በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ሹመት መንዶካ በሚባል ከተማ በሱዳን በመሰልጠን ላይ የሚገኘው ፅንፈኛዉ የሳምሪ ቡድን ሰርጎ በመግባት የሰው ህይወት ማጥፋቱን እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታውቋል ።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገደማ ሰርጎ የገባው ፅንፈኛው የሳምሪ ቡድን ቁጥሩ በመጣራት ላይ የሚገኝ የሰው ህይወት ሲቀጥፍ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። በተጨማሪም የቁም እንስሳት ዘርፎ መሄዱን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አ/ቶ ቢክስ ወርቄ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።
የጉዳቱ መጠን ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን በቀጣይ እናሳውቃለን በማለት ተናግረዋል ።ይህ ሳምሪ የተባለው ፅንፈኛ ቡድን በማይካድራ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ንፁሃንን ጨፍጭፎ ወደ ሱዳን መሸሹ የሚታወስ ነዉ ።
ዞኑ ከሱዳን የሚያዋስን በመሆኑ የክረምት ወቅቱን ተከትሎ የእርሻ ስራ እንዳይከናወን ተደጋጋሚ ትንኮሳ እንደሚደርስ እና ከሰሞኑን ትንኮሳው መጠነኛ መሻሻል አሳይቶ እንደነበር ብስራት ሬዲዮ መዘገቡ ይታወሳል ።
