
The former OPDO official who decided the Government of Oromia State to leave Finfinne/Shagar now tasked to establish a bank in the name of Shagar to help the corrupt OPDO officials to launder their dirty money.
አቶ ጁነዲን ሳዶ ‹‹ሸገር›› የተሰኘ ባንክ ለመመሥረት እንቅስቃሴ ጀመሩ
የኦሮሚያ ክልልን በፕሬዚዳንት ከመመራት ባሻገር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በስደት ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ‹‹ሸገር›› ባንክ የተባለ አዲስ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ በመጀመር የባንኩን የአክሲዮን ሽያጭ አስጀምረዋል፡፡
አቶ ጁነዲን ሸገር በሚል መጠሪያ የሰየሙትን ባንክ ለማቋቋም የተሰባሰበውን አደራጅ ኮሚቴ በአስተባባሪነት እየመሩ ሲሆን፣ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሟላት ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር ከመከሩና አክሲዮን የሚገዙ በርካቶችን ከጎናቸውን ካሰለፉ በኋላ ወደ ካፒታል ማሰባሰብ ሥራ መግባታቸው ይጠቀሳል፡፡
ከሸገር ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ በተሠራጨው መረጃ መሠረት፣ እንደ ሕጉ አግባብ አንድ አክሲዮን የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ይኖረዋል፡፡ አንድ ባለአክሲዮን ከአሥር አክሲዮኖች ጀምሮ መግዛት ይችላል ተብሏል፡፡ ባንኩን በተያዘው ዓመት መጨረሻ ሥራ ለማስጀመር መታቀዱን ከአደራጅ ኮሚቴው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሸገር ባንክን ለመመሥረት አቶ ጁነዲን ጨምሮ 150 አደራጆች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ ካፒታል በማሰባሰቡ ረገድ ባንኩ ውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራም ተጠቅሷል፡፡ የባንኩን አብላጫ ድርሻም በገጠሩ ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት በማድረግ የአክሲዮን ሽያጩ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡
የባንኩ አደራጆች፣ ከባንኩ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑና ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት ሐሙስ፣ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል የባንኩን አቅጣጫ የሚያመላክት ትንታኔ አቅርበዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ እንደተጀመረ ተገልጾ፣ ከታዋቂ ግለሰቦች መካከል ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ አቶ ጁነዲን ሳዶ፣ አቶ ጌቱ ገለቴ፣ አቶ ድንቁ ደያስና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡ የተለያዩ ከተሞችን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችና ከንቲባዎች እንዲሁም አባ ገዳዎች ተሳትፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንክ ለማቋቋም 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የሸገር ባንክ የተፈቀደ ካፒታል እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡ የባንኩ አደራጆች ቢሮ ቦሌ መንገድ ላይ በሚገኘው ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ላይ መከፈቱም ታውቋል፡፡
የሸገር ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጁነዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያቅፍ እንደሚደረግ በተለይ ግን ለገበሬው ክፍልና በተለያዩ ከተሞች በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ተደራሽ የፋይናንስ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ይታሰባል፡፡ ባንኩ የገጠሩን ክፍል ከከተማው ጋር በማስተሳሰር የገቢ ምንጩ እንዲሰፋ የማገዝ ዓላማ እንዳለውም አቶ ጁነይዲ ጠቅሰዋል፡፡
የአክሲዮን ሽያጭ በ10 ባንኮች መሸጥ ጀምሯል።

