Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Ejersa
Member
Posts: 3978
Joined: 05 Nov 2019, 10:39

በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ የጦር መሳሪያዎች እና የመገናኛ ሬደዮኖች ተያዙ!

Post by Ejersa » 20 Nov 2021, 17:17

በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ 5 ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ እና 6 ሽጉጦች ከነተተኳሾቻቸው እንዲሁም 2 የእጅ መገናኛ ሬዲዮ እና ሌሎች ንብረቶችን ፖሊስ ይዟል፡፡

ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል አንደኛው ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ በዕድሳት ምክንያት ተዘግቷል በተባለ ፔንሲዮን ግቢ ውስጥ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ የተቀመጠ ሲሆን መገናኛ ሬዲዮዎቹ ደግሞ በፔንሲዮኑ ኮርኒስ ውስጥ ተደብቀው የተያዙ ናቸው፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከሰፈራ አካባቢ ፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በክፍለ ከተማው ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ኮንፈርት ፔንሲዮን በዕድሳት ምክንያት በሚል ለረጅም ጊዜ ተዘግቶ መቆየቱ ያጠራጠራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ነው ብርበራው የተደረገው፡ ፖሊስም የአስቸኳይ ጊዜ

አዋጁን መሰረት በማድረግ ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ብርበራ 2 የእጅ መገናኛ ሬዲዮ በፔንሲዮኑ ኮርኒስ ውስጥ በፌስታል ተጠቅልለው ተደብቀው ተገኝተዋል።

አንድ ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ ከ19 ጥይት ጋር በሸራ ተጠቅልሎ ግቢው ውስጥ በሚገኝ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ መያዙንም ፖሊስ አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ካዝና ውስጥ የተቀመጡ 138 ግራም የወርቅ ጌጣጌጦች እና የውጪ ሃገር ገንዘብ በብርበራ ተገኝተዋል፡፡ በፔኔሲዮኑ ውስጥ ምንም አይነት ዕድሳት እየተደረገ አለመሆኑንም ፖሊስ አረጋግጧል፡፡

በተመሳሳይ በክፍለ ከተማው ወረዳ 3 የህወሓት እና ሸኔ የሽብር ቡድኖችን በተለያየ መንገድ ይደግፋሉ ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ 4 ክላሽን- ኮቭ ጠብመንጃ ከ140 ጥይት ጋር ፣ 6 ሽጉጥ ከ65 ጥይት ጋር እንዲሁም አንድ የእጅ ቦንብ በቁጥጥር ስር ውሎ በተጠርጣሪዎች ላይ ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል ።

አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ለሚገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋናውን እያቀረበ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እያስገኘ ያለው ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡