ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በጦርነቱ የተጎዱትን የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎችን ከጎበኙ በኋላ ለሰላም ተስፋ እንዳለ የገለጹ ሲሆን "በእርግጥ የሚስተዋለው ከጥቂት ወራት በፊት ከነበሩ ግጭቶች ያነሰ ነው" ብለዋል።
ከትግራይ አመራሮች፣ ከአማራ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደረጉት አሚና መሐመድ ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ" ብለዋል።
ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቀናት በፊትም መግለጻቸው ይታወሳል።
ሰላም ለማስፈን ግጭቱን እንዲሁም ተኩስ ማቆም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ የተናገሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተፋላሚ ወገኖች ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከዚህ ቀደምም ጦርነቱን ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ዋና ፀሐፊው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ከሆኑት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት እያደረጉት ስላላው ጥረት ከሕብረቱ ተወካይ መረዳታቸውን በወቅቱ አስታውቀው ነበር።
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ዋና ፀሐፊውን በመወከል የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በጦርነቱ የተጎዱ የአማራና የትግራይ ክልል ከተሞችን ጎብኝተዋል። እንዲሁም ከክልል አመራሮችም ጋር ተገናኝተዋል።
Continue reading https://www.bbc.com/amharic/news-60319702
