉት ብዙዎቹ ከጉልህ የአማራ ጥያቄዎች ይልቅ አጨቃጫቂ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንዲመደቡ ተደርገዋል። ለምሳሌ ያህል የኃይማኖት አባቶች ሊመክሩበት የሚገባው ኃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ የእምነቱ እውቀት የሌላቸውን አካላት መድቦ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ እንዳይደርሱ አድርጓል። የአዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች ዋና ጉዳዮች ላይ ኦህዴድ ብልፅግና ጥቅምና አካሄድ ይደግፋሉ ያላቸውን ነው የመደበበት።
2) በየቡድኑ የተመደቡትም መካከል ኦህዴድ ብልፅግና እያገኘ "አቅጣጫ" የሚሰጣቸው እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚያነሳውን በማጥናት የሚያስተካክሉ ሰዎች የተመደቡበት ነው።
3) በርካታ ጉዳዮች ምክክር የተባለው ከመጀመሩ በፊት ብልፅግና አቋም የያዘባቸው ናቸው። በዚህ "አቅጣጫ" መሰረት ነው ያስቀመጣቸው ሰዎች ምክክር ተብየውን የሚመሩት።
እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ወዘተ ብለው የሚያደርቁት መድረክ ተሳታፊ የተባሉት እንኳን አጀንዳ ተከልላ ተሰጥታቸው ነው ጉንጭ አልፋ ክርክር የሚያደርጉት። ዋና ዋና የተባሉ ጥያቄዎች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ሌሎች እንዳይሳተፉ ተደርገዋል።
ለይስሙላህ አዳራሽ ውስጥ አስገብተው መሰረታዊ ያልሆኑ፣ ሌሎች ባለድርሻዎች በደንብ ሊወያዩበት የሚችሉት አጀንዳ ላይ ጠምዶ የራሱ ብሎ የሚያስባቸው አጀንዳ ላይ ደጋፊዎቹን አሰልፏል። ይህ ምርጫ ላይ ከሚያደርጉት በከፋ የጨረባ አካሄድ ነው። ቢያንስ በምርጫ ወቅት እንኳን አጀንዳዎቹ ላይ በሚዲያ ክርክር ይደረጋል። ምክክር በተባለው መርጠው አጀንዳ ይሰጣሉ። መርጠው ተወያይ ይመድባሉ። እየሆነ ያለው ይህ ነው! የጨረባ ነው!
በአጭር ምሳሌ!
ለ50 ተማሪዎች መቶ ጥያቄ ያለው ፈተና ታወጣለህ!
እያንዳንዱ ተማሪ ሁለት ሁለት ጥያቄ ብቻ ይመልሳል።
በተናጠል ያረምክላቸውን 50 ተማሪ የመለሰው እያንዳንዱን ጥያቄ መቶ ታደርገዋለህ። እያንዳንዱ 98 ጥያቄ ሳይሰራ ተፈቶኖ አለፈ ትለዋለህ። ይህ ፖለቲካ ሲሆን ደግሞ ምክክር የተባለው መድረክ ማለት ነው!
የቡድን አላማቸውን ለማስፈፀም ጥድፊያ ላይ ናቸው!
1) የኦህዴድ ብልፅግና ምክክር ኮምሽኑን የሚያይበት የሚጠቀምበትም ሌሎች ምክክሩ ይጠቅማል ከሚሉት፣ ምክክሩን ከሚያዩበት በተቃራኒ ነው። የፈለጉት እስካሁን ጀምረዋቸው ላልጨረሷቸው ፕሮጀክቶች ህጋዊ ሽፋንነት መስጠት ነው። የአገሬው አርሶ አደር "አንድ ሰኔ የነቀለውን ሰባት ሰኔ አይተክለውም" እንደሚለው ኦህዴድ ብልፅግናም በዚህ ወቅት በተቀናቃኞቹ ላይ በምክክር ስም የሚያደርገው ብልጫ ለአመታት የማይካካስ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ጥድፊያው። በአንድ ወሳኝ የፖለቲካ ሰኔ ተቀናቃኞችን ከፖለቲካ ትርክት፣ ስልጣንና መሰረታዊ ጥያቄዎች አርቆ የክፍለ ዘመን የፖለቲካ ሰኔ እንዳይክሳቸው ማድረግ ነው። እስካሁን ያሰባቸውን ሁሉ በኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ስም ዶሴ የሚዘጋበት ነው።
2) ይቀናቀኑናል የሚሏቸውን የፖለቲካ ሃይሎችና ማህበረሰቦች በጦርነት ጠምደዋል። በርካቶችን አስረው፣ ቀሪውን በተለያየ መንገድ ከጨዋታ ውጭ አድርገዋል። ዳያስፖራው ኩርፊያ ላይ ነው። በዚህ ወቅት ተረጋግቶ ምክክር ወዘተ ሊያደርግ የሚችለው የተደራጀው፣ ስልጣን አስጠባቂው ኃይል ነው። ሌላው ትኩረቱ ጦርነት ላይ ነው፣ በአጀንዳ አለመግባባት ይተራመሳል። ሌላው ኩርፊያ ላይ ነው። ይህን የሌሎችን ትርምስና ተረጋግቶ አጀንዳ አለማስያዝ፣ ከመድረክ ማራቅ ኦህዴድ ይፈልገዋል። አሸንፋለሁ የሚለው በዚህ መንገድ ነው። ኦህዴድ በክፈለ ዘመን የማይገኝ እድልን በጥቂቶች ታጅቦ የሚሮጥበት መድረክ ለማሳካት ሌላው በትርምስ ውስጥ መሆኑን ይፈልገዋል። ኦህዴድ ብልፅግና "በጊዜ የለም" መርህ እየሰራ ያለው ይህን ሌሎች በትርምስ ውስጥ፣ እሱ በአንፃራዊነት አጀንዳ ለመምራት ያለውን እድል አሟጦ ለመጠቀም ነው።
3) ሌሎች በትርምስ ውስጥ ባሉበት በዚህ ወቅት ኦህዴድ ብልፅግና ሌሎቹን ከአጀንዳ አርቆ ለዘመናት ስልጣንና ትርክት የሚቆጣጠርበትን አጀንዳ "አርቀን እንስቀለው" ብሎ እየሰራ ነው።
መርሁ “ተቀናቃኞቻችንን በጦርነት ጠምደንና እረፍት አልባ አድርገን አጀንዳቸውን አርቀን እንቅበረው፣ የእኛን አጀንዳ አርቀን እንስቀለው” በሚል መርህ እየተመሩ የገቡበት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ “አሁን በደንብ ከነቀልናቸው መልሰው ለማንሰራራት ብዙ ጊዜ ይጠይቃቸዋል፤ ላያንሰራሩም ይችላሉ፤ እስከዚያ እኛ ተጨማሪ ስራዎችን እንሠራለን” ብለው በሚያምኑት መሰረት ነው እየሰሩ ያሉት። "አርቀን የቀበርነው የሌሎች አጀንዳ እስኪወጣ፣ እኛ አርቀን የሰቀልነውን እስኪያወርዱ ዘመናት አይበቃቸውም" ብለው ነው እየሰሩ ያሉት።
4) ይህ የምክክር ጉዳይ ለብልፅግና የአገር ችግር መፍቻ አይደለም። የአገር ጉዳይ በዚህ ወቅት ጉዳያቸው አይደለም። ቅድሚያ መቀመጫዬን እንዳለችው እንስሳት ቅድሚያና ቅድሚያ ስልጣንና የቡድን ጥቅም ከዛ እነሱ የሚበይኑት፣ እንደፈለጉ የሚያደርጉት፣ በእነሱ የጥቅምና ትርክት ማዕቀፍ የሚሽከረከር የኢትዮጵያ ጉዳይ ሊሰሩ ይችላሉ። ይህ አጣዳፊ ጉዳያቸው አይደለም።
5) ይህ ምክክር የሚሉት እስካሁን ያላሳካቸውን አላማዎቹን ማሳኪያ የትግል ግንባር ነው። “የትኛውንም መንገድ ተጠቅመን የምንፈልገውን ካሳካን፣ የተከልነውን ስርዓት፣ ያቆምነው መዋቅርና ያወጣነውን ህግ ለመሻር ጊዜ ይወስዳል፤ የሆነ ጊዜ ቢሻር እንኳን ሙሉ በሙሉ አይሆንም” የሚል አቋም ይዘው እንደሚሰሩ ይታወቃል፡፡ አገዛዙ ይህን አላማውን ለማስፈፀም ለአባላቱ በተደጋጋሚ የሚነግራቸው “መፍጠርና መፍጠን” የሚል መፈክር ነው።
በኮሚሽኑ ውስጥ ለሀገራቸው በጎ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዓላማ የነበራቸው አካላት የሉም ማለት አይደለም፡፡ አሉ፡፡ ሆኖም ከኦህዴድ ብልፅግና ሸፍጥና አካሄድ አንፃር ተቋሙ እንደ ተቋም እና ብዙሃኑ የኮሚሽኑ አባላት የኦህዴድ ብልፅግና ጉዳይ አስፈፃሚዎች መሆናቸው የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡
የምክክር ኮሚሽን የሚቋቋመው ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎች እንዲሽሩ መንገድ ለመፈለግ ነው፡፡ ያደረጉ አከራካሪ የታሪክና የትርክት ጉዳዮች በነጻነት እየተነሱና ውይይት እየተደረገባቸው የጋራ መፍትሄ እንዲበጅላቸው ለማድረግ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጋራ አማካይ (mean) የሚባለውን በመፈለግ ሁሉም የእኔ የሚላቸውን ህጎችና መዋቅሮች ለማደራጀት ነው፡፡ የኦህዴድ ብልፅግና ድራማ ግን በጥያቄ ላይ ጥያቄ የሚጨምር፣ በችግር ላይ ችግርን የሚደራርብ፣ ተጨማሪ የጦርነትና ትርምስ ምክንያቶችን የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ኦህዴድ ብልፅግና እየሰራ የሚገኘው እስካሁን የጀመራቸውን የስልጣን፣ የሀብትና ትርክት ቅርምት፣ ተቃውሞ ያስነሱበትን አካሄዶች፣ ተቃውሞ ያስነሱብኛል ያላቸውን ጉዳዮች ብዙሃንን አሳትፈናል በሚል ማህተም ማስመታትና ህጋዊ ሂደት አስመስሎ ለማቅረብ ነው። ይህ ሁሉ ጥድፊያ ይህን የቡድን አላማ ለማስፈፀም ነው።
TO READ MORE ARTICLS ON TIS ISSUE : https://www.facebook.com/Getachew.Shiferaw.Offical

