የሰዉ ልጅ ካላቸዉ ትልቅ ቁሶች ዉስጥ ኣንዱ ቋንቋ ነዉ። የምያግባባም የምያጣላም ቁስ ነዉ።
ሁለት ቋንቋዎችን የሚናገሩ ቀርቶ ኣንድ ቋንቋን የሚናገሩትን ማግባባት ይችላል። ማጣላትም ይችላል።
ይህን ቁስ ለመግባብያነት መጠቀም ብልህነት ያስፈልጋል። ቀልብ ያስፈልጋል።
ለመሆኑ ኣንድ ሰዉ በኣንድ ቀን ዉስጥ ቋንቋን ለስራዉ መግባብያነት የሚጠቀመዉ ግዜ ምን ያህል ነዉ?
ኢትዮጵያ ዉስጥ ኣርሶ ኣደር ቤተሰብ ስራዉን ለመተግበር ቋንቋን የሚጠቀመዉ ምን ያህል ግዜ ነዉ? ተግባሩ ስራዉ ነዉ። ከሩቅ ሆኖ የኣርሶ ኣደር ቤተሰብ ስለሚጠቀመዉ የቋንቋ መብት ማለት ወሬ ነዉ።
እዚህ ዐለም ላይ ያሉት የሰዉ ጎሳዎች ብዛት መሪዎች የሆኑ ግለሰቦች ካቋቋሙት ሃገሮች እጅግ ብዙ ነዉ። ኢትዮጵያ ኣንድ ሃገር ስትሆን ከሰማንያ በላይ የጎሳዎች ቋንቋዎች ኣላት። ህንድ ኣንድ ሃገር ስትሆን ከኣንድ መቶ ሃያ በላይ የጎሳዎች ቋንቋዎች ኣላት።
በየግዜዉ ራዕዮቻቸዉን ይዘዉ ተነስተዉ በየሜዳዉ እንደ እንስሳዎች ተበትነዉ ይኖሩ የነበሩትን ጎሳዎች ኣንድ መንግስታዊ መዋቅር ስር ኣድርገዉ ሃገር ያቋቋሙ መሪዎችን መቁጠር ቀላል ነዉ።
የሰዉ ልጅ በኣብዛኛዉ እንደ እንስሳዎች ሜዳ ላይ ተበታትኖ ይኖር እንደነበረ በየሃገራቱ የነበሩትን እና ያልነበሩትን የመንግስታዊ መዋቅሮችን መቃኘት በቂ ነዉ።
መንግስታዊ መዋቅርን መመስረት እና ኣጽንቶ ማኖር የሰዉ ልጅ ትልቅ ጥበብ ነዉ። ይህቺን ያለማስተዋል ንዝህላልነት ሰዎችን እንደ እንስሳዎች ሜዳ ላይ ተበታትነዉ እንዲኖሩ ማድረግ ነዉ።
ለጥበቡም ሆነ ለንዝላልነቱ ኢትዮጵያ በቂ ምሳሌ ናት።
በጣም ጥንታዊ የነበረዉ የፈረኦኖች ዘመን ይቅር እና ከአክሱም ስልጣኔ ዘመን ብንጀምር በጣም ግልጽ ምሳሌን መመልከት እንችላለን።
የአክሱም ዘመን የነበረዉ መንግስታዊ መዋቅር ፈርሶ፣ የዛጉዌ ስሩወ መንግስትም ተዳክሞ በኣፄ የኩኖ ኣምላክ መሪነት መንግስታዊ መዋቅር ተመልሶ ተቋቋመ።
ያንን ማድረግ መቻል ትልቅ ምስጋና የሚገባዉ መሆኑን ኣለማስተዋል ታሪካዊ ንዝህላልነት ነዉ ብዬ ኣስባለሁ።
ካልተሳሳትኩ አማርኛ የጎሳ ቋንቋ ሳይሆን መንግስታዊ መዋቅርን ለማቋቋም በለፉ የአከባቢዉ ወታደሮች ቋንቋ ሆኖ የተወለደዉ በዛ ዘመን ነዉ።
ኣንድ የሰማሁኝ አፈ ታሪክ ስህተት ካልሆነ በዛን ዘመን የነበረን የሀይማኖት ዉይይት አባይ ባቦ የተባለ ሰዉ ሰምቶ ባህሌን ብሎ ወደ ቦረና ተሰደደ።
ከዛ ዘመን በፊት አማራ ሆነ ኦሮሞ የሚባሉ ጎሳዎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ተስፋፍተዉ የሚኖሩ ማህበረሰቦች መኖራቸዉን የዘገበ ታሪክ መኖሩን ኣላዉቅም። ይህ ታሪክ መኖሩን የማያዉቅ ኢትዮጵያዊ አማራ ሆነ ኦሮሞ ብሎ ማዉራት መሃይምነትን ማንጸባረቅ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነዉ።
በኣፄ የኩኖ ኣምላክ ዘመን የተመለሰዉ መንግስታዊ መዋቅር በግራኝ ዘመን ተናግቶ ቦረና ዉስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን መሃል ኣገር ዉስጥ ተስፋፉ።
ኣሁን ኦሮምኛ የሚባለዉ ቋንቋ አባት ቦረና ዉስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ይዘዉት የሰነበቱት እጅግ ጥንታዊ ቋንቋ ነዉ።
ይህ ማለት በዚህ ዘመን ኦሮምኛን የሚናገሩት የኦሮምኛ ቋንቋ አባት የሆኑት ቦረናዎች ብቻ ኣይዴሉም። ሸዋ ዉስጥ ገበሮ የተባሉት ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የቦረና ጎሳ ያልነበሩ፣ ቦረናዎች ሸዋ ሳይደርሱ ወይም ሳይመለሱ በፊት ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ጎሳዎች ናቸዉ። ከግራኝ ዘመን በፊት ቦረናዎች ወለጋ ዉስጥ ይኖሩ እንደነበረ የማዉቀዉ ታሪክ ዬለም።
ስለዚህ ሸዋ ዉስጥ ገበሮ የተባሉ ጎሳዎች ቁጥር ኣንሶ ነዉ ሸዋ ዉስጥ የገበሮዎችም፣ የቦረናዎችም ሃገር ሳይሆን የቦረናዎች ሃገር ነዉ የሚባለዉ?
ወለጋ ዉስጥ የቦረናዎች ቁጥር ከሌሎች ጎሳዎች ቁጥር በልጦ ነዉ ወለጋ የቦረናዎች ሃገር ነዉ የሚባለዉ?
የኢትዮጵያ ዜጎች በብዛት ባለሃገር ዉስጥ የሚኖሩ ናቸዉ። ቦረና ዉስጥ የሚኖሩ ሸዋ ዉስጥ ወይም ሀረርጌ ዉስጥ ወይም ወለጋ ዉስጥ ወይም ጎጃም ዉስጥ፣ ወዘተ፣ ከሚኖሩት ጋር ተገናኝተዉ መግባብያ ቋንቋ ችግር የሚሆንባቸዉ የወሬ ችግር ነዉ ወይስ በተግባር የተረጋገጠ ነዉ?
በተግባር ጉልህ ያልሆነ ችግርን በማጉላት ለሁላቸዉም ለፖለትካ ማህበረሰብ ሉዓላዊነት ከለላ የሆነዉን ሃገር ማናጋት እና ተግቶ ነዋሪዎችን መበጥበጥ እንዴት ዐይነት እኩይነት ነዉ?
የመንግስታዊ መዋቅር ቋንቋ ሆኖ የተወለደዉ አማርኛ በሌሎች ቋንቋዎች ላይ የነበረዉ ተፅዕኖ መንግስታዊ መዋቅሩ ስንት ግዜዎች ተመልሶ ሳይፈርስ ሌሎችንም ቋንቋዎችን የማሳደጉ ህደት መንግስታዊ መዋቅር ወስጥ ገብቶ የራሱን ሂደት ጀምሮ ነበር።
ለምሳሌ በሪሳ ጋዜጣ እና ሃገር ኣቀፍ የመሠረተ ምህርት ዘመቻ የዚህ ሂደት አካል ነበሩ ማለት የሚቻል ይመስለኛል። በብልህነት ከተስተዋለ።
የመሠረተ ትምህርት ዘማች ሆኜ ኣዉቃለሁ።
ይህን የግል አስተሳሰቤን ማጋራት የንዝህላነት አስተሳሰቦችን ማስተዋል እና ይህ አስተሳሰቤ ምን ይመስላችኋል ለማለት ነዉ።
ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ንዝህላልነትን ማስተዋል ሰልችቶኝ የነበረኝን አስተሳስብ ኣጋርቼ ወደ አካዳሚ ዝንባሌዬ ማተኮሩን ልቀጥል ኣልኩኝ።
በቅንነት ያጋራሁኝ አስተሳሰቤ ንትርክ ማስከተሉ ያለኝን ሀሳብ ማጋራቱን ኣስቀጠለኝ።
ይህ እ ኢ አ ከዉሳኔ 96 በፊት ነበረ። ያ ዉሳኔ ለምን እንደሆነ ኣሁንም ኣላዉቅም።
ሀሳቡን ከሰጠሁበት ፎረም ተባርሬ እሺ ብዬ ተቀበልኩኝ። በኣንድ ተሳታፊ “ሃይሊ ኤጁኬትድ ኤንደ ሞስት ደንጀረስ” ተብዬ ተወቅሻለሁ። በተሳታፊዎቹ ሁሉ ፊት ማለት ነዉ። ያን ያህል የምያስወቅስ አስተሳሰብ ነበረኝ ብዬ ኣላሰብኩም ነበር።
ሌላ ግዜ በሌላ ግለሰብ “ኦቨርኤጁኬትድ” ተብዬ ተወቅሻለሁ። ይህም ያልጠበኩት ወቀሳ ነበር።
ኣሁን ሃያ ሁለት ዓመታት ገደማ ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስብ ያኔ ያጋራሁኝ አስተሳሰቤ ዛሬ በሰፊዉ ከምንሰማዉ መንግስታዊ መዋቅርን ሁሉም ተባብረዉ ኣሻሽሎ በማፅናት ማሳደግ እንጂ ማናጋት ቀልበቢስነት ነዉ ብዬ ካካፈልኩኝ አስተሳሰብ ብዙ የተለየ ኣይመስለኝም።
ዛሬም ቢሆን የቋንቋ ጥያቄ ወሬን በንዝህላልነት ማስተናገድ ሳይሆን በተግባር ምን ያህል ችግር ኖሮት ነዉ? የኣንድ ሃገር ዜጎች ከሰሜን እስከ ደቡብ እና ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እንደ ኣንድ ሃገር ወገን በመሆን ተባብሮ ማደግን እንጂ በቋንቋ ምክንያት ብቻ በጥርጣሬ ዐይኖች እየተያዩ ተባብረን እንደግ ማለት እንዴት ነዉ የሚቻለዉ ለማለት ነዉ።