በአዲስ አበባና ክልሎች ከተሞች ውስጥ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደረግ እስራትና ወከባ አስመልክቶ ከሲዳማ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (SNLF) የተሰጠ መግለጫ
ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም (08 November 2021)
አንድ ዓመት የሞላው በትግራይ ሕዝብ ላይ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና በአጋሮቹ የተከፈተው ጦርነት ለተስፋፊ አማራ ልህቃን ግዛት ለማስፋፋትና የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ዋና መሰረት የሆነውን ሕገ መንግስት በመናድ አሀዳዊነትንና ነፍጠኛነትን ለማንገስ ያለመ መሆኑን በመጥቀስ በንፁሀን የትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ጭካኔ የተሞላና አረመኔያዊ ግፍ/በደልን የሲዳማ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር በተለያዩ ጊዜያት ሲያወግዝ መቆየቱ የሚታዎስ ነው ::
በዚህ ዓለማ የለሽ የፋሽቶች ጦርነት ሳቢያ በርካታ የኢትዮጵያ ብሔሮች : ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልጆች ደም እንደጅረት በየጦር ቀጠናዎች በከንቱ የፈሰሰ ሲሆን የአገሪቱ ሀብትና መሰረተ ልማቶችም ወድሟል::
ነገር ግን ብዙ ግፍና ሰቆቃ ከደረሰባቸው በኃላ የትግራይ ሕዝብና የትግራይ መንግስት ያንን ሁሉ መከራ ተቋቁሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጦርነት የበላይነትን ማግኘቱ በመሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው :: ሰላማዊውን ሕዝብ የወረረው የአምባገነኖች ቡድን ጦርነቱን አቁሞ ለሰላም እራሱን ማዘጋጀት በሚገባበት በዚህ ወቅት: አዲስ አበባ ከተማና ሐዋሳን ጨምሮ በተለያዩ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ከተሞች ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ከቤታቸውና ከስራ ገበታቸው ላይ እየታፈሱ እየታሰሩ መሆናቸውን መረዳት ችለናል ::
የሲዳማ ብሔርና ሕዝብ ፈርሃ እግዚአብሔር ያለውና በሞራል የታነፀ ሕዝብ ስለሆነ ወንጀል የፈፀመ አካል ካለ አግባብነት ባለው ሕግ ከመጠየቅ ውጭ ምንም ወንጀል ያልፈፀሙና ንፁሀን ዜጎች በዘራቸው/በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ተለይተው ጥቃት እንዲደርስባቸው ባህሉና እሴቱ አይፈቅድለትም ::
ስለዚህ የሲዳማ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (SNLF) ምንም ጦርነት በሌለበት ክልላችን ውስጥ በሐዋሳ: በይርጋዓለም : በአለታ ወንዶና ሌሎች ከተሞች ውስጥ በዘራቸው ምክንያት በንፁሀን የትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደረገውን እስራት : ወከባና እንግሊት አጥብቆ ከማወግዙም ባሻገር ከስራ ገበታቸውና ከቤታቸው የሚታፈሱ ዜጎች ላይ የምፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ በአስቸኳይ ቆሞ ወደ ቤታቸውና ወደ ልጆቻቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ አጥብቆ ያሳስባል ::
ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊስት ሐይሎች ያሸንፋሉ!!
ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ/ም (November 08, 2021)
https://www.facebook.com/sidaamuqeele.092016/