እራስህ በቀረጽከው ስርዓት ትምህርት ( Curriculum)ና ባዘጋጀኸው የማስተማርያና የመማርያ ግብአት ላይ ተመርኩዘህ ለአራት ዓመት ያስተማርከው ሀገር ተረካቢ ትውልድ በአምስት መቶ ሺዎች ፈተና ሲወድቅ ድንኳን ጥለህ ማቅ ለብስ በራስህ ውድቀት ማዘንና መጸጸት ሲገባህ በትውልዱ ኪሳራ ላይ መዘባበትና ማላገጥ በውስጥህ የሰረጸ የጥላቻ መንፈስ ካልኖረህ በስተቀር ታዳጊ ወጣት ልጅ ባለው ሰው ሰብእና ልክ የሚቻል አይደለም።
ላለፉት አራት ዓመታት በቢሊዮኖች የወጣበትና በየመድረኩ ሲደለቅለት የከረመው የትምህርት ስርዓት ኩረጃን ከመከላከል ባሻገር እስከ አሁን አንዳችም የፈየደው ነገር እንደሌለ ዘንድሮም አስረግጦ አልፏል። ፈተና ያለፉት ተማሪዎች የፐርሰንትም ሆነ የቁጥር እድገትም በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚጨምረው የተማሪዎች አንጻራዊ የተፈታኝ ቁጥር እድገት ተጽኖ እንጂ መሬት የወረደ ወሳኝ የቁጥር ለውጥ እንዳልሆነ ተራ ስሌት የሚያስረዳው ሆኗል።
ከዚህ በላይ የሚያሳስበው ነገር በቀረበው ግርድፍ መረጃ መሰረት ኢንተርናሽናል ት/ቤቶች 85%፣ የግል ት/ቤቶች ከ50% በላይ አዳሪ ት/ቤቶች 100% ማሳለፋቸውና በተቃራኒው በርካታ የአርሷ አደርና የአርብቶ አደር ልጆች የሚማሩባቸው የመንግስት ት/ቤቶች 5% ገደማ ተማሪ ማሳለፋቸው ጉዳይ ነው።
ይህ የሚስረዳን ነገር ቢኖር ስርዓት ትምህርቱ ና የፈተናው ውጤት ከዓመት ወደ ዓመት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃና በንጽጽር በኑሮ ደረጃቸው አቅመ ደከማ የሆኑ የማህበረሰባችን አካላት ልጆችን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መገለላቸው ተጠናክሮ የመቀጠሉ ክስተት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ነው።
በዚህ መሰረትም "አዲስ" የተባለለት ስርዓተ ትምህርት ድሃና ሀብታምን ሳይለይ ትምህርትን በአንጻራዊነት በእኩል ደረጃ ለሁሉም ማዳረስ፣ ማስፋፋትና ሚዛናዊ ዉጤትን ማስጠበቅ ሲኖርበት በአጼ ሐይለ ስላሴ ዘመን እንደ ተዘመተበት (Secter Review) ትምህርት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ልጆችን ዳር በማስያዝ ከፍተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆችን ቀጣይነት ባለው መንገድ ባለመብት የሚያደርግና በዚሁ መንገድ ውጤቱ እየተዛባና እያገለለ እንደሚቀጥል እየተዘገበ አለማስደንገጡና አለማወያየቱ አስደማሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በአጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱ የአራት ዓመት ግምገማ የተማሪ ጥራትና የቁጥር እድገት ያልታየበት፣ የመማር ማስተማር፣ የተማሪና መምህር ጥመርታ ያልተሰናሰለበት፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የአርሶ አደር፣ የአርብቶ አደር ልጆች በከፍተኛ ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተጠቃሚነት ያገለለ፣ ጥግ ያስያዘና በ4 ዓመት ውስጥ ከ2 ሚሊየን በሚበልጡ ወጣቶችን መነሻና መዳረሻ ያሳጣ ሆኗል።
እንደዚህ ዓይነት የትውልድና የሀገር ተስፋን ጥያቄ ላይ የሚጥል ስርዓት ትምህርት ለምን፣ እንዴትና ወዴት በሚሉ መሰረታዊ መስፈርቶች በገለልተኛ አካለትና በባለሙያዎች ኦዲት ተደርጎና ተገምግሞ ወደ ተገቢው አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረግ ወጣቱን ከመደናበርና ተስፋ ከመቆረጥ ቤተሰብን ከጭንቀትና ከሐዘን መታደግ ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።
በተለይ ደግሞ በየዓመቱ መጨረሻ ላይ በከፍተኛ እርካታና አጀብ ተማሪና ሕዝብን በሚያሳዝን መልኩ የሚዘገበው ከ500 ሺህ የሚልቁ ታዳጊ ልጆች ወድቀትና ኪሳራ ከስሜዊነት ተላቆ ሙያዊ በሆነና በሰከነ መንገድ በጥንቃቄ እንዲዘገብና ሙያ ከባለሙያው ጋር እንዲገናኝ ክንዋኔው ወደ ሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነት ሊመለስ ይገባዋል።
ሙሼ ሰሙ እነደከተበው
https://www.facebook.com/share/p/1YVA2r ... tid=wwXIfr