ጥቅምት 26/2014 (ዋልታ) ወያኔና ሸኔ ያላቸው ጥምረት የሚቀጥለው የወያኔን የበላይነትና የገዥነት ባህሪ መሸከም እስከቻለ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኦቢኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እብሪተኛው ወያኔ የኦሮሞን አቅም ስለሚያውቅ በኦሮሞ ላይ ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ባለፉት 27 ዓመታት የራሱን የበላይነት ለመጫን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ወያኔ በኦሮሞ ፖለቲካ ላይ አተኩሮ የሰራውም በመጀመሪያ የራሱን የበላይነት በሌሎች ላይ በመጫን ሌሎች ህዝቦች የበታችነትን እንዲቀበሉ ለማድረግ ነው ብለዋል።
27 ዓመታት ሙሉ የኦሮሞን ሀብት በመዝረፍ ህዝቡም ሆነ የኦሮሞ ልጆች ጥያቄና የተለየ ሀሳባ እንዳያነሱ ማድረግ ዋነኛው ዓላማው እንደነበረም ገልጸዋል።
የህዝቡን ትግል በስርዓት ለመምራት የሚችል ብቁ አመራር እንዳይወጣና የኦሮሞ ትግል ፍሬ እንዳያፈራ ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያብራሩት።
አሸባሪው ሕወሓት በህዝባችን ጫንቃ ላይ ይህንን የበላይነትና የገዥነት ባህሪ ሲጭን የኖረው በሀሰተኛ ፌደራሊዝም ስም ሲነግድ መኖሩን በማስታወስ ነበር።
https://twitter.com/walta_info