ለዚህ የእንግሊዘኛ ሀረግ ተመጣጣኝ የሆነ የኣማርኛ አገላለጽን ኣሁን ኣላስታዉስም። የሚከተለዉን ሌላ መነዛነዝ፣ ቅብጥርስም ይሁን ቅርስ፣ የሚገልጽ ከሆነ።
እንዲህ ይጀምራል። የእስፖርት ኣስተማሪ ኣንድ የኮሌጅ ተማሪ ኣፍ እላፊ ተናገረኝ የሚል ሶሞታ ያቀርባል።
ኣፍ እላፊ ሲሰማ የእስፖርት ኣስተማሪዉ የእስፖርት ሜዳ ዉስጥ ነበረ። የተናጋረዉ ተማሪ ከእስፖርት ሜደ ርቆ በሚገኝ የተማሪዎች ዶርም ወይም መኖርያ ፎቅ ላይ ነበር። ቀልድ ኣድርጎት ይሁን ኣይሁን ከእስፖርት ሜዳዉ ኣሻግሮ በርቀት ከሚገኘዉ ፎቅ ላይ ተናገረ።
የእስፖርት ኣስተማሪዉ ጆሮ ደርሶ ተገቢ ኣይዴለም ኣለ። ምናልባትም የእስፖርት ሜዳ ዉስጥ ትንሽ ተሯሩጦ የሰማዉን የተማሪ አፍ እላፊ ረግቦለት ታዝቦ ከመተዉ ከሜዳዉ በሩጫ ኣንድ ተማሪ ኣፍ እላፊ ተናገረኝ ብሎ ከሰሰ።
በሩጫ፣ ምክንያቱም በፎቁ ዉስጥ ይኖሩ ከነበሩት ብዙ ተማሪዎች የተናገረዉ ጫት በመቃም የሚታወቅ ነዉ ኣለ። ማረጋገጫዉ የዛ ተማሪ ጫት መቃም መዉደድ ነበር ማለት ነዉ።
ስሞታዉን የሰማዉ የዲሲፕሊን ኮሚቴም በፍጥነት ለዚህ ስሞታ ያ ተማሪ ለኣንድ ዓመት ተቀጥቶ ወደ ትምህርቱ ይመለስ የሚል ዉሳኔ በማስተላለፍ ማስታወቅያ ለሁሉም ተማሪዎች ዱብ ኣደረገ።
ዱብዳዉ ለሁላችንም ቶሎ ኣልተዋጠልንም። የተቀጣዉን ተማሪ ማን ወክሎት ይህ ፍርድ ፍትህ ሊሆን ይችላል? ይህ ነገ በእኔ ነዉ ብለን መጠየቅ ጀመርን።
ተወካዮቻችሁን ምረጡ እና በእነሱ በኩል እንነጋገር ተባልን። ብቃቱ ኖሮኝ ይሁን የሽግግር ግዜ እድል ደርሶኝ ይሁን ባላዉቅም የተወካዮች መሪ ሆንኩኝ። ፍላጎቱ ያልነበረኝ ቢሆንም።
የተማሪ ተወካዮች ፍርዱን ከሰጡት ጋር ብያንስ ሁለቴ ተሰብስበናል። የእኛ ጥያቄ ዉሳኔዉ የተደረገዉ ለተቀጣዉ ተማሪ መብት የቆመ አካል ባልነበረበት ስለሆነ ዉሳኔ የተማሪዎች ተወካይ በተሳተፈበት እንደገና ይታይ ነበር። ለስሞታዉ ኣይቀጣ ሳይሆን ስሞታዉ እሱንም የሚወክል አካል ባለበት እንደገና ይታይ ነበር።
የዲሲፕሊን ኮምቴዉ ፍርዳችን ፍትህ ስለሆነ ተቀበሉ ሆነ።
በዚህ ሁለት ሀሳቦች ስላልተስማማን ብዙ ተከራከርን። የድሲፕሊን ኮምቴዉ አባል የነበረ የወቅቱ ሬጅስትራር ክርክራችን የእስራኤል እና የፍልስጤም አይነት ሆነ እስከማለት ደርሶ ነበር።
የተማሪዎች ተወካዮች የደረስንበትን ለተማሪዎች ስንነግራቸዉ ተገቢ ኣይዴለም ወደሚል አመጽ ደረስን።
ኣንድ ቀን ትምህርት ኣቁመን የፍርዱን መሪ ለመጠየቅ ቢሮዉ ሄድን። ማነጋገር ብቻ ነበር የፈለግነዉ። ከቢሮዉ ወጥቶ ኣላነገረንም። ከቢሮዉ እስኪወጣ ቁጭ ብለን ጠበቅን። ኣልወጣ ኣለ።
በከተማዉ ለነበሩ ኣዲስ የኢሕኣዲግ አለቃዎች ተማጽኖ ድረሱልኝ ኣላቸዉ። እኛ ዉጪ ቁጭ ብለን ስንጥብቅ ለካስ የቢሮዉ ዉስጥ ስልክ ቢዚ ነበረ።
ከዛም ከአዲስ አለቃዎች ጋር ሆነን ጥያቄያችሁን ለመስማት ተዘጋጅተናል የሚል መልዕክት ተነገረን። ለስብሰባም የሚሆን የምግብ አዳራሽ ዉስጥ ተሰብሰቡ እና ጠብቁን፣ እዛ እንመጣለን ተባልን። እሺ ብለን ወዳ እዛ ኣቀናን።
የፈራጁ መሪ ጠብቁኝ እንኳን ሳይለን ወደቤቱ ኣቀና፣ መጀመርያ ምሳ ለመብላት። እኛም ምሳ ሳንበላ ቆይተን ጠብቁኝ ብሎ ወደቤቱ ይሄዳል ወይ ብለን በሌላ አመጽ ስንጠብቅህ ነዉ የቆየነዉ፣ ና እና እንነጋገር ለማለት ተከተልነዉ።
የእኛ እንመጣለን ብለሀን ሀሳብህን ቀይረህ ወደ ቤትህ ትሄዳለህ ወይ ብሎ መከተል ለሌሎች አስተማሪዎች ሌላ ግርግር መሰለ።
ከተከተልነዉ በኋላ ሳይቆይ መጥቶ ከኣዲሶቹ አለቃዎች ጋር ሆነዉ ጥያቄያችን ምን እንደሆነ ግለጹልን ተባል። በስነ ስርኣት በኣጭሩ ገለጽናላቸዉ። የተፈረደበት ተማሪ ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ ነዉ ኣልናቸዉ።
ኣዲሶቹ አለቆች ጥያቄያችሁ ተገቢ ነዉ ኣሉ። የተጠሩብን ፈረዱልን። እሺ ብለን ስብሰባዉ ኣበቃ።
በዚህ አመጻችን ዉስጥ ኣንድ መስታወት ወይም ኣንድ ሳህን ኣልሰበንም።
የእኛ ጥያቄ ተፈቷል ብለን ወደ ትምህርት ገበታችን ለመመለስ እየተዘጋጀን በማግስቱ ሌላ ስብሰባ ከሌሎች በከተማዉ ከነበሩ የኢሕኣዲግ መሪዎች ጋር ስለምናደርግ እንደገና እንሰብሰብ የሚል መልዕክት ደረሰን። እሺ ብለን ሄድን።
ስለፍርዱ ማብራራት ተጀመረ። ኣዳመጥን።
ስለይግባኙ ማብራርትም ቀጠለ። ተፈታ ተብሎ የነበረዉ ይግባኝ እንደገና ማገርሸቱ ገርሞኝ በጥሞና ሳዳምጥ ኣንድ ተማሪ የዘገየሁ መስሎት ተናጋር እንጂ እስከሚለኝ ደረሰ።
እኔም መናገር ስጀምር ኣዲሱ የኢሕኣዲግ አለቃ ስምህ ማነዉ ብሎ እኔን በመጠየቅ ጀመረ። ያገረሸዉ ለዚህ ነዉ በሚመስል ተማሪዎች ድምጽ ማሰማት ጀመሩ። የቅርብ ጓደኛዬ ስሙን ለምን ትጠይቃለህ ብሎ የኢሕኣዲጉን አለቃ በቁጣ የጠየቀዉ የማይረሳ ነዉ።
የተማሪዎችን ቁጣ በተቻለኝ አቅም እጆቼን በማራገብ ኣረጋግቼ፣ ስሜን ተናግሬ፣ መልስ ሰጠሁኝ።
ስብሰባዉ ብዙም ሳይቆይ ተማሪዎች አካሄዱን ትተዉ ወጡ።
በከተማዉ የነበሩ ተተክተዉ የመጡት ኣዲሶቹ አለቆች ተመልሰዉ ሄዱ። ምክትል ዲኑም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እኔም ተረጋግቼ ከስብሰባዉ ኣዳራሽ ወደ ዶርም ተመለስኩኝ። ምክትል ዲኑም ወደ ቤቱ ሲመለስ፣ እኔም ወደ ዶርም ስመለስ ማዶ ከማዶ እያየሁ።
ብዙም ሳይቆይ በስራ ምክንያት በአከባቢዉ ያልነበረ ዋናዉ ዲን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርዚቲ ቴክኖሎጂ ፋካልቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበረ፣ ተመልሶ መጣ።
ሳያድር ምሽቱን ወደ ዶርም ብቅ ብሎ ተማሪዎችን ፈልጎ በርካታዎችን ኣነጋገረ።
ለካስ በከተማዉ ወደ ነበረዉ በቀለ ሞላ ሆቴል ብቅ ብሎ እዛ ይዝናኑ የነበሩ ፍረንጆ የእኛ የተማሪዎች አመጽ ጀርባ ኦነግ አለ የሚል ወሬ ጆሮዎቹ ደርሰዉ ነበረ።
ሳያድር ተማሪዎች ዶርም ድረስ በመምጣት ካነጋገረ በኋላ መጀመርያ ኣዳራሹ ዉስጥ ሰብስቦ ኣነጋገረን። ስሞታችንንም ኣዳመጠ። ቀጥሎ የተማሪዎች ተወካዮችን ጠርቶ ኣነጋገረን።
ጥያቄያችን ተገቢ መሆኑ ኣሳምኖኛል ኣለን። ቀጥሎም ዶርም ድረስ መጥቼ ተማሪዎችን ያነጋገርኩኝ ይህ አመጽ ጀርባ ኦነግ ኣለ የሚል ወሬ ደርሶኝ ስለነበረ እዉነት ከሆነ ለመለየት ነበር ኣለን። ከተማሪዎች የሰማሁት ስለወሬዉ ኣላሳመነኝም። ስለዚህ ይህን ጉዳይ እኔ ኣይቼ ፍትህ እሰጣለሁ ኣለን።
ምክትል ዲኑ ተሰብሰቡ ብሎን ሀሳቡን ቀይሮ ወደቤቱ የሄደ ግዜ ተከትለን መሄዳችን ሌሎች ኣስተማሪዎችን ስላስቆጣ እነሱን ለማረጋጋት ግዜ ስጡኝ ኣለ። እሺ ኣልነዉ።
እኔ ጉዳዩ በእሱ በኩል ተፈቷል ብዬ ትኩራቴን ወደ ትምህርት መለስኩኝ።
ከዛም ቋሚ የተማሪዎች ኮሚቴ ይቋቋም ሲባል እኔ ትኩረቴን ወደ ትምህርት ማመዘን ስለምፈልግ ኣልፈልግም ብዬ ሌላ ኮሚቴ ተቋቋመ።
የምንተዋወቀዉ ሬጂስትራር የነበረዉ እና ክርክራችን የእስራኤል እና ፍልስጤም መሰለ እስከማለት የደረሰዉ ኣንድ ቀን መንገድ ላይ ኣይቶኝ ለምን እምቢ ኣልክ ሲለኝ ወድያዉ እንከፋፈል ብዬ ነዉ የሚል መልስ መጣልኝ። በጣም ስቀ።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ አፍ እላፊ የተናገረዉ የተቀጣዉ ሳይሆን ሌላ ተማሪ መሆኑን ሰማሁኝ። ሁለታቸዉንም የማዉቃቸዉ ቢሆንም የተናገረዉን የበለጠ ኣዉቃለሁ።
ከዛም ጉዳዩ አብደታ በተናገረ ጉደታ መቀጣት ሆነ። ወይም በለዉ በተናገረ እንዳለ መቀጣት ሆነ።
በጉዳዩ ስንቶች ተሳሳቱ።
፩) የእስፖርት ሜዳ ዉስጥ ወድህ ወድያ ተሯሩጦ አፍ እላፊዉን በትዝብት ማለፍ ያልቻለዉ ወይም የተናገረዉን ተማሪ ማንነት ሳያረጋግጥ ለመክሰስ የሮጠዉ የእስፖርት ኣስተማሪ
፪) የዲሲፕሊን ኮሚቴ
፫) የኮሚቴዉን ዉሳኔ ያጸደቀዉ አካል
፬) ለሁለተኛ ግዜ ተጠርተዉ የመጡት በከተማዉ የነበሩ ኣዲሶቹ የኢሕኣድግ አለቆች
፭) ለዲኑ ኦነግ ከጀርባዉ ኣለ ብለዉ ያወሩት ፈረንጆች
በዚህ ምክንያት ይሁን በሌላ የፈለኩት እና ይገባዋል የተባለ ስራ ተጠይቆ ኣልፈልግም ብሏል ተብሎ ከተመረኩ በኋላ ያስተማረኝን ቦታ ተሰናብቼ ወጣሁ።
ከዛም በኋል መንግስት ምሩቃንን ስራ ላይ የሚመድብበት ግዜ ስለነበረ ያስተማረንን ኮምሽን ስራ ላይ መድቡን ብለን ድጅ ጥናት ጀመርን።
ኣንድ ቀን የኮሚሽኑ ምክትል ኮምሽነር ልያነጋግሯችሁ ይፈልጋሉ እና ተወካዮቻችሁን ወደ ቢሯቸዉ ላኩ የሚል መልዕክት ሰማን።
ተወካዮች ኣዘጋጅተን ስላልነበረ በፍጥነት እነማን ይሁኑ ተባለ። ኣሁንም እድሉ ደርሶኝ የተወካዮች መሪ ሁን ተባልኩኝ።
ከዛም ቢሮ ገብተንስ ምን እንበላቸዉ የሚል ጥያቄ በቅጽበት መጣ። ብዙ ያልታሰቡበት ሶስት ሀሳቦች መጡልኝ። ኣንደኛ) የተማርነዉ ሕዝብ በከፈለዉ ቀረጥ ስለሆነ እኛን ስራ ላይ መመደብ መንግስት ሀላፊነት አለበት፣ ሁለተኛ) ተምራን ስራ ላይ ካልተሰማራን የተማርነዉን እየዘነጋን እንሄዳለን፣ ሶስተኛ) ተምሮ ያለስራ መቀመጥ የምሩቃንን ሞራል የሚጎዳ እና ወደ ኣላስፈላጊ ነገሮች የሚመራ ሊሆን ስለምቺል ስራ ስጡን ነበር።
እነዚህ አስተሳሰቦች ሁላችንም ስናስብ የነበረ ነዉ ማለት ይቻላል። ነገር ግን ያልተጠበቀ ሀላፊንትን ቶሎ መዉሰድ እና ያልተጠበቀ ስብሰባ ላይ ቶሎ ሀሳብ ኣሰባስቦ መቅረብ የማይረሳ ስለሆነ ቃል በቃል ባይሆንም በደንብ ኣስታዉሳቸዋለሁ።
ኮምሽነሩ አጠር ያሉ ትሁት ሰዉ ነበሩ። ምናልባትም ሀሳቦቻችንን በደንብ ያስታዉሱ ይሆናል። ብዙም ኣልተናገሩም። መልስ እንሰጣቸዋለን ብለዉ ስብሰባዉ ኣበቃ።
ይህ መነዛነዝ በወቅቱ ከያዝኩኝ ማስታወሻ ሳይሆን ኣሁን ከማስታዉሰዉ ነዉ። የተሳሳትኩኝ ወይም የዘነጋሁኝ ካሉ እታረማለሁ፣ ይጨመሩበት።