****************************
የኦሮሞ የባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ማዕከል እና የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ በዘርፉ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።
በኦሮሞ የባህል ማዕከል እየተካሄደ ባለው ውይይት በአፋን ኦሮሞ የተጻፉ ታሪኮች እና ቅርሶች በስጦታ መልኩ ለትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ተበርክተዋል።
የኦሮሞ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት የሁለቱን ክልሎች ቋንቋዎች፣ ባህል እና ታሪክን ለማሳደግ በጥናት እና ምርምር የታገዘ ሥራ እንሠራለን ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲሪባ ተፈራ በውይይቱ ላይ የተገኙ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችም አፋን ኦሮሞን፣ የኦሮሞን ባህል እና ታሪክ አስመልክቶ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል ተኽሉ አካዳሚው በ2008 ዓ.ም የተመሠረተ መሆኑን ገልጸው፣ የትግራይ ቋንቋዎችን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ የተለያዩ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ብለዋል።
ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያለንን ወንድማማችነት እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከርም ከኦሮሞ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እንሠራለን ብለዋል።
የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ባለፉት 2 ዓመታት በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሥራዎች ሳያከናውን መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን የኦሮሞ ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ለማዕከሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።
አበባ አርኣያ
Please wait, video is loading...