በቅርቡ አንድ ተስፋይ ቀለታ ደምሳስ የተባለ ኤርትራዊ የነጻነት ታጋይ ግሩም ባለ 390 ገጽ መጸሐፍ ለህትመት አብቅቷል። ታጋዩ ከኤርትራ ህዝብ የነጻነት ትግል ታሪክ ኣኳያ ምርምር ለማካሄድ ለሚያስቡ ዜጎቻችን ሁነኛ “የሳይንሳዊ ምርምርና ጥናት አቡጊዳ መርሆችን” ቁልጭ አድርጎ ለማሳዬት ሞክሯል። ለዛሬ ይህ ጉምቱ የምርምር ሰው፡ የህዝባዊ ግንባር የከባድ መሳርያ የምርምርና የጥናት ክፍል በትግሉ ወቅት ስለነበራቸው አስተዋጽኦ በተመለከተ ከገጽ 194 ጀምሮ ያቀረበውን ታሪክ እናስኮምኩማችኋለን።
74ኛዋ መካናይዝድ የትምህርትና የጥናት ቡድን
“ለትምህርት ሱማሊያ ሄደው የነበሩ ጓዶቻችን እስኪመለሱ ድረስ፡ የከባድ መሳርያ ትምህርታችን ይበልጡኑ ቴክኒክ እና ቲዮሪ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህም ማለት ይሰጥ የነበረው ትምህርት፡ ከባድ መሳርያዎችን እንዴት አድርገህ ታቀባብለዋለህ፡ እንዴት አድርገህ ትተኩሳለህ፡ እንዴትስ በእንክብካቤ ትይዘዋለህ ወዘተ የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የተገደበ ነበር። እንደ ዒራቕ ከመሳሰሉ ሃገሮች ተምረው የመጡት የመጀመርያዎቹ መምህራኖቻችን፡ ይህንን መሰል ትምህርቶች ነበር ያጋሩን። እነሱ ባደረጉልን ትምህርትና ራሳችን ባደረግነው ጥረት ደግሞ በርካታ ብቁ ታንከኞችና መድፈኞች የከባድ መሳርያ ተዃሾች (መድፍዓጂታት) ፈጥረናል። በዚህ ኣማካኝነትም ታንኮች፡ የ122 ሚ.ሜ መድፎች፡ ቀላልና ከባድ ሞርታሮች፡ ወዘተ በቅጡ ተጠንተው፡ በሰዓቱ በጠላት ላይ ተወድረው በአግባቡ ግልጋሎት ላይ ውለዋል።” ይላል አፈወርቂ ኢያሱ ኣስመራ ውስጥ ሰኔ 2017 እ.ኣ.ኣ. ከታጋይ ተስፋይ ቀለታ ደምሳስ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ። ከዚህ በተጨማሪም፡ የተክኒክ ባለሙያዎችም፡ ከካርታ ጋር አስደግፈው ከባድመሳርያ ዬት ላይ ቢተከል፡ የትኛውን ዒላማ ባግባቡ ያደባያል እያሉ የሚያስተኩሱ ባለሙያዎችም ነበሩን።
“44 ታጋዮች ሱማሊያ ውስጥ ተምረን እንደተመለስን፡ የ74ኛዋ መካናይዝድ የትምህርትና የጥናት ቡድንን በመጋቢት 1986 እ.ኤ.ኣ መስርተናል። ዓላማዋም በሶስቱ ግንባሮቻችን ማለትም በሰሜናዊ ምስራቕ ሳሕል፡ በናቕፋና በሓልሓል የነበሩ የመካናይዝድ ሃይሎቻችንን የተመጣጠነና ሚዛናዊ የሆነ እውቀትንና የስራ ክንውን አፈጻጸምን እንዲጎናጸፉ ማድረግ ነበር።” በማለት ዳዊት አርአያ ለደራሲው ገልጿል።
በነሐሴ 1977 እ.አ.አ. ወደ ትግል የተሰማራው ለፍተናንት ኮሎነል ዳዊት አርአያ፡ ሱማሊያ ውስጥ የተማሩት የከባድ መሳርያ ትምህርት ምን አስተዋጽኦ ነበረው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፡ “ሲጀመር ቴክኒክ ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረው ትምህርታችን፡ ስልት፡ የተኩስ ጥበብና ብልሃት፡ የአተኳኾስ ጥበብ (ጋነሪ)፡ የካርታ ንባብ ትምህርት፡ ቅየሳ፡ የከባድ መሳርያዎች ኣጠማመድና የማወሃሃድ ስልት፡ የመሳርያዎች አፈታትና አገጣጠም ባጠቃላይ የከባድ መሳርያዎችን ሁለመና በቅጡ እንድንፈትሽና እንድንረዳ አስችሎናል” ይላል። ቀጥሎም፡ ተመሳሳይና ቀጣይነት የነበራቸው ስልጠናዎች ለሃላፊዎች በየግዜው ይሰጥ እንደነበርም ይገልጻል። በዚህም ማንኛውም አዛዥ፡ ኣስተኳሽ፡ ተኳሽ ወዘተ ባንድ ቃል እንዲግባባና እንዲናበብ ለማብቃት ተችሏል። እያንዳንዱ ሰው፡ ታንክ አሽከርካሪ፡ የታንክ ሃላፊ፡ አስተኳሽ፡ ተኳሽ ሆነ ወዘተ ሆኖ በብቃት ለመታገል የሚያስችለውን ሙያ ቀስሞ ስለነበር፡ እያንዳንዱ ሰው የብዙ ሰዎችን ስራ መስራት በመቻሉ፡ በጥቂት የሰው ዓቅም እንደ ብዙዎች ሆነን ግዙፍ ስራ ለመስራት ችለናል። በእለታዊ ስራችን አንድ ሰው በብዙ ተራብቶ እንደ ብዙ ሰው ሆኖ ሰርቷል። ይህ የትግል ወኔያችንና ጥረታችንም ለተጎናጸፍነው ድል ጉልሕ ሚና ነበረው።
በእያንዳንዱ ውጊያ የሚማረክ አዲስ ከባድ መሳርያን፡ ባጭር ቅጽበት ለምደን፡ ወደ ጠላታችን ወድረን እዚያው በገዛ ከባድ መሳርያው ማደባዬት ችለናል። ለምሳሌ በናቅፋ ግንባር የማረክነውን 130 ሚ.ሜ. መድፍ፡ ወዲያው አቀባብለን ወደ ከረን ግንባር እንደተኮስነው፡ በጠላት ሰራዊት አዛዦች ላይ ትልቅ ሽብርና ፍራቻን ፈጥሯል” ይላል በኣሁኑ ወቅት የትራንስ ሆርን ኩባንያ ስራ አስኪያጅ የሆነው የያኔው የነጻነት ታጋይ ዘርአብሩኽ ገብረስላሴ። “ስርሒት ፈንቅል” በሚል መጠሪያ ምጽዋን ነጻ ለማድረግ በተደረገው ግጥሚያ፡ ማይ-ኣዋልድ በተባለው ስፍራ የተማረኩት 20 ታንኮችም፡ ያኔውኑ ከመቅጽበት ነው አፈሙዛቸውን ወደ ጠላት አቅንተን የተጠቀምንባቸው። ታንኮቻችን ከእግረኛ ሰራዊታችን ጋር ተወሃህደው የሚያጠቁበት መድረክም ተፈጥሮ፡ በአግባቡ ተጠቅመን ለድል በቅተንበታል። እዚያው “ኦፕሬሽን ፈንቅል” ላይ ታንኮቻችን ከእግረኛ ጋር በሰመረ ሁኔታ ተዋህደው ጎን ለጎን ስላጠቁ፡ ጠላት ላይ ሽብርን፡ ወገን ላይ ደግሞ ሞራልና ወኔን ቀስቅሰው እንደነበር አስታውሳለሁ፡ ይላል የያኔው የክፍሉ ታጋይ ዳዊት ምሕረተኣብ።
በመሆኑም በቀጣይ እናገኘው የነበረው ትምህርት ጥቅሙ ይህ ብቻ ኣልነበረም። ከእውቀት ማነስ ምክንያት በከባድ መሳርያ ጓዶቻችን ላይ ይደርስ የነበረው አደጋ እንዲቀንስ ለማድረግ ችለናል። ምክንያቱም የከባድ መሳርያ ትምህርት በቅጡና በይፋ መሰጠት ከመጀመሩ በፊት ታንከኞቻችን ደህንነታቸውን በተመለከተ ሊያደርጉት የሚገባ ቅድመሁኔታ ላይ ትልቅ ክፍተት ነበረን። በመሆኑም ባንድ ወቅት በአባሎቻችን ላይ አደጋ ደርሶ ነበር፡ ይህም የ100 ሚ.ሜ. መድፍ ሲተኮስ በተፈጠረው ወላፈን ኣማካኝነት መሆኑ ነው። ይህና ከመሳሰሉ የትግል ልምዶች ትምህርት በመቅሰም፡ አደጋው እንዳይደገም በማስቻል፡ ይሰጥ የነበረው ትምህርት ጉልህ ሚና ነበረው።
ግራት በተባለው ስፍራ ምጽዋ ውስጥ ታንክ ለታንክ የታንክ ውጊያ በተደረገበት ወቅት፡ ጸሃይ ፊት ለፊታችን ስለነበረች የታንክ በታንክ ግጥሚያ ልምዱም ስላልነበረን የተወሰነ ኪሳራ አጋጥሞን ነበር። ይህን መሰሉ ኪሳራ ግን መደበኛውን የከባድ መሳርያ ትምህርት መማር ከጀመርን በኋላ በፍጹም አላጋጠመንም። በመሆኑም የኋላኋላ ከባድ መሳርያ አጠቃቀምን በተመለከተ፡ እኛ ታጋዮች በዚያች በውስኗ ኣቅማችን ከግዙፉ ከጠላታችን የኢትዮጵያ መንግስት የከባድ መሳርያ ባለሙያዎች ጋር ተስካክሎ ነበር ማለት ማጋነን አይደለም ይላል ታጋይ ኣፈወርቂ እያሱ በበኩሉ።
ታጋይ ዳዊት አርአያ በበኩሉ “ማንኛውም ከባድ መሳርያን በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንቶ፡ በጥንቃቄ ተፈትሾና በደንቡ ተለማምደነው፡ በአግባቡ ስለተጠቅመንበት፡ አስፈላጊውን ድል ልንጎናጸፍበት በቅተናል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከእውቀት ሆነ ከልምድ ማነስ ኣኳያ ሊያጋጥም ይችል የነበረውን እክል በሙሉ ለመቅረፍ ችለናል።” ይላል።
ታጋይ ዳዊት አርአያ ኣክሎም፡ “የነበረን የእውቀት ሆነ የልምድ እጥረት በጥበብ ተቀርፎ፡ ከባድ መሳርያንና አጠቃቀሙን የሚመለከት ጉዳይ በሙሉ ሊፈታ ችሏል። በጠላቶቻችን ብቻ ሳይሆን በሁሉም ጐረቤቶቻችን ልንፈራና ልንከበርም ችለናል። በጐረቤቶቻችን በኩል፡ ‘የከባድ መሳርያ ባለሙያዎቻችሁ የኛን ሰዎች ያስተምሩልን ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን’ የሚሉ ጥያቄዎች ይጎርፉልን ጀመር። በዚህም መሰረት ለኢትዮጵያውያን ሃይሎች ማለትም ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ማለትም ለወያኔዎች የከባድ መሳርያ ክፍል ከተራ እስከ የሃይል አደረጃጀት እንዲኖራቸው አድርገን በቅጡ ስልጠና ሰጥተናቸዋል።
ይህም ብቻ አይደለም፡ በተጨማሪም እ.አ.አ. በ1996 ለሩዋንዳዉያን፡ ለ6 ወራት የዘለቀ፡ የመድፈኛና የታንከኛ ሰልጣኞች፡ በዲፕሎማ ደረጃ ስልጠና በመስጠት አስመርቀናል። ደቡብ ሱዳኖችንም (S.P.L.A.)፡ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ውስጥ ተከታታይ ስልጠናዎች እንዲያገኙ አድርገናል። ኡጋንዳውያንም ኤርትራ ውስጥ የመድፈኛ ስልጠና እንዲቀስሙ አድርገናል።" ይላል ታጋይ ዳዊት አርአያ።
ታጋይ ሰለሞን በርሀ በበኩሉ፡ “ህዝባዊ ግንባር፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ በሌሎች አጎራባች ሃገራት፡ ጭቆናንና በደልን አሻፈን ብለው ይንቀሳቀሱ ከነበሩ የዲሞክራሲ ሃይሎች ጋር ዝምድና መፍጠርና መተጋገዝ ከመርሆዎቹ አንዱ ስለነበር፡ ለህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያልተገደበ ድጋፍ ያደርግ ነበር። የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ አስኳልና ቁንጮ አመራሮች ባሕሪ-ባራ በተባለው የታጋዮቻችን የስልጠና ጣቢያ እንዲሰለጥኑ የተደረጉ ነበሩ።” ብሏል። እስከ የኤርትራ ነጻነትና ኢትዮጵያ ውስጥ ደርግ ጠቅልሎ እስከተደመሰሰበት ግዜ ድረስ፡ የሕክምና ትምህርት፡ የመገናኛ ሬዲዮዎች ትምህርት፡ የፈንጂ አጠማመድና ምከና ማለትም የወታደራዊ ምህንድስና ትምህርት፡ የሬዲዮ ስርጭት ትምህርት ወዘተ እንዲማሩ አድርገናል።
የከባድ መሳርያ ትምህርትን በተመለከተ፡ እ.ኣ.ኣ በ1979. ዓራግ በተባለው ስፍራ፡ 12 የህወሓት አባላት ለአንድ ወር ያህል የመካከለኛ መድፎች፡ ሞርታሮች፡ ላውንቸሮች ወዘተ አጠቃቀም ተምረዋል። ከዚህ በኋላም ከባድ መሳርያ አጠቃቀም ትምህርት መሰልጠን ይገባቸዋል ተብሎ፡ አምስተኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተመርጠው፡ የ122 ሚ.ሜ.፡ የ 85 ሚ.ሜ.፡ የ76 ሚ.ሜ. እንዲሁም የተለያዩ ካርቤኖች የዙ 23 ወዘተ መሳርያዎችን ሁለመና እንዲማሩ ተደርገው በቅጡ ተሸኝተዋል። ህዝባዊ ግንባር ማለትም ሻዕብያ ይህ በቂ ነው ብሎ ስላላሰበም፡ በሕዳር ወር 1989 (እ.ኣ.ኣ.) የከባድ መሳርያ መምህራኖቹን ወደ ነጻው የትግራይ መሬት በመላክ፡ ለ6 ወራት ያህል በማሰማራት፡ ከ200 በላይ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ታጋዮችን በማስተማር፡ የከባድ መሳርያ ክፍሎቻቸውን በሚገባ አደራጅተንላቸዋል ይላሉ የኤርትራ ነጻነት ታጋዮቹ ዳዊት አርአያና ዳዊት ምሕረተኣብ።
የሕዝባዊ ግንባር ታጋዮች ታሪክ የጥበብና የብልሃት ታሪክ ነው። በቀጣይ ጥረት ከችግር ማምለጫን ጥበብ ፈልስፈህ ችግርህን የመፍታት ታሪክ ነውም ሊባል ይችላል። ለምሳሌ በመካናይዝድ ክፍለጦር ተመድበው የነበሩ ታጋዮች፡ ይገጥማቸው የነበረን ችግርና የአቅርቦት እጥረት፡ በገዛ ጥበባቸው እዬፈቱ፡ ለነጻነት ትግሉ ሂደት አኩሪ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል። ይህን በተመለከተ ታጋይ ነጋሲ ሰንጋል የተባለው የክፍሉ ኣባል እነዚህን ጉዳዮች እንደ ምሳሌነት ይጠቅሳል።
የT62 ታንኮች ቦምብ፡ T62 በተባሉት ታንኮች ላይ ብቻ ነው የሚሰራው። ነገር ግን ሻዕብያ እነዚህ T62 የተሰኙ ታንኮች በጭራሽ አልነበሩትም። በመሆኑም በውጊያ የተማረከ የነዚህ ታንኮች ቦምብ፡ የተባሉት ታንኮች እስኪማረኩ ድረስ ከመጠበቅ ወይም በግምጃ ቤት ውስጥ ከማስቀመጥ ይልቅ፡ ታጋዮቻችን የነዚህ ታንኮችን ቦምብ በጥበብ የ122 ሚ.ሜ. መድፍ ላይ ተገጥሞ ሊተኮስ የሚችልበትን ጥበብ አግኝተው ነበር።
የሩሲያ ስሪት የሆኑ የ4.2 ኢንች የሞርታር ቦምቦችም ከአሜሪካ ስሪት የ4.2 ኢንች ሞርታሮች ጋር ኣይገጥምም ነበር። በመሆኑም የተማረኩት የሩሲያ ስሪት የሆኑ የ4.2 ኢንች ቦምቦችን በማስተካከል የአሜሪካ ስሪት በሆኑት የ4.2 ኢንች ሞርታሮቻችን ላይ እንዲገጥሙና እንዲተኮሱ ለማድረግ ችለናል።
በተመሳሳይ መልኩ የተማረኩ ሩሲያ ስሪት የሆኑ የ81 ሚ.ሜ ቦምቦችን አሜሪካ ስሪት በሆኑ ሞርታሮቻችን እንዲገጥሙና እንዲተኮሱ አድርገናል።
በምጽዋው ጦርነት ወቅት የተማረከ ትልቅ የ149 ሚሜ ሮኬት ቦምብ፡ ላውንቸር ተሰርቶለት፡ ሰሌዳ ተደርጎለት፡ መነጸር ተገጥሞለት፡ እዛው ውጊያ ውስጥ እንዲሰማራ ተደርጓል።
ዝርዝሩ ብዙ ነው። እንዲያው ጥረቱና ብልሃት ፈጠራው ምን ያህል እንደነበረ ለመረዳት ያህል፡ ነጋሲ ሰንጋል ያቀረባትን አንድ አብነት እስቲ እንመልከት።
https://www.facebook.com/moieritrea/pos ... 775946834/
ቀጣዩን ክፍል ሌላ ግዜ እናስነብባችሁ ይሆናል። በነገራችን ላይ ተመራማሪ ተስፋይ ቀለታ ደምሳስ በነጻነት ትግሉ ወቅት በዜናው ክፍል ጉልህ ሚና እንደነበረው ስለተገነዘብን፡ የህዝባዊ ሃይልታት የዜና ክፍልን ከጅምሩ ለመሩና ለተሰዉ ኤርትራዉያን ታጋዮች ክብር ይህንን ጽሑፍ አጋርተናችኋል። viewtopic.php?f=17&t=172815&p=871442&
