
በመሆኑም መላ የአገራችን የፖለቲካና የሲቪክ ተቋማት እንዲሁም የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገራችንን ከጥፋትና መበታተን ለመታደግ በአንድ ላይ ቆመን መታገል የሚገባን ታሪካዊ ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ለዚህም ሲባል የሃገራችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ያሳሰበን የኢትዮዽያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ ይቻል ዘንድ ለመላ የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ለመላ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት የሚከተለውን የሃገራዊ መድህን ጥሪ እናቀርባለን፡፡
1.የፌዴራሉ መንግስት በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያካሂደውን ግድያና የግፍ ተግባር በአስቸኳይ በማቆም ለሰላማዊ ሽግግር ዝግጁነቱን እንዲገልፅ፤
2.በፌዴራልና በክልሎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ ዜጎችን በሙሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችን ጨምሮ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈታ፤
3.ሁሉም የሌሎች አገሮች የፀጥታ ሃይሎች በተለይም የኢሳያስ መንግስት ያሰማራቸው የፀጥታ ሃይሎች ከአገራችን በአስቸኳይ እንዲወጡ እንዲደረግ፤
4.በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተጫነው ወታደራዊ አስተዳደር እንዲነሳ፤ ኮማንድ ፖስቶች እንዲፈርሱ፤ የፌዴራሉ መከላከያ ሰራዊት በህገመንግስቱ በተሰጠው ተልዕኮ እንዲገደብ፤ ክልሎች በህገመንግስቱ የተሰጣቸውን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን እንዳይጠቀሙ የሚሰነዘርባቸው ጥቃት እንዲቆምና በፌዴራልና በክልል ደረጃ ሰላምን የማስጠበቅና ህግ የማስከበር ስራ በብቸኝነት ለፌዴራልና ለክልል ፖሊስ ሃይሎች እንዲተው፤
5.ሁሉም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮዽያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች የሚሳተፉበትና ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የፌዴራልና የክልል የብዙሃን ማህበራትና የሙያ ድርጅቶችን ያካተተ ሃገራዊ የመድህን ሸንጎ እንዲመሰረት፤ ሸንጎው በአገሪቱ ለተከሰተው ቀውስ ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት የሚቻልባቸውን ስትራቴጂዎችንና መፍትሄዎችን እንዲመክር፤ እንዲሁም በአገሪቱ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ በህዝብ ተቀባይነት ያለው መንግስት የሚመሰረትበትን ሁኔታ እንዲያመቻች፤
6.የሸንጎ ምስረታውን ሂደት የሚያስተባብሩ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያተረፉና በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያላቸው እና የኢትዮዽያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስብጥር ግምት ውስጥ ያስገባ የአገር ሽማግሌዎች ቡድን እንዲቋቋምና የሰላምና የአገር መድኅን ሸንጎ ምስረታውን እውን እንዲያደርጉ፤
7.ሸንጎው በአገሪቱ ያሉትን ችግሮች ተወያይቶ ለሃገሪቱ ፖለቲካዊና ህገመንግስታዊ ችግሮች የጋራ መፍትሄ እስከሚያስቀምጥ፤ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረትና በፖለቲካ ሂደቱ ያገባኛል ባይ አካላት ጋር በሚደረግ ምክክር አገሪቱን የሚያስተዳድር የኢትዮዽያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስብጥር ግምት ውስጥ ያስገባ የባለሙያዎች የባላደራ መንግስት እንዲመሰረት፤
8.በኢህአዴግ ዘመን ተፈፀሙ የሚባሉትንና በተመሳሳይ መልኩ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተግባራት፤ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን፣ የፖለቲካ ግድያዎችን፣ ዘረፋና የውንብድና ተግባራት የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን እንዲመሰረትና ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፤ በይቅርታ የማይታለፉና በህግ ፊት ቀርበው መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ለይቶ እንዲያቀርብ፤
9.የሚድያ ተቋማት በህገ-መንግስት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ብቻ በመወጣት አገርን በማዳን ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ እንዲደረግ፤ ለዚህም ተግባራዊነት በጋራ ስምምነት ላይ የሚደረስበት አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን፤
10.አህጉራዊና አለማቀፍ የሰላምና የደህንነት ስጋትን ማስወገድ ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን በሚደረገው ጥረት አህጉራዊና አለማቀፍ አጋሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ፤
11. ይህንን ታሪካዊ አገርን የማዳን ተግባር በመደገፍ መላ የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና የሲቪክ ድርጅቶች ሃገራዊ የመድህን ጥሪውን በመደገፍ እንዲሰለፉ የሰላም ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የኢትዮዽያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድህን
መስከረም 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
