በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ ተቋምን ለማዘመን በተያዘው ስትራቴጂካዊ እቅድ የፖሊስ ሰራዊት አርማ እና የደንብ ልብስ እንዲቀየር በተወሰነው መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ/ም አዲስ የደንብ ልብስ እና የተቋሙን አርማ ሥራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል፡፡
አዳዲስ ተጨማሪ የደንብ አልባሳቱን ለማስተዋወቅ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ/ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባደረጉት ንግግር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን ሽብርተኛውን የህወሃት ቡድንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እየተፋለመ መሆኑን ተናግረው ለዘመቻው ስኬታማነት ዜጎች እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
መንግሥት የጀመረው የሀገርን ህልውና የማስከበር ዘመቻ በድል እንዲጠናቀቅ የከተማው ነዋሪ የማይተካ ሚና እንዳለው ኮሚሽነሩ ተናግረው ነዋሪው ከፀጥታ ሀይሉ ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር አካባቢውን በንቃት ሊጠብቅ እና ለፖሊስ መረጃ የመስጠት ተግባሩ ለከተማችን ፀጥታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከህዝቡ ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ከህዝብ የሚደርሳቸውን እያንዳንዷን መረጃ በአግባቡ በመቀበል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ኮሚሽነር ጌቱ አሳስበዋል፡፡
በሀገራችን የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት የፖሊስ ተቋምን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረው
አዳዲሶቹ የደንብ አልባሳት ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው የተቋማችንን ገፅታ ከመገንባት አኳያ ሚናቸው የጎላ በመሆኑ መላው የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት የደንብ ልብስ አጠቃቀምን አስመልክቶ በወጣው መመሪያ መሰረት የደንብ ልብሱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አመራሮችም መመሪያውን በአግባቡ እንዲያስፈፅሙ አሳስበዋል፡፡
ከዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ አዳዲሶቹ የደንብ አልባሳትን ብቻ መጠቀም እንደሚገባ እና ነባሩን የደንብ ልብስ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ አሮጌውን የደንብ ልብስ ለብሶ የተገኘ አመራርና አባል ላይ ጠንከር ያለ የዲስፕሊን እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት አሮጌው የደንብ ልብስ ሙሉ በሙሉ በአዳዲሶቹ መቀየሩን ተገንዝበው አሮጌውን የደንብ ልብስ የለበሰ የፖሊስ አባል ሲያጋጥማቸው መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ስራ ላይ ካዋላቸው አዳዲስ የደንብ አልባት ጋር ወይም ከሌሎች የፀጥታ አካላት የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ዩኒፎርም መጠቀም ክልክል መሆኑ በህግ የተደገገ ስለሆነ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ዩኒፎርም የሚጠቀሙ አካላት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተቋሙ መልዕክቱን አስተላልፏል።
25/02/2014
የልብ ድካም መንስኤዎችና መከላከያ ወሳኝ መንገዶች። ለጥንቃቄ መታየት ያለበት። መፍትሄዉ በእጃችን ነዉ:: ለማየት ሊንኩን ወይም ምስሉን ይጫኑ