Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 11587
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

– – – የመቀሌዉ ድምጽ ተሰማ

Post by sarcasm » 21 Dec 2020, 21:42

I just read this amazing comment on Zehabesha and I want share it with you. The comment was written on 14 December 2020 when the phone lines were restored in Mekele. The writer's name is Belay. I don't know the person but I was impressed at his narrating skills.

– – – የመቀሌዉ ድምጽ ተሰማ
Written by Belay - December 14, 2020


የአዲሳባዉ አቢይ አህመድ “ቀይመስመሩ ስለታለፈ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ——” ብለው በትግራይ ለ 3- ሳምንታት ያህል የዘለቀዉን ጦርነት መጀመር ይፋ ሲያደርጉ፡ ለእንደኔ አይነቱ “የፈሩት ይደርሳል – – ” የሚለዉ ብሂል እዉን የሆነበት ጊዜ ነበር።
ጦርነቱ በይፋ ከመታወጁ ሰአታት ቀደም ብሎ ጥዋት ላይ ከዚሁ ከአመሪካ መቀሌ ነዋሪ ለሆኑት እህቴና ባለቤቴ ደዉየ ሳናግራቸዉ፡ እህቴን “የጦርነት ድባብ አለ? ምናልባት ጦርነት ሊከሰት ይችላል – – ” ብያት ነበር። እስዋም ስትመልስልኝ “ምን – – አሁንም መግለጫ ነዉ። ያዉ ሁሌም እንደተለመደዉ – – – ። መግለጫዉን እንደሆነ ለምደነዋል። ማለቂያ የለዉም – – ” ነበር ያለችኝ።
ባለቤቴን ደግሞ “መቀሌ ላይ የጦርነት ሁኔታ ያለ ይመስላል?” ስላት “ምን እነዚህ በራሳቸዉ ጊዜ የለመዱትን ጦርነት አሁን ለኛ እያመጡብን ነዉ። ገና ሂወትን እየጀመርናት ላለነዉ እኮ ነዉ እያበላሹብን ያሉት። ህጻኑ ልጃችን ለምን ጦርነት ያያል? ጊዜዉ የኛ እንጂ የነሱ እኮ አይደለም” ብላኛለች።
በመጨረሻም “ለማንኛዉ ከቤት እንዳትወጡ። ጦርነት ሊኖር ይችላል!” ነበር ያልኳት።
ለሶስት ሳምንት የሚቀጥል ጦርነት፡ ከአንድ ወር በላይ ትግራይን በመዝጋት ድምጽ አልባ የሚያደርግ ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ ማሰብ ግን እንዴት ይቻላል? ማታ ላይ በድንገት የሆነዉ ነገር እሱ ነበር።
የመቀሌ ቤቴሶቦቼና ወዳጆቼ የማገኝበት የኢሞ አፕሊኬሽን ላይ በእንግሊዝ ቋንቋ የሚንነበበዉ ጽሁፍ “ለመጨረሻ ጊዜ መስመር ላይ የነበሩት ኖቨምበር 3 2020 ላይ ነዉ – – ” እንዳለ ከአንድ ወር በላይ ቆሟል። ልክ የመቃብር ድንጋይ ላይ ያለ ጽሁፍ ይመስላል። በዚሁ ቀን ነበር ጥዋት ላይ ከቤተሰቦቼ ለመጨረሻ የተገናኘነዉ። ከዚሁ ቀን በኋላም በኢሞዉ መደወያ ላይ ያሉት የቤተሶቦቼና ወዳጆቼ ፎቶግራፎችም የህያዉያን አልመስልህ አሉኝ። በየቀኑ እነዚህን ምስሎችንና ጽሁፍን ስመለከት ጸጸት ይለቁብኝ ነበር – – “ጦርነት እያጠላ መሆኑ ገብቶኝ ሳለ ሚስቴንና ልጄን ከመቀሌ ወደ አዲሰባ ለምን ዞር አላደረግኳቸዉም?” የሚል ጸጸት ሲሞሮምረኝ ቆይቷል – – ።
አመሪካ አገር አብራኝ ካለችዉ እናቴ ጋራ ስንነጋገር “ባለቤቴን ለምን ገንዘቡን በዛ አድርጌ አላኩላትም?” በየ እራሴን በምወቅስበት “በአንድ ምሽት፡ በድንገት እኮ ነዉ ሁሉም ነገር ቀጥ ያለዉ። ቴሎፎ ባይቋረጥ አንድ ነገር ማድረግ ይቻል ነበር” ብላኛለች ካንዴም ሁለቴም፡ ስታጽናናኝ።
ከዜህ በፊት ባለቤቴን ዳጎስ አድርጌ ገንዘብ ስልክላት “ለምን? ከበቂ በላይ ነዉ – -!” ትለኛለች። እኔም “የሚሆን አይታወቅም። ምን ግዜም ከእጅሽ በቂ ገንዘብ ቢኖርሽ ጥሩ ነዉ” እላት ነበር። ታዲያ፡ ዛሬ ዲሰምበር 13 2020 እንደገለጸችልኝ፡ ጦርነቱ ከመሆኑ ከጥቂ ቀናት በፊት የላኩላትን ገንዘብ ከባንክ ሳታወጣዉ ስለቀረች የባንክና የተሌፎን አገልግሎት በድንገት ቀጥ ሲል ጊዜ ከእጅዋ ምንም ገንዘብ አልነበራትም።
– በደርጉ ጊዜ በ17 አመታት ዉስጥ በትግራይና ኤርትራ ጦርነት እያየንና እየሰማን አድገናል። ምጽዋ በሻቢያ ተይዛና አስመራ ዙርያዉን ተከባና ተጨንቃ ከአንድ አመት በላይ በቆየችበት ጊዜም ከከተማዉ ነበርኩኝ። ነገር ግን እንዳአሁኑ ወቅት ህዝብ ያለ ቴሌፎን፡ ዉሃ፡ መብራትና የባንክ አገልግሎት ለአንድ ወር ዝግትግት ያለበት ሁኔታ አልነበረም። ትግራይን ያጋጠማት ይህንኑ ነበር። ለዚሁ ሁሉ ተጠያቂ ማን ነዉ? እንዲህ ለማድረግ ባለመብቱስ ማን ነዉ? ቤተሰቦቻችን ከፍተኛ አደጋ ዉስጥ ለመክተት ማን መብት አለዉ? በእዉነቱ የትግራይ ህዝብ ይህን ጉዳይ አጥብቆ መጠየቅ አለበት።
“ህግ ለማስከበር – – ” ይላል ይየፌደራል መንግስት። “ሳይቀድሙን፡ እራሳችን ለመከላከል – – ” የትግራዩ መንግስት ምክንያት ያቀርባል። ነገር ግን በማሃሉ ፍዳዉን ያየዉ የትግራይ ነዋሪ ምን ይላል?
“የሰሜን እዝ ተመታ – – ” የሚለዉ የፌደራል መንግስቱ ማብራርያ፡ የጦርነቱን ምክንያት አደገኛ አድርጎታል።
ለእንደኔ አይነቱ፡ ልክ የደርግ መንግስት ወድቆ ክረምት ሲሆን አዲስባ ከፒያሳ በረንዳ ላይ የገዘኋት መጽሃፍ “አፍሪካና አምባገነን መሪዎችዋ፡ ዘአፍሪካንስ፡ የምትለዋ መጽሃፍ ያሳፈረችዉ – – “አፍሪካ ዉስጥ ሰላም መጣ ብሎ መተማመን አይቻልም። ምን ግዜም ጦርነት ሳይታሰብ ይፈነዳል” የምትለዋ አረፍተነገር ነዉ ጦርነት በተቀሰቀሰ አጋጣሚ ከአምሮየ የምትመጣብኝ። ከኢህአዴግ ንግስና በኋላ ጥቂት አመታት እንደተቆጠሩ የፈነዳዉ የኢትዮ-ኤርትራዉ ጦርነት ይህቺንኑን አረፍተነገር ነበር ያስታወሰኝ። የዶክተር አቢይ የፍቅርና የሰላም መርሆ ከታወጀ በሶስት አመታት ዉስጥ ከትግራይ ክልል መንግስት የተገባዉ ጦርነት አሁንም ያቺኑ አረፍተ-ነገር ነዉ ያመጣብኝ።
ለጦርነታችን ማናችዉም ማብራርያና ምክንያት ልንሰጠዉ እንችላለን። ዞሮ ዞሮ ግን “አፍሪካ ዉስጥ ሰላም ሰፍኗል ብሎ መተማመን አይቻልም” ነዉ መደምደሚያዉ።
– መቀሌ ዛሬ እሁድ ዲሰምበር 13 2020 ድምጽዋ እንደተሰማ ከአንድ ወር በኋላ ያገኘኋት ባለቤቴ “ዋናዉ ጭንቀቱ ነበር የገደለን። በተለይ መጨረሻ ላይ አስቸጋሪ ሆኖብናል። ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመቱ አዳግቶን ነበር” አለችኝ።
“ገንዘብስ። ተቸገርሽ ነበር አይደል?” ስላት “እንደ አጋጣሚ በማንዋል ሰርተዉ አባቴን ደሞዝ ሰጥተዉት ነበር። እህልም አስፈጭተን ይዘን ቆይተናል። ዉሃ ነበር ከፍተኛዉ ችግራችን።”
“ወደ ገጠር ትሸሻለች ብየ ፈርቼ ነበር” ስላት፡
“ስዎች እንሂድ ብለዉን አበር። እኔ ግን ልጄን የት አስተኛዋሎህ? ይታመምብኛል ብማለት አብምቢ ብያሎህ። ለራሴ አልተጨነቅኩኝም። እዚሁ ከተማ ዉስጥ የሚሆነዉን እንቀበላለን ነዉ ያልኩዋቸዉ” አለችኝ።
“ልጄ ጦርነቱ አላስጨነቀዉም?” ስላትም
“ሚጎቹ በአከባቢ ስለደበደቡ ድምጹ አሸብሮታል። ከዚህ ቀደም በእጁ እያመለከተ አየር – – ብሎ ይደሰት ነበር። አሁን ግን አዉሮፕላን ሲያይ አየወድም” ብላኛለች።
እህቴንም ብቴሎፎ ሳወራት “ከፍተኛ ጭንቀት ነበር። በተለይ ‘ቲፒ ኤል ኤፍ’ ከከተማዉን ለቀዉ ሊወጡ ሲሉ ፍንዳታዎች ነበሩ” ብላኛለች።
ስለሶት አመቱ ልጄ ስጠይቃትም “ፍንዳታዎች ሲሰሙ አሁንስ ወዴት ነዉ የምንሄደዉ? ብሎ ጠይቋል አለችኝ። ስለሚጎቹ ስትነገረኝም “አየር እንዳትመታሽ ብቻሽን አትሁኚ። ወደኛ ቤት ነይ” ብሎኛል አለችኝ።

– ይሄዉ ነዉ – – ። ጦርነቱና ብጥብጡ ወደ ሶስተኛዉ ትዉልድ ዘልቋል። አዲስ የተወለዱ ልጆቻችንን ልክ እንዳባቶቻችን፡ ጦርነት፡ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ ቀዉስ እያወረስናቸዉ ነዉ። እኛዉ እራሳችን ችግሩን ስለምንፈጥረዉ መፍትሄዉ የለንም። በዚሁ ምክንያትም መከራችን ከፍ ያለ ይሆናል።