እንኳን ለዚህ ቀን አበቃችሁ
ከፊታችሁ በመቆሜ ታላቅ ክብር ይሰማኛል
ታሪክ የራሱ ነፍስና የራሱ ረቂቅ የስሌት ቀመር አለው። ከነመፈጠራቸው የማይተዋወቁ ሁለት ሰዎችን በራሱ ልብ መርምሮ፥ በራሱ ቀመር አንጥሮ ከየጥጉ ጎትቶ አምጥቶ ለአንድ ወርቃማ አላማ ሲል ያገናኛቸዋል። እናም ለብዙሃኑ እውነትና ነፃነት እንደጧፍ ያበሩ ዘንድ በፍቅር ያሰልፋቸዋል። ይበራሉ።በድቅድቅ ጨለማ መሃል የተስፋ ብርሃን የነፃነት ወጋገን ይሆናሉ።ይህ አስበው የማይዘልቁት የታሪክ ጥልቅ ምስጢር ነው።ታሪክ እኔንና እናተንም በዚህ ዘመን በዚሁ ስሌት ለአንድ ወርቃማ የትውልድ ፕሮጀክት አገናኝቶናል።ዛሬ እየታገልን ነው፥ነገ እናሸንፋለን።የአማራን ቀን እናመጣለን።
በድጋሜ እንኳን ደስ ያላችሁ
ህልውናችን እስካልተረጋገጠ ድረስ የዛሬ አምሳ አመት በዚህ ቦታ ላይ ሌላ አማራ ቆሞ፥ ሁልጊዜም ስለመሰልጠንና ስለመዘጋጀት አስፈላጊነት ሊናገር ይችላል።መደራጀታችን፥ መሰልጠናችን፥ መታጠቃችንና ለህልውናችን መታገላችን የሚቆመው ህልውናችን የተረጋገጠ እለት ብቻ ነው።ይህ የዛሬው የእናንተ ምርቃት የአማራ ህዝብ ትግልና የሃገሪቱ እጣፋንታ ተገፍቶ አንድ ጫፍ ላይ የቆመበት ምእራፍ ላይ የሚደረግ ነው። ስራ የሚጠይቅ የድል ታዛ ላይ የቆመ እጅግ አጓጊ ምእራፍ ነው ።
ውድ ጓዶቼ በዚህ አጋጣሚ አደራ ልላችሁ የምፈልገው ብዙ ጉዳይ አለ፦
ዛሬ ለመመረቅ ላለፉት በርካታ ወራት ብዙ ወጣችኋል፥ብዙ ወርዳችኋል፥ ብዙ ላብ አፍሳችኋል። በአካልና በመንፈስ ጠንክራችኋል፥ የትግላችን ሀሁ እና ግብ ተገንዝባችኋል።በዚህ ሙሉ ቁመናችሁ መከላከያ የሚባል የአብይ አህመድ ታጣቂ ጋር ፊት ለፊት ትገጥማላችሁ።
ትግል ግን ሌላም መልክ አለው። ከራስ ጋር የሚደረግ ትግልና አብሮ ሲኖር ከጓድ ጋር የሚደረግ ትግል እጅግ ከባድና ፈታኞቹ የትግል መልኮች እንደሆኑ ልትገነዘቡ ይገባል። ወደ አብይ አህመድ መተኮስና አብይን ማሸነፍ ቀላል ነው፥ ከባዱ ወደ ራስና ጓደኛ ድክመቶች ማነጣጠር ነው።
አብይ በታንክና በድሮን ያልቻለውን ጦርነት በገንዘብ፥ በሽማግሌና በወሬ ሊያሸንፍ እየሞከረ ነው።አንዳንዴ ከሽህ የአብይ ታንከኛ አንድ ወሬኛ ትግላችን ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላልና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።እንግሊዞች "ስራ ለፈቱ እጆች ሰይጣን ስራ ይፈጥርላቸዋል" ይላሉ።ብዙ ጊዜ የወሬና ሃሜት ምንጩ መቦዘን ስለሆነ እያንዳንዱን ደቂቃ ስለትግላችን በመድከምና በማሰብ እናሳልፍ።
ታጋይ ወንድሞቼ
ክፋትን፥ ምቀኝነትን፥ ቅናትንና ተንኮልን ተፀየፉ። ማንም የግለሰብም ይሁን የቡድን ጠላት አማራ ላይ ይነሳ መግጠምና መጣል እንችላለን። እነዚህ የመፈስ ደዌዎች ከተጠናዎቱን ግን ከጠላት ቀድመው እኛኑ ይጥሉናል።ፖለቲካችን ችላ ያለው ፥ያልተሄደበት መንገድ ቅንነት ነው።አለም ደጋግሞ የሚወድቀውም በዚህ ምክንያት ነው። በተንኮልና በክፋት በቦካ ፖለቲካ አለም የራሱን እጅ እየበላ ለጊዜው ይረካ ይሆናል እንጅ የትም አይደርስም። ይህ የመሳሪያም የቅንነትም አቢዮት ነውና ክፋትንና ተንኮልን ራቁ።የወንድምን ስኬት ውደዱ።ለሌሎች መኖርን ልመዱ።ራስ ወዳድ እንዳትሆኑ። ህዝባችን እያለቀ ራስ ወዳድ እንደመሆን ትልቅ ወንጀል የለም።ከፍ ባላችሁ ቁጥር የበለጠ ትሁት ሁኑ።
ይህን የምላችሁ የአለም ፖለቲካ እንዴት እንደሚሰራና እንደሚሰራ የማላውቅ ቂል ሆኜ አይደለም፥
ይልቁንም በመደበኛ ፖለቲካው ውስጥ ያለው መደበኛ የቅጥፈት መንገድ ውጤቱ ውድቀት እንደሆነ የአለም ተሞክሮ በተለይ ደግሞ የራሳችን ልምድ ስለሚነግረኝ እንጅ።
ይህ ትግል የህዝብ ትግል ነው። ይህ ትግል ለአማራ ህዝብ የሚደረግ ትግል ነው። መነሻችንም መድረሻችንም ህዝባችን ነው። ምድራዊዩ እግዜራችን ህዝብ ነው። ይህን እግዜር አይኑን መጠንቆል ያስቀስፋል። በስህተት እንኳን ህዝብን የሚያስቀይም ነገር አንዳትሰሩ። ክልክል ነው። ህዝብ እንኳን መብቱን ሰብል የለበሰ የእርሻ መሬቱን ስትረግጥበት፥ የቤት አጥሩን ስትደገፍበት አይወድም። ህዝብ "ፈጣሪያችን" ነውና እንቅስቃሲያችን ያያል፥ እስትንፋሳችን ይለካል።ጥንቃቄ እናድርግ።
የአማራ ህዝብ የራሱ የሆነ ንፁህ ተቋም እንዲኖረው ብዙ ቀደምቶች ብዙ ደክመዋል።ታስረዋል፥ አካላቸውም ቅስማቸውም ተሰብሯል፥ህይወታቸውንም ሰጠዋል። በቀጠለ ጥረትና ብዙ ድካም በዚህ በኛ ዘመን ተሳክቷል። የአማራ ህዝብ የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄን ፈጥሯል።ይህ ተቋም መድህናችን ሆኖ ወደምንፈልገው ግብ ያደርሰን ዘንድ በየዘርፉ የተሳሉ ፖሊሲዎች አሉት።የተቋማችን የመጀሪያውና ቋሚው ፖሊሲያችን ራስን መቻል ነው። ሁሉን አቀፍ ራስ በቅነትን በየቀኑ ማሳደግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ድርጅታዊ ውስጣዊ አንድነታችን እናጠናክራለን። ራሱን ያልቻለ አንገት የሚያቅፈው የለውም።ስለዚህ የእዞች ውስጣዊ አንድነት፥ የድርጅታችን አፋብን ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት እጅግ አስፈላጊ ነው።የህዝባችን አንድነት የመተንፈስ ያክል ፍፁም አስፈላጊ ነው።የተበተነ ህዝብ ነጥሎ የሚበላውን ጠላት ከየአቅጣጫው ይጋብዛልና።
ሁለተኛውና ተያያዥ ፖሊሲያችን ከራስ መቻል ላይ የመነጨ ከሌሎች ጋር የሚደረግ የተመረጠ በጎ ትብብር ነው። የተሰላና የተጠና ትብብር ሁልጊዜ አስፈላጊ ነው። ጥቅምህን በሚስጢር ኪስህ ይዘህ ፥ የሌላን ወገን ጥቅም ሳትነካ፥ የራስህን ሳታስነካ መተባበር ሁሌም ልክ ነው። ስለዚህ በአጭርም በረጅምም እንተባበራለን።የቀጠናው ሃይሎችም ጋር ቀጠናዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከጥቅማችን አኳያ እናብራለን። ፋኖ ልብ አለውም አላለውም የግዙፉና የውስብስቡ የምስራቅ አፍሪካ መልክአፖለቲካ አካል ሆኗል። ወይ ዋኝቶ ይወጣል ያለበለዚያ ግብግቡ በሚያስነሳው ማእበል ውስጥ ይሰጥማል።ግዙፉ ቁመናችን በስሌትና በጥበብ ታግዞ፥ የምላጭ ጠርዝ ላይ የመቆም ያክል ተጠንቅቆ ሌሎችን ሳይደፍቅ አሸናፊ ይሆናል።
ከዚህ አኳያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ግርግር አማራን ብቻውን ለማቆም ነው።
በእርግጥ ማንም ሃይል መተማመኛው የራሱ አቅም ነው።የማይሸሽ፥ የማይለወጥና የማይነቅዝ የራስ አስተማማኝ አቅም ነው።ይህም ሆኖ አማራ በአለም ፊት ቆሞ ብቻውን ገለባብጦ ተራራውን ሜዳ ፥ሜዳውን ተራራ እንዳላደረገ ሁሉ የአማራ ትግል "ተነጥሎ" የቆመ እለት ይከስማል የተባለ ይመስል ይህ ሁሉ ግርግር ፋኖን ብቻውን ለማቆም ነው።
ከሶስት አመታት በፊት ሁሉም የጨዋታው ተሰላፊ የየራሱን ስሌት ይዞ በፕሪቶሪያ መድረክ ቢጫዎትም "በስምምነቱ" ውስጥ የነበረው የብዙዎች ተሰላፊዎች "ድብቅ" የጋራ ግብ ግን መቀጣጠል ጀምሮ የነበረውን የአማራ የአቢዮት እሳት በጋራ የማጥፋት እቅድ ነበር ብዬ አምናለሁ ። በዚህ " አደገኛውን ሰደድ የማጥፋት ተልእኮ" ውስጥ ህወሃትና ብልፅግና በደስታ አብረው እንደሚሰለፉ የፕሮቶሪያ ስምምነት "ሽማግሌዎቹም" እርግጠኞች ነበሩ ማለት ይቻላል። ምናልባት የትግራይ ሃይሎች ታሪካዊ ውሳኔ ወስነው ራሳቸውን ግሉል አድርገው ማቆማቸው እስኪታወቅ ድረስ በቀላሉ አማራን ጨፍልቀው ወደ ኤርትራ መሻገርና የየራሳቸውን ግብ ማሳካት እንደሚችሉ እርግጠኞች ነበሩ።ባልጠበቁት ሁኔታ ህወሃት የራሱን ስትራቴጅካዊ ስሌት ይዞ አማራን አልወጋም፥ ኤርትራ ላይም አልዘምትም ሲል ቀመሩ ተዛባ። የአማራው የህልውና ትግልም በመካከል በፍጥነት ሌላ ደረጃ ላይ ደረሰ።ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በአንድ እጁ እየተዋጋ በሌላኛው እጁ የራሱን ትግሉን የሚመራ ተቋም ፈጠረ።ይህ ሲሆን የጨዋታው መልክ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ ማለት ነው።
አብይ ግን እድሎች ከተገኙ አሁንም እዛው ጨዋታ ውስጥ መሆኑን እና ተስፋ አለመቁረጡን የሚያሳየው በተለይ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ አማራውን ለመነጠል የሚያደርገው ሩጫ ነው። በዚህ መሃል አንዳንድ አውቀው የተኙ ወይንም በአሞሌ ጨው ራሳቸውን የሸጡ የኛን ወገኖች ሳይ "ሌላው ሁሉ ይቅር ይህ ሁሉ ሩጫና ግርግር አማራን ብቻውን አቁሞ ለማጥፋት በመመኜት የሚደረግ መሆኑን እንዴት ማወቅ ተሳናቸው ?" እላለሁ።ለዚህ እፍኝ እድሜስ ስንት አመት አሞሌ ይላሳል?
በእኔ እምነት፦
የፕሪቶሪያ አፈራራሚዎች ዋና ግብ ፀረ-አማራ ብለው ያሰቧቸውን ሃይሎች አስተባብሮ እየተነሳ ያለው አዲሱ የአማራ አቢዮት መንፈስ ላይ ማዝመት ነበር።ለጊዜው አልተሳካም።
እነዚህ ሃይሎች የአማራ ልዩ ሃይል እንዲፈርስ ለአብይ ቀጭን ትእዛዝ ሰጠዋል።ልዩ ሃይሉ ፈረሰ። ያም ሆኖ ያሰቡት ሳይሳካ እንዴውም የፈረሰው ልዩ ሃይል ለትግሉ ልዩ ግብአት ሆነ።
ትንሽ ገፋ እና ደፈር አድርጌ ከደመደምሁ... የፕሪቶሪያው ስምምነት በራሱ "የአማራ ትንሳኤ" ፍርሃትና ድንጋጤ ውጤት ነው።አማራው ባይነሳ ኖሮ የፕሪቶሪያ ስምምነትም አይፈጠርም ነበር።ለዚህ ነው አንዳንድ ወገኖች የአማራው የህልውና ትግል የዘመናት ፍጅትና መጎሳቆል ውጤት መሆኑን ረስተው በፕሪቶሪያው ስምምነት ምክንያት የተፈጠረ ኩርፊያ የወለደው ሊያስመስሉት ሲሞክሩ ሲታይ አስቂኝና አስተዛዛቢ የሚሆነው።ፕሪቶሪያ የአማራን ትግል አልወለደም፥ የአማራ መነሳት ፕሪቶሪያን ወለደ እንጅ።
ቆላም ነፈሰ ደጋ ጨዋታውን በደንብ ተጫውተናል። ።ስርአቱንም እንደተደገመበት ሰይጣን አፍዝዘን አስቀምጠነዋል። እጣፋንታውንም በምንወስደው ቀጣይ ሙሉ ለሙሉ ገፍቶ የመጣል እርምጃ ላይ እንዲወሰን አድርገነዋል።
የዚህ ትብብር ስኬትና ውድቀት ግን የሚቀጥሉት ብዙ መቶ አመታት የእርስበርስ እልቂት ወይም ሰላምና ልማት ማለት ነው።
በዚህ አጋጣሚ፦ ባለሃብት ነን የምትሉና ይህን ትግል ለማፍረስ በድለላ የተሰማራችሁ ወገኖች ተው።!---ከፀሃይ በታች የምትሰሩት እያንዳንዱ ስራ ይታወቃል።እንኳን ከህዝብ ከጎረቤት ተጣልቶ መኖር ይቸግራልና አስቡበት።አርፋችሁ ስራችሁን ስሩ።
በዚሁ የፖለቲካ ድለላ ውስጥ የተሰማራችሁ አንዳንድ የሃይማኖት አባት ነን የምትሉ የየቤተ እምነቱ ሰዎችም ከዚህ ድርጊታችሁ ተቆጠቡ።ሌላው ቢቀር ቤተ እምነታችሁን ለሚያፈርስ ሃይል አካፋ አቀባይ አትሁኑ።ለምድርም ለሰማይም የማይሆን ነገር አትስሩ። በ80 አመታችሁ የሰላሳ አመት ጆሮ ጠቢን አትፍሩ።በውድቀታችሁ የጣላችሁትን ዘመንና ህዝብ ልናቃና ስንደክም ደንቃራ አትሁኑ።ትንሽ እንኳን እፈሩ።
ለውዱ የአማራ ህዝብ!
የአለምን መከራ ተሸክመሃል፥ እንድታልቅ ፍጅት ታውጆብሃል።ከዘመናት ሞት-ቀመስ እንቅልፍ በኋላ ተነስተሃል። ጠላትህ አቁስለህ የምትተወው አውሬ አይደለምና ሳትቀብረው እንዳትቀመጥ።ጠላት አንድነትህን በወንዝ ለመክፈል፥ በጎጥ ለመተልተል፥እየሰራ በመሆኑ በደምህ የገነባኸውን ቤት የሙጥኝ በል። እንደወትሮው ሁሉ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ግዜ ወዲህ አብይ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር እየሰራ በመሆኑ መዋደድህ የበለጠ መጠንከር ይኖርበታል። በየቀኑ የሚከፈለውን ዋጋ ባውቅም በነፃ ነፃ አይወጣምና አይዞህ በርታ!
ለመላው የኢትዮጲያ ህዝብ
ይህ እብድ ሰውዬና ቡድኑ በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ የማይጎሳቆል፥ የማይራብ፥ የማይታረዝና ህልውናው አደጋ ውስጥ የማይገባ ኢትዮጲያዊ አይኖርም። በኢትዮጲያ ምድር ላይ ቆሞ መራመድ እስከቻለ ድረስ መሬቱንም ህዝቡንም በግራም ሳይቀር እየለካ ከመሸጥና ከማጥፋት አይመለስም። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይነሳ።
ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ
ዛሬ ከአብይ ጎን ቁሞ የሚገኝ ብሄራዊ ጥቅም ነገ ከቀጠናው የሚመነጭ ትልቅ ብሄራዊ ኪሳራን ያመጣባችኋልና ከእውነት፥ ከፍትህና ከነፃነት ሃይሎች ጎን ቁሙ። በተለይ አንዳድ ሃገራት አብይን መደገፍ አቁሙ።አብይ አማራን ሲፈጅ፥
የትግራይን፥ የኦሮሞን፥ የጋምቤላን፥ የሲዳማን፥ የጉምዝን፥ የቤኒሻንጉልን፥ የአፋርን፥ የሶማሊን፥ የጉራጌን በአጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ ላይ እሳት ለኩሶ እያቃጠለ ቆሞ መመልከት ነገ አለም ቢጮህ የማይፈታው ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ምስቅልቅል ይፈጥራልና አስቡበት።ፍትህና ነፃነት ደንበር የላቸውም። እንደ ፀሃይ ለሁሉም መሆን አለባቸው።
ለሚሊሻ፥መደበኛና አድማ ብተና ፖሊስ አባላት።---በራሳችሁ ፀብ ውስጥ የጠላት ዱላም ገላጋይም መሆን ታሪክ የማይረሳው ክህደት ነው። ወደ ወገኖቻችሁ ኑ።ያለበለዚያ እጣ ፋንታችሁ አንደኛው ተራራ ስር ወይ አንዱ ጎዳና ላይ ደመ-ከልብ መሆን ነው።አሁንም ቢረፍድም አልመሸምና ወደ ወገኖቻችሁ ኑ።በኛ በኩል እንደ ወንድምና እንደ አባት እንቀበላችኋለን።
ድል ለአማራ ህዝብ!
ክፋት ለማንም፥ በጎነት ለሁሉም
አዲስ ትውልድ፥ አዲስ አስተሳሰብ አዲስ ተስፋ!
ህልውናችን በተባበረ ክንዳችን!
በጣም አመሰግናለሁ!!