እንዳለመታደል ሆኖ የፖለቲካ ባህላችን ከመቀንጨሩ የተነሳ በሀሳብ ተለያይቶ ተከባብሮና ተዋዶ( ቢቻል) አብሮ መቀጠል የማይቻልበት ዘመን ላይ ደረስን። ይሄ እንደ ማህበረሰብ ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከባድ ዋጋ እያስከፈለን ነው፤ ወደፊትም የትውልድ እዳ ሆኖ ይቀጥላል። የፖለቲካ ነቀርሳ ከባድ በሽታ ነው፣ የፀረ-እድገትና ለውጥ ነቀርሳ።
↪መጀመሪያ አካባቢ በአቋምና ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ምክንያት ብዙ ጓደኞች አጣን። እኔ በግሌ የቅርብ ጓደኞቼን አጥቻለሁ። እኔ የሀሳብ ልዩነትን አክብሬ ለመቀጠል ብፈልግም ሁሉም ሰው የሁሉም ፀር ወይም ወዳጅ መሆን ስላለበት ቻልነው።
↪ቀጥሎ ግዚያዊ ፖለቲካ የምናከብራቸውን ሰዎች አሳጣን። ግማሹን የብልፅግና መንግሥት አስፈርሞ እንትን የነካው እንጨት አደረገው፣ የቀሩት ሞራል አልቦ ሆነው መንጋውን ሜዳ ላይ በትነው ቀሪውን ወደ ገድል ወረወሩት። እሱም ግድ የለም በግዜ ሂደት ሊስተካከል ይችላል የሚል ተስፋ ነበረን።
↪መጨረሻ ላይ ጦርነቱ መጣና ግራና ቀኝ አሰለፈን። ግማሹ አገር አዳኝ ቀሪው ባንዳ፣ የሩቁ ዘመድ የቅርቡ ባዳ፣ ገሚሱ ቅዱስ ቀሪው ሰይጣን፣ አንዱ ጀግና ሌላው ፈሪ፣ ወዘተ አድርጎ አሰለፈን። ጦርነቱ እንደ ጎርፍ የቀረውን እንጥፍጣፊ ይዞት ሄደ። ሰውነታችንን እስክንጠራጠረው ( ህሊና ላለው) ሁሉ አደረሰን። ሽማግሌ አሳጣን፣ የመንጋ እረኛ አሳጣን፣ ቤተሰብ አሳጣን፣ ዝምድና ወሰደብን፣ ጠላት አበዛልን፣ መጪውን ዘመን ሁሉ ቀማን።
ይሄ ጋንጩር ፖለቲካችን ምን ያላሳጣን ነገር አለ!?
ክፉ ዘመን ነው። ዝብርቅርቅ ያለ ግዜ። ግራም ቀኝም ያልገባው፣ ምንም ያልገባው ዘመን። የቁልቁለትና የጨለማ ዘመን። ይሄ ቀን ያልፍ ይሆን!???
Please wait, video is loading...